ፓርቲዎችን የሚመለከቱት የምርጫ ሕግ የማሻሻያ አንቀጾች በጥንቃቄ እንዲታዩ ተጠየቀ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 5 2017ፓርቲዎችን የሚመለከቱት የምርጫ ሕግ የማሻሻያ አንቀጾች በጥንቃቄ እንዲታዩ ተጠየቀ
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ላይ ትናንት በተካሄደ የሕዝብ መድረክ ፓርቲዎች ከአባላት 30 በመቶ መዋጮ እንዲሰበስቡ የሚያስገድደው ረቂቅ ድንጋጌ እንደገና እንዲታይ ተጠየቀ።
ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች የድጋፍ ፊርማ ቢያንስ ከሰባት ክልሎች እንዲያሟሉ በሚል የተካተተው አንቀጽም ከሀገሪቱ ኹኔታ አንጻር ፈታኝ ነው በሚል እንዲከለስ ጥያቄ ቀርቦበታል።
በውይይቱ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች እና አባላትን ካልተገባ እንግልት እና መዋከብ ሊከላከል የሚችል ድንጋጎ በረቂቅ ማሻሻያው እንዲካተት ሀሳብ ቀርቧል።
በሌላ በኩል የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም እንኳ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚጠይቅ ቢሆንም ሀገሪቱ የምትከተለው የምርጫ ሥርዓት እንዲለወጥም ጠይቀዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ውይይት እየተደረገበት ያለው ረቂቅ የማሻሻያ ሕግ ሃይማኖትን፣ ብሔር መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ልማዶችን እንዲያስቀር፣ አልፎም የፖለቲካ ድርጅቶች ከአባሎቻቸው ቢያንስ 30 በመቶ መዋጮ መሰብሰብ ካልቻሉ ከመንግሥት የሚደጎሙትን ገንዘብ እንዳያገኙ መከልከሉን የሚቃወሙ ሀሳቦች የተንፀባረቁበት ሆኗል።
"እኛ ባለንበት ኹኔታ 30 በመቶ መክፈል እንችላለን ወይ? ቢያንስ ወደ አምስት ወይም አሥር በመቶ ዝቅ ብታደርሁት" ፣ አብዛኛው የተቃዋሚ አባላት ሥራ አጥ በሆኑበት 30 በመቶ አሁንም ብዙ ነው"።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሳሰቢያ እና የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ምላሽ
የፖለቲካ ምህዳሩን ስለሚያሰፋ እና ስለሚያበረታታ በሚል የመንግሥት ሠራተኞች በምርጫ ለመወዳደር እጩ ሆነው ሲቀርቡ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያካሂዱበት ወቅት እና ምርጫ በሚከናወንበት ጊዜ "ከደሞዝ ጋር" ረፍት እንዲሠጣቸው የተካተተውን ማሻሻያ በአዎንታ የተቀበሉ የድርጅት መሪዎች ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት በአራት ክልሎች ማሰባሰብ ይጠይቅ የነበረውን የድጋፍ ፊርማ ወደ ሰባት ከፍ ማድረጉን ግን አልተቀበሉትም።
"በጸጥታ መታወክ ምክንያት የመመዝገብ አቅሙ ተሽመድምዶ እንዳይሳተፍ መደረግ የለበትም"። በቁጥር ላይ የተመሠረተ ድጋፍ ይዞ ወደ ምርጫ ይምጣ የሚባለ በፍፁም የሀገሪቱን ፖለቲካ ሁኔታ በተጨባጭ የተረዳ ሕግ አይደለም"።
የፖለቲካ ፓቲዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በምርጫ ቦርድ አወያይነት በተካሄዱ መድረኮች ያነሷቸው የማሻሻያ ሀሳቦች በረቂቁ አለመካተታቸውም ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው የሕዝብ መድረክ ላይ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን አስቀድሞ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚጠይቅ ቢሆንም ሀገሪቱ የምትከተለው የምርጫ ሥርዓት የበርካታ ድምፅ ሰጪዎችን ተሳትፎ ከንቱ የሚያስቀር በመሆኑ እንዲሻሻል ያስፈልጋል የሚለው አንደኛው ጉዳይ ነው።
"የተመጣጣኝ የምርጫ ሂደት መስተካከል አለበት"
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ተደጋግሞ ጥያቄ ለቀረበበት የአባላት መዋጮ ጉዳይ በይበልጥ ሰፋ ያለ መብራሪያ ሰጥተዋል።
"እየተጠየቀ ያለው ከሚመጣው የአባላት ስብስብ ቢያንስ 30 በመቶው አባላት ለፓርቲያቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው"።
በውይይት ሂደት ላይ ያለው ማሻሻያ ሕግ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥፋት አጥፍተው ሲገኙ ከመሰረዛቸው በፊት ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ታግደው እንዲቆዩ እና የቦርዱ የሥራ አመራሮች ሥራ በለቀቁ በአምስት ዓመታት ውስጥ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም አመራር እንዳይሆኑ የሚያደርግ ረቂቅንም ያካተተ ነው።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ