ጽዱዋ ካፓኖሪ የጣሊያን ከተማ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017
አውሮጳ ውስጥ በዓመት አንድ ሰው እስከ 500 ኪሎ ግራም ቆሻሻ ከቤቱ ያስወግዳል ተብሎ ይገመታል። ምንም እንኳን ይህ ግምት በቀመር ተሰልቶ ቢገለጽም በየቀኑ የቆሻሻው መጠን እያደገ መሄዱ እየተነገረ ነው። የጣሊያንዋ ካፓኖሪ ከተማ ግን የቆሻሻን መጠን መገደብ እና አካባቢን ጽዱ አድርጎ መኖር ይቻላል በማለት ለሌሎች ትምህርት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል የቆሻሻ ቁጥጥርና ክትትል ስልትን ተግባራዊ በማድረጓ በምሳሌነት ለመጠቀስ በቅታለች።
ማርቲና ፒቺኒኒ አምስት አባላት የሚገኙበት ቤተሰባቸው ቆሻሻን ለማስወገድ የወሰደውን እርምጃ እንዲህ ያስረዳሉ፤
«አምስት አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ ነን፤ ሦስቱ ልጆች ሲሆኑ ሁለቱ አዋቂዎች ናቸው። በዓመት ሦስት ጆንያ ቆሻሻ ከቤታችን ይወጣል፤ በጥቅሉ ወደ 30 ኪሎ ይሆናል።»
በዓመት አምስት አባላት ከሚገኙበት ቤተሰብ 30 ኪሎ ቆሻሻ ብቻ? አንድ ግለሰብ በዓመት እስከ 500 ኪሎ ግራም ቆሻሻ ያስወግዳል የሚለውን ስሌት ጥያቄ ላይ የሚችል ነውና፤ ይህ የሚታመን ዓይነት አይመስልም። ግን እውነት ነው። እሳቸው ከነቤተሰባቸው በሚኖሩባት በማዕከላዊ ጣሊያን በሚገኘው ቱስካና ግዛት ውስጥ በምትገኘውና 47 ሺህ የሚጠጋ ነዋሪ ባለባት ካፓኖሪ ከተማ ግን ሰዎች ከቆሻሻ በጸዳ አካባቢ እየኖሩ መሆኑ ይነገርላቸዋል። እንዲህ ማድረግ ይቻላል ወይ ለሚሉም ሥርዓትን ተከትሎ ደረጃ በደረጃ እንዴት ከዚህ መድረስ እንደሚቻል ዘዴውን እያሳዩ ነው። ማርቲና ፒቺኒኒም የዚህች ጽዱ ከተማ ነዋሪና ለጽዳቱም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ቤተሰቦች አንዷ ናቸው። እንዴት አድርገው ከቤታቸው በየዕለቱ ቆሻሻውን እንደሚያስወግዱም ይናገራሉ።
«እዚህ ጋ ያለው ድጋሚ ሥራ ላይ መዋል የማይችል ቆሻሻ ነው። ለምሳሌ ለሥራ የምጠቀምባቸው ከጥጥ የተሠሩ ንጣፎች፤ ለአንዴ ብቻ የሚያገለግሉ የተጠቀምኩባቸው የጎማ እጅ ጓንቶች፤ ያው እነዚህ መጨረሻቸው ከሚጣለው ቆሻሻ ጋር አብሮ መውደቅ ነው።»
ዳግም ጥቅም ላይ ማዋል
መላው አውሮጳን ከቆሻሻ ለማጽዳት በአውሮጳ ሕብረት ሥር የተደራጀ ዚሮ ዌስት ዩሮፕ የተሰኘ ፕሮጀክት ተነድፎ እንቅስቃሴ ከጀመረ ውሎ አድሯል። የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ የቆሻሻ እና ቁሳቁሶችን መጠን እና መርዛማነት በዘዴ እንዲወገዱ፤ ሁሉም አቅምና ሀብቶች ተጠብቀው እንዲመለሱ እና እንዳይቃጠሉ ወይም እንዳይቀበሩ ምርቶችን እና ሂደቶችን መንደፍ እና ማስተዳደር ነው።
በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓም ብራስልስ ላይ የተቋቋመው ይህ ሲቪክ የማኅበረሰብ ትስስር ወይም ኔትወርክ፤ በ28 የአውሮጳ ሃገራት 35 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ያቀፈ ነው። ይህ ፕሮጀክት በሥሩ ከቆሻሻ የጸዱ ከተሞች ዘመቻ የተሰኘ እንቅስቃሴን ያቋቋመ ሲሆን በዚህ ዘመቻም ብራስልስ፤ ሙኒክ እና ሪጋን ጨምሮ ከ480 በላይ የአውሮጳ ከተሞች እና ማዘጋጃ ቤቶች እየተሳተፉ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
የዚህ ዘመቻ አባል የመሆኛ መስፈርቱ ደግሞ የነፍስ ወከፍ የቆሻሻ ገደቦችን ማስተዋወቅ እና 90 በመቶውን ቆሻሻ እንደገና ጥቅም ላይ የማዋል የረዥም ጊዜ ቁርጠኛ እርምጃን ማሳየትን ያካትታል። እስካሁን የዜሮ ቆሻሻ ዘመቻው ከተሳካላቸው ከተሞች መካከል የጣሊያኗ ካፓኖሪ፤ የጀርመኗ ኪል ከተማ ተጠቃሽ ናቸው። ከጀርመን ትላልቅ ከተሞች በሦስተኝነት የምትገኘውና ጀርመኖች ሙንሽን የሚሏት የባየር ሙኒክ መዲናዋ ሙኒክ ከተማና የምሥራቅ ጀርመኗ ላይፕዚሽ ከተሞችም ከዚህ ደረጃ ለመካተት ጥረታቸው ክትትል እየተደረገበት የሚገኙ ከተሞች ናቸው።
በአውሮጳ ከቆሻሻ የጸዳ ከተማ የሚለውን ማረጋገጫ ለማግኘት በአማካይ በግለሰብ ደረጃ ከ65 ኪሎ ግራም ያነ ቆሻሻ መጠን መድረስ ይኖርበታል።
አውሮጳ ውስጥ በዓመት በነፍስ ወከፍ ደረጃ አንድ ግለሰብ እስከ 511 ኪሎ ግራም ቆሻሻ ያስወግዳል ቢባልም ለዳግም ምርትነት የሚለው 38 በመቶው ብቻ መሆኑን የአውሮጳ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።
የጣሊያኗ ካፓኖሪ ከተማን ጽዳት ለመጠበቅ ተግባራዊ የሆነው ስልትም አብዛኞውን ከየቤቱ የሚጣል ቆሻሻን ለዳግም አገልግሎት የማዋሉ ዘዴ ነው። ማርቲና ፒቺኒኒም ሆኑ ሌሎች የካፓኖሪ ከተማ ነዋሪዎች የየዕለት ተግባራቸው አድርገውታል። ለምሳሌ ማርቲና ፒቺኒኒ ከቤት ቁሳቁሶቻቸው መካከል ከሌሎች የከተማ ነዋሪዎች ቤት ሊጣሉ የነበሩ ዕቃዎች እሳቸው ቤት ለዳግም አገልግሎት እንዲሰጣቸው አድርገዋል።
«ፍራሹ እና አልጋው፤ እንዲሁም ይህ ቁምሳጥን ከከተማዋ አንድ የሚታደስ ቤት የወጣ ነው። ደወልንና እንዲረዱን ጠየቅናቸው፤ ይህ በ1920 ዓም የተሠራ ቁምሳጥን ነው።»
እዚህ ጀርመንም ሆነ በአብዛኞቹ የአውሮጳ ሃገራት ሰዎች ቤት ሲለውጡም ሆነ አዲስ ቤት ሲገቡና ሲገዙ አዳዲስ የቤት ቁሳቁሶችን መግዛት የተለመደ ነው። ለዓመታት የተገለገሉባቸውን ሶፋዎች፤ ቁምሳጥንና መደርደሪያዎች የመሳሰሉ የቤት ዕቃዎችን ይጥላሉ። አንዳንዶች ለሚያውቁትም ሆነ ለማያውቁት ያንን ዕቃ ለሚፈልግ መስጠታቸው የተለመደ ነው። ሰዎች ካልወሰዱት ደግሞ እዚህ ጀርመን ሀገር እንዲህ ያሉ ያገለገሉ የቤት ዕቃዎች የሚጣሉባቸው ወቅቶች አሉ። የሚጣሉት ዕቃዎች አብዛኞቹ ዳግም ጥቅም መስጠት የሚችሉ እንደመሆናቸው ከተጣሉት መካከል የተሻሉትን አንስተው ወደሌሎች ሃገራት በተለይም ወደ ምሥራቅ አውሮጳ የሚወስዷቸው ነጋዴዎች ተሻምተው የእድላቸውን ይወስዳሉ። ይህን ማድረጉ አያስተችም አያስነቅፍምም፤ አያስከስስምም። በአንድ በኩል ይህ ለጽዳቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ የሚወስዱትም ለዳግም አገልግሎት እንዲውል ነውና።
«ሁለተኛ ዕድል መስጠት»
ቁሳቁሶችን ዳግም ጥቅም ላይ ማዋልን የሚደግፉ ወገኖች ይህን ድንቅ የጽዳት መንገድ «ሁለተኛ ዕድል መስጠት» ይሉታል። የጣሊያኗ ካፓኖሪ ከተማ ውስጥ ሪ ሳይክሊንግ ወይም ዕቃዎችን ዳግም ለጥቅም የማዋል እሳቤ ሰው በነባቤ ቃል ብቻ ሳይሆን ዕለት በዕለት በተግባር በኑሮው ሊገልጸው የሚገባ መሆኑን አሳይተውበታል። ከዚህ የጽዳት አብዮት ጀርባ ሮዛኖ ኤርኮሊኒ ይገኛሉ። ኤርኮሊኒ በካፓኖሪ ከተማ የዜሮ ዌስት ምርምር ማዕከል ባልደረባ ናቸው። በየቀኑ ከየቤቱ የሚጣሉ ቆሻሻዎች ተመዝነው ናሙናም ተወስዶላቸው ይታያሉ። የሮዛኖ ኤርኮሊንን ትኩረት የሚስበው የሚተርፈው ቆሻሻ ነው። በከተማዋ ከሚሰበሰበው ቆሻሻ 86,5 በመቶ የሚሆነው ዳግም ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ነው። ቆሻሻውን ከየቤቱ ደጃፍ ዞረው የሚሰበስቡ አሉ። እሳቸው እንደሚሉት ቆሻሻ ሁሉ የሚጣል አይደለም፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የአሰራር ችግር አለ ባይ ናቸው።
«ዚሮ ዌስት ማለት፤ ማደስ፤ ዳግም መጠቀም፤ እንዲሁም ሁኔታውን ማጤን ማለት ነው። ነዋሪዎቹ ቆሻሻውን ይለዩታል፤ የማይለይ ዓይነት ከሆነ ደግሞ ኃላፊነቱ የአምራቹ አካል ነው። ይህ የዲዛይን ሂደት ጉዳይ ነው። ምርቶች ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርገው መዘጋጀት አለባቸው እንጂ እንዲጣሉ መሆን የለበትም።»
በምርምር ማዕከላቸው የሚጣሉ ቆሻሻዎች ይመረመራሉ። አንድያውን በቆሻሻነት የሚጣሉት በአንድ መዝገብ ይጻፋሉ። ከዚያም ለፋብሪካው ስልክ ይደወላል፤ ወይም ደብዳቤ ይጻፋል። አብዛኛውን ጊዜም ከኩባንያው አዎንታዊ ምላሽ ያገኛሉ። በድርጅታቸው ከተመዘገቡ 107 ምርቶች መካከል ገሚሱ በአግባቡ ዳግም ሥራ ላይ መዋል የሚችሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በከፊል ዳግም ጥቅም የሚሰጡ ወይም ሊሰጡ የሚችሉ ዓይነቶች እንደሆኑ የተናገሩት ሮዛኖ ኤርኮሊን፤ ዕቃዎች ሲመሩ ይህ ታሳቢ ቢደረግ የሚጣል ቆሻሻ መጠን በአግባቡ ሊቀንስ ይችላል ነው የሚሉት።
በጣሊያኗ ጽዱ ከተማ 46 ሺህ የሚሆኑት ኗሪዎቿ በየደጃፋቸው በየቀኑ ውስጡ ምን እንደያዘ በሚያሳይ የቆሻሻ መጣያ ከረጢት የሚጥሉትን በፈርጅ በፈርጁ ለይተው ያስቀምጣሉ። ይህ ስልት ቆሻሻውን ከየቤቱ የሚሰበስቡት ሠራተኞች ሁሉም በአግባቡ መከናወኑን እንዲመለከቱም ዕድል ይሰጣል።
በከተማዋ ከተሰበሰቡት መካከል ዳግም ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉት የሚከማቹባቸው ስድስት መጋዘኖች ይገኛሉ። እዚህ ስፍራ ከሚገኙት የቤት ዕቃዎች መካከልም በቂ ገቢ የሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መረጃ እያቀረቡ በነጻ እንዲወስዱ ይደረጋል። ይህን የሚያከናውነው የማኅበራዊ ፕሮጀክት ሀላፊ አና ሊዛ እንደሚሉት ሌሎች ቆሻሻ ነው ብለው ከሚጥሉት 90 በመቶው ዳግም ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ዕቃ ነው።ምንም እንኳን ድርጊቱ የኤኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለሆነ ወገኖች የእርዳታ ተግባር ቢመስልም ዋና አላማው ግን ብክነትን ቀንሶ የአየር ንብረት ለውጥን የሚያባብሱ ነገሮችን የመቀነሻ መንገድ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ሮዛኖ ኤርኮሊኒ እንደሚሉት የተጣሉ የቤት ዕቃዎችን በማደስ ሂደት ሥራ ላይ የሚውል አዲስ ነገር የለም። ይህ ደግሞ በሂደቱ ሊፈጠር የሚችለውን ብክለት ይቀንሳል። የእሳቸውና የባልደረቦቻቸው ጥረት መቶ በመቶ ከቆሻሻ የጸዳ አካባቢን መፍጠር ነው። ቀጣዩ እቅዳቸው ከብራስልስ የሚያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ በመጠቀም ዳይፐሮችን ለዳግም አገልግሎት ማዘጋጀት ነው። በዚህም የቆሻሻ ክምቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ የሚል ተስፋ አለ። ከዚህ አልፎም ይህ ስልት ወጪን ለመቆጠብም ይረዳል ነው የሚሉት። ሮዛኖ ኤርኮሊኒ፤ እንደተናገሩትም ቆሻሻን ለማስወገድ የካፓኖሪ ከተማ የምትከፍለው ወጪ በመካከለኛው ቱስካና ግዛት ከሚገኙ ማዘጋጃቤቶች ከሚያወጡት የመጨረሻው ዝቅተኛ ወጪ ነው።
አውሮጳ ውስጥ የሚገኙ ከ300 የሚበልጡ ከተሞች ታዲያ የጣሊያኗን ጽዱ ከተማ የካፓኖሪን አርአያ እየተከተሉ ነው። እርግጥ ነው አሁን ካፓኖሪ ቀዳሚዋ ከቆሻሻ የጸዳች ከተማ ሆናለች። የመጨረሻና ብቸኛ ግን አትሆንም፤ በርካታ ከተሞች ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ