ጀርመን የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ድንበርዋን ዘጋች
ሰኞ፣ መጋቢት 7 2012ማስታወቂያ
የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን በመስጋት ጀርመን የሚያዋስንዋትን የአምስት ሃገር ድንበሮች ዘጋች። ስዊዘርላን፤ ፈረንሳይ፤ ኦስትርያ ዴንማርክ እና ሉክሰንበርግ በተሽከርካሪ ለሚገቡ መንገደኞች ጀርመን ድንበርዋ ላይ ቁጥጥር የምታደርግባቸዉ ሃገራት ናቸዉ። ይሁንና የምግብ እና አስፈላጊ የተባሉ ሸቀጣ ሸቀጦች የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በልዩ ፈቃድ ወደ ሃገሪቱ የመግባት ፈቃድን አግኝተዋል። በጀርመን ትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ ተቋማት ወደ አምስት ሳምንት ተዘግተዋል። ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች፤ ቤተ እምነቶች ማለትም መስጊድ ቤተ ክርስትያን እንዲሁም ሙክራቦች ሁሉ ዝግ ሆነዋል። በጀርመን ባቫርያ ግዛት በበኩሉ «የአደጋ ጊዜ» ሲል በግዛቱ ምንም አይነት ስብሰባዎች ፤ ሕዝባዊ ድግሶች ፤ አይካሄዱም ሲል ቀደም ሲል አዉጆ ነበር።የጀርመን መንግሥት በአሁንዋ ሰዓት በሃገሪቱ ዉስጥ የሚገኙትን ሱቆች ሁሉ ለመዝጋት እየመከረ ነዉም ተብሎአል። በወጡት መረጃዎች መሰረት የምግብ እና መድሃኒት መሸጫ ሱቆች አቀልግሎት ይሰጣሉ። ምግብ ቤቶች ቡና ሆቴሎች እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ብቻ ክፍት ይሆናሉ። በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት የተዘጉ የተለያዩ ድርጅቶች የሚደርስባቸዉን ኪሳራ ለማካካስ የጀርመን መንግሥት 500 ቢሊዮን ይሮ መመደቡ ይታዉቃል።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ