ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ በሚያውቁት ሰዎች አንደበት
እሑድ፣ ጥር 16 2013ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ከእናቱ ከወሮ በላይነሽ ሃብተማርያምና ከአባቱ ከግራዝማች ደስታ አርአያ በአዲስ አበባ ፈረንሣይ ኤምባሲ አካባቢ ተወለደ:: አንጋፋውና ተውዳጁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ እውነተኛና ተአማኒ መረጃ ሲያከማችና ሲያስተላልፍ ኖሯል፡፡ ባሕላዊ ትምህርቱን ለድቁና በሚያበቃወ ደረጃ የተማረው ጌታቸው ደስታ ዘመናዊ ትምሕርቱንም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እና በባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ትምሕርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከዚይም ተመርቆ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኢትዮጵያ ሬዲዮ በወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ በመቀጠር ልለረጂም ዓመታት አገልግሏል፡፡ እዚያ በሥራ ላይ እያለ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድሮ፤ አብላጫ ውጤት በማግኘት ኒውዮርክ በሚገኘው የመንግሥታቱ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ በትጋት ሰርቶ ኮንትራቱ በማለቁ ተመልሶ ወደ ነበረበት የኢትዮጵያ ሬዲዮ መጥቶ በማገልገል ላይ እንዳለ፤ እንደገና የጀርምን ሬዲዮ ዶይቼ ቬለ ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ በአብላጫ ነጥብ በማለፉ ወደ ጀርመን በመሄድ በዶይቼ ቬለ ሬድዮ ለዓመታት ሲሰራ ቆይቶ በራሱ ጥያቄ የጡረታ መብቱ ተጠብቆለት ወደ ሃገሩ ቢመለስም ከኢትዮጵያ ሆኖ በዶይቼ ቬለ ወኪልነት አንዲሰራ ሆኖ ለዓመታት ከሰራ በሁዋላ ተተኪ ሲመደብ የጡረታ ጊዜውን በተለያዩ ቦታዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ይሰራ ነበር፡፡ በግሉ ባጠናው የንብ አናቢነት ችሎታው በትግራይ ላሉ አናቢዎች ዘመናዊውን ስልጠና በመስጠት ለሙያቸው አድገትና ለተሻለ ማር አምራችነት እንዲበቁ አድረጓል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ በዋልድባ ገዳም ለሚገኙት አባቶች በራስ ተነሳሽነት የንብ እርባታን ለማዘመን የሚያበቃቸውን የሙያ ስልጠና በተደጋጋሚ በመስጥት የተሸለ የማር ምርት እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በሁዋላ ከባለቤቱ ከወሮ ብርቱካን የምስራች ሙሉጌታ ጋር ትዳር መስርቶ ለ25 ዓመታት በፍቅርና በመግባባት በመተሳሰብ አብረው ሲኖሩ ባደረበት ሕመም በሃገርና በጀርመን በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥር 6 ቀን 2013 በተወለደ በ86 ዓመቱ ዓምላክ የፈቀደለትን የምድር ኑሮውን ጨርሶ ወደማይሞትበት ዘልዓለማዊ ቤቱ ሄዷል፡፡አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በሚቋቋምበት ጊዜ የድርጅቱ መስራች ክቡር አቶ መኮንን ጠይቀውት ለአባልነት የሚጠየቀውን ክፍያ ሙሉ የወር ደምወዙን በመክፈል መስራች አባል ሆኖ እስክ ህልፈቱ ድረስ በተለያየ የአባልነት ደረጃ እስከ ሊቀመንበርነት አግልግሏል::
ከዚህ ተጨማሪም ጀርመን ሀገር ይኖር በነበረበት ጊዜ በተለይም በኮሎኝ አብያተ ክርስትያናት ውስጥም በማገልገል ለሃይማኖቱ ቀናኢ ተግባራትን በማከናወን ይተጋ እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ላይ በስፋት ተጠቅሷል።
ያለፈው ሐሙስ ዕለት አስክሬኑ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ አርብ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ የሙያ አጋሮቹና አፍናቂዎቹ በተገኙበት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ቤተ ክርስትያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል።
ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ