ጋዜጠኞችን "ከሕግ እግባብ ውጪ መሰወር በአስቸኳይ ይቁም" የሙያ ማሕበር
ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2017
ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ "ወታደራዊ መለዮ እና የፊት ጭንብል በለበሱ ግለሰቦች" ከመኖሪያ ቤቱ መወሰዱን ያስታወቀው አሠሪው ሪፖርተር ጋዜጣ፤ ግለሰቡን ከመያዛቸው በፊት "ምስል እንዳይቀረጽ በአካባቢው ያሉትን ነዋሪዎች ሞባይል ወስደዋል፣ ስለ ጉዳዩም እንዳይናገሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል" ብሏል።
የጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ባለቤት ጋዜጠኛው እስካሁን የት እንዳለ ማወቅ እንዳልቻሉ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
በአሐዱ ሬዲዮ 94.3 (ኤፍ ኤም) የሚቀርበው "ቅዳሜ ገበያ" የተባለው የሞገድ መርሐ ግብር አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም "ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ተይዞ ተሰውሯል" ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ከአራት ቀናት በኋላ ነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በጸጥታ ኃይሎች ታጅቦ ቢሮው መበርበሩን" ፣ ከዚያ በኋላ ግን የት እንደሚገኝ ማወቅ እንዳልተቻለ መገንዘቡን የማሕበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋዜጠኛ መርሻ ጥሩነህ ለዶቼ ቬለ ገልጿል። የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ ያሽቆለቆለበት ምክንያቱ ምን ይሆን?
"ጋዜጠኞቹ ከተያዙ በኋላ ያሉበት አይታወቅም፤ ቤተሰቦቻቸው፣ የሚዲያ ተቋሞቻቸው፣ ባልደረቦቻቸው አፈላልገዋቸዋል የተገኘ ምንም ፍንጭ የለም።"
የጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ሞሐመድ ባለቤት ወይዘሮ እመቤት ቡታ ዛሬ ሰኞ ለዶቼ ቬለ "እስካሁን ምንም አዲስ መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ" ገልፀዋል። ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ባደረጉት ማጣራት ስሙ እንደሌለ እንደተገለጸላቸው የነገሩን ወይዘሮ እመቤት "በምንም ይጠየቅ በምን መንግሥት ያለበትን ኹኔታ እንዲያሳውቀን" ሲሉ ተማጽነዋል።
ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ የሚሠራበት ሰለንዳ ኤቨንትስ እና ኮሚኒኬሽን "ጉዳዩ ቤተሰቡን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የከተተ" መሆኑን ጠቅሶ "ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት እስካሁን የተጨበጠ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን" አብራርቷል። "ማንም ሰው ከሕግ በላይ መሆን እንደማይችል እንደምንረዳው ሁሉ የአንድ ግለሰብ የሰብአዊ መብቶች ሲጣሱ መመልከት ደግሞ እጅጉን የሚያሳዝነን ነው" ሲል ድርጊቱን ተቃውሟል። እንወያይ፤ የኢትዮጵያ የመናገር ነጻነት ወዴት እያመራ ነው?
በተመሳሳይ የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ በሚኖርበት ሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ መንደር ነሐሴ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ ጭንብል በለበሱ "ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ከቤቱ ተይዞ መወሰዱን ከአካባቢው የጥበቃ አካላት መረዳት መቻሉን የሙያ ማሕበሩ አስታውቋል። "ጋዜጠኞቹ ስለመታሠራቸው ጥቆማ እንደተሠጠን ከቤተሰቦቻቸው፣ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመተባበር አብረን ኹኔታውን ለማጣራትና ለመከታተል ጥረት አድርገናል። ነገር ግን ምንም አይነት ፍንጭ ሳይገኝ ይኼው ሳምንት አልፏቸዋል።"
ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳለው የጋዜጣው ከፍተኛ አዘጋጅ ዮናስ አማረ "ወታደራዊ መለዮ እና የፊት ጭንብል በለበሱ ግለሰቦች" ከመያዙ በፊት የወሰዱት ሰዎች "ምስሎች እንዳይቀረፁ በአካባቢው ያሉትን ነዋሪዎች ሞባይል ወስደዋል፣ ነዋሪዎቹ በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፣ ከዚያ በኋላም ስለ ጉዳዩ እንዳይናገሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።"
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዮናስ በሥሩ እንደሌለ እንደገለፀለትም ጋዜጣው አስታውቋል። በዮናስ ላይ ምንም አይነት መደበኛ ክስ እንዳልተመሠረተና ፍርድ ቤትም እንዳልቀረበ ያስታወቀው ሪፖርተር ጋዜጠኛውን "ለማግኘት የተደረገው ሙከራ እስካሁን አልተሳካም"። ብሏል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ጋዜጠኞች በሥራቸው የሚያስጠይቃቸው ወንጀል ከፈጸሙ በሕግ መጠየቅ አንዳለባቸው ቢያምንም ከሕግ ውጪ "መሰወርና ፍርድ ቤት አለማቅረብ በምንም አግባብ ተቀባይነት የሌለው አደገኛ ልምምድ" መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል። በጉዳዩ ዙሪያ ከፌዴራል ፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "የሕግ የበላይነት ይከበር" ብሏል። ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለማጣራት ያደረግነው ጥረትም ምላሽ አላገኘም። በኢትዮጵያ “በቅርቡ የተገኙ የፕሬስ ነጻነት አብዛኞቹ ውጤቶች ተቀልብሰዋል” ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን
ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ የሰጠው ምክረ ሀሳብ ወደ ጎን ተብሎ በቅርቡ የፀደቀው የሚዲያ ሕግ ላይ ሥጋቱን ገልጾ እንደነበር እና አተገባበሩ ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበው እንደነበር ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ገልፀው ነበር። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ይህ አይነቱ "ሕገ-ወጥ" ያለው የስወራ ድርጊት የሚዲያውን ምኅዳርና ነጻነት በእጅጉ የሚሸረሸር በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መከላከል አለባቸው ብሏል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ