ጀርመን የእስራኤል 60ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት
ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017ጀርመንና እስራኤል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 60ኛ ዓመት ዛሬ በርሊን ላይ በተለያዩ ዝግጅቶች እያሰቡ ነዉ። በርሊን በሚካሄደዉ ሥነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት አይዛክ ኸርዞግ ዛሬ ሰኞ በርሊን ገብተዋል። ከጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጋር በመሆን በግሩነዋልድ ባቡር ጣቢያ የሆሎኮስት መታሰቢያ 'የባቡር መስመር 17' ን ይጎበኛሉ። በናዚዉ የናሽናልሶሻሊስት ዘመን 10,000 አይሁዳውያን ሴቶችና ወንዶች ከዚህ ወደ ማጎርያ ስፍራ ተባረዉ ነበር። የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እስራኤል ላይ በሚካሄደዉ የሁለቱ ሃገራት የዲፕሎማስያዊ ግንኙነት 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ነገ ማክሰኞ ከእስራኤሉ አቻቸዉ ጋር ወደ እስራኤል ያቀናሉ። ጀርመን እና እስራኤል በጎርጎረሳዉያኑ ግንቦት 12 ቀን 1965 ዓም ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት ሲጀምሩ የጀርመኙ መራሔ መንግሥት የነበሩት ሉድቪግ ኤርሃርድ እና የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሌዊ ኤሽኮል በፊርማቸዉ ያረጋገጡ የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት ነበሩ። ይህ ከመሆኑ በፊት ናዚ ጀርመን ወደ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ አይሁዳውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደሉ ምክንያት በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት እና መሻከር ነበር። ጀርመን እና እስራኤል ዲፕሎማስያዉዊ ግንኙነት ከጀመሩ ከ 60 ዓመታት ወዲህ ግን ሁለቱ ሃገራት የጠበቀ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ሳይንሳዊና ባህላዊ ትስስር እስከ ዘልቀዋል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ