ፈናን ፔይ፤ ለኦንላይን ክፍያ እና ግብይት ምን ይዞ መጣ?
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017ገንዘብ ነክ ቴክኖሎጂ (Fintech) እንደ ሞባይል ባንኮች፣ ዲጂታል ክፍያዎችን፣ ቁጠባ፣ ብድር እና የመድህን አገልግሎት (ኢንሹራንስ) የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ከዚህ በፊት ተጠቃሚ ላልሆኑ ህዝቦች ያቀርባል። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ሀገራት የፋይናንስ አካታችነትን ለመጨመር፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ እና ድህነትን ለመቀነስ በእጅጉ ጠቃሚ ነው።
ያም ሆኖ እንደ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ የፊንቴክ ወይም የገንዘብ ነክ ቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል።የኦንላይን ክፍያን ጨምሮ የሀገሪቱን የገንዘብ ዝውውር የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ዘርፉን በ2020 ዓ/ም ከፋይናንስ ውጭ ለሆኑ አካላት ከከፈተ ወዲህ የኦንላይን ክፍያን የሚያሳልጡ ገንዘብ ነክ ቴክኖሎጅዎች ፈቃድ ማግኘት ጀምረዋል።ከነዚህም መካከል በቅርቡ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኦንላይን ክፍያ መግቢያ ፍቃድ ያገኘው ፈናን ፔይ (FenanPay) የተባለው ዲጅታል መድረክ ይገኝበታል።
በንግድ ድርጅቶች እና በደንበኞች መካከል ስራን ያሳልጣል
በፈናንፔይ ዋና የስትራቴጂ ኦፌሰር የሆኑት አቶ አብዲ መኮነን እንደሚሉት ይህ ዲጅታል መድረክ በንግድ ድርጅቶች እና በደንበኞች መካከል የማሳለጥ ስራ ይሰራል።በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍቃድ ከተሰጣቸው 11 የኦንላይን ክፍያን ከሚያሳልጡ ገንዘብ ነክ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተቀላቀለው ይህ ዲጅታል መድረክ ፤የንግድ ድርጅቶች በማንኛውም የክፍያ ዘዴ ከደንበኞቻቸው የሚቀበሏቸውን ክፍያዎች አንድ ቦታ ላይ እንዲያገኙ ያስችላል።ይህም እንደ አቶ አብዲ ገለፃ ከዚህ በፊት የነበረውን የንግድ ድርጅቶች የአሰራር ውጣውረድ ያስቀራል።በተለይ በአሁኑ ወቅት ተጠቃሚው ከዲጅታል አሰራሮች እንዲያፈገፍግ የሚያደርጉ በምግብ ቤቶች እና ሱቆች የሚታየውን የኦንላይን ክፍያ ማረጋገጫ ችግርን ከመፍታት አንፃር ዲጅታል መድረኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም አስረድተዋል።
አገልግሎቱ አስተማማኝ ነው
ከሶስት ዓመታት በፊት በምጣኔ ሀብት እናበቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የተመሰረተው ፈናን ፔይ፤በጎርጎሪያኑ ጥቅምት መጨረሻ 2024 ዓ/ም የመጀመሪያ ፈቃዱን ያገኘ ሲሆን፤ ላለፉት አራት ወራት ደግሞ ሙከራ ላይ ነበር።ፌናን ፔይ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግብይት ፈቃድ ያገኘው 1.5 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የኦንላይን ግብይቶችን በማካሄድ የሙከራ ጊዜውን አጠናቆ ነው።ለመሆኑ አገልግሎቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
አቶ አብዲ አስተማማኝነቱን እንደሚከተለው አብራርተዋል።«ባለፈው «ላውንች» ከማድረጋችን በፊት ስንሰራ የቆየነው በአስተማማኝ መልኩ «ሲስተማችን» ማሳለጥ እንዲችል» በሙከራ ጊዜ እየሰራን ነበር።» ያሉት ባለሙያው፤ የፍናንፔይ የመረጃ ደህንነት በስርዓት መሰራቱን ከኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ( INSA ) ማረጋገጫ ማግኘቱን ገልፀዋል።ብሄራዊ ባንክም ዲጅታል መድረኩ ወደ ገበያ እንዲገባ ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ተገቢውን ማጣራት ማድረጉን አመልክተዋል። በሙከራ ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ዝውውር መደረጉን የገለፁት አቶ አብዲ በዚህም ወቅትም ፈናን ፔይ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠመው አመልክተዋል።
ለአጠቃቀም ቀላል ሆኖ ነው የተሰራው
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የዲጅታል ቴክኖሎጂ እውቀት ውሱንነት ግምት ውስጥ በማስገባት ፈናንፔይ አጠቃቀሙ ቀላል ሆኖ መሰራቱን የሚገልፁት ባለሙያው ፤ ከኢንተርኔት ተደራሽነት አንፃርም ያለበይነመረብ እና ያለ ስማርት ስልክ ክፍያዎችን መክፈል የሚቻልበትን ዲጅታል አማራጭ (USSD Push) አቅርቧል። የገንዘብ ማስተላለፊያ የአገልግሎት ክፍያውም አነስተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ፈናንፔይን፤ በድረ ገፅ ፣በአንሮይድ መተግበሪያእንዲሁም የጥሪ ማዕከል በማዘጋጄት በስልክ አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።ይህ ዲጅታል መድረክ ከሚሰጣቸው ገንዘብ ነክ አገልግሎቶች ባለፈ ፤ ለንግድ ድርጅቶች ሶፍትዌሮችን ማዘጋጀትን ጨምሮ ሰፋ ያሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችንም ይሰጣል።
ሌሎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን የማካተት ዕቅድ አለ
እንደ አቶ አብዲ ገለፃ ፤ዲጅታል መድረኩ በአሁኑ ወቅት በእንግሊዥኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች የሚሰራ ሲሆን፤ ለወደፊቱ ግን ሌሎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን የማካተት ዕቅድ አለ።61 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ የባንክ አገልግሎት አያገኝም የሚሉት ባለሙያው፤ ከዚህ የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ ቢያንስ የተወሰነውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ፤በከተሞች ሳይወሰን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በአነስተኛ የኢንተርኔት ግንኙነት እንዲሁምያለ ኢንተርኔት አገልግሎቱን የማስፋፋት ግብ መኖሩንም ገልፀዋል።
ፈናን ፔይ ፤ ቢትኔት ቴክ ሶሉሽንስ በተባለ የሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተመሰረተ ነው።ኩባንያው ድሬ ቲዩብ የተባለው የመዝናኛ ድረ-ገጽ መስራች በሆኑት አቶ ቢኒያም ነገሱ ተባባሪ መስራችነት የተቋቋመ ነው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ