ጀርመን ጸረ ኮሮና ክትባት እና የነዋሪው አመለካከት
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 22 2013ጀርመን ውስጥ እስከአሁን ድረስ ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች ጸረ ኮሮና ክትባት መከተባቸው ተዘግቧል። እስከ ዛሬ ሐሙስ፤ ታኅሣሥ 22 ቀን፣ 2013 ዓም ድረስ ጀርመን ውስጥ ጸረ ኮሮና ክትባት የወሰዱ ሰዎች ቊጥር 131 626 መሆኑን ሮበርት ኮኽ የተባለው የበሽታ መቆጣጠሪያ ምርምር ተቋም መዝገቡን የጀርመን ዜና አገልግሎት ጠቅሷል። በዛሬው እለት ብቻ 51 465 ሰዎች መከተባቸውን ተቋሙ ዐሳውቋል። ከተከታቢዎቹ መካከል ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የተባሉት እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ የሆኑ 31 250 ሰዎች ይገኙበታል። የኮሮና መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም ቢሆን ግን በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዘው ሰው ቊጥር አልቀነሰም። በእርግጥ ውጤቱ በፍጥነት ላይታ ይችል ይሆናል። ግን በተሐዋሲው የሚያዘው ሰው ቊጥር ያልቀነሰበት ምክንያቱ ምንድን ነው?
እስካሁን ከፍተኛ ቊጥር ያለው ተከታቢ የሚገኘው ባየርን የሚባለው ግዛት ውስጥ ነው። ባየርን ውስጥ 28 206 ሰዎች ተከትበዋል። በመቀጠል ቦን ከተማ የሚገኝበት የኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ ግዛት ነው። እዚያ 19 930 ሰዎች መከተባቸው ተዘግቧል። በሔሰን ግዛትም የተከታቢው ቊጥር 15 674 ነው። ሐምቡርግ 2040፣ ብሬመን 1691 እንዲሁም ቱይሪንገን ግዛት ውስጥ 810 ሰዎች እያለ ይቀጥላል። የተከታቢዎች ቊጥር በተለይ ባየርን እና ኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ ውስጥ ለምን ከፍ አለ? አንዳንድ የአገልግሎት መስጫ አካላት እና የመጓጓዣ ዘርፎች በተለይ አየር መንገዶች ያልተከተበ ሰው አገልግሎት አያገኝም ሲሉ ይሰማል። ይኼ ምን ማለት ነው?
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ይልማ ኃይለ ሚካኤል