የአስትራ ዜኒካ ውዝግብ
ረቡዕ፣ መጋቢት 22 2013የጀርመን መንግሥት አስትራ ዜኒካ የተባለዉ ኩባንያ የሚያመርተው የኮሮና መከላከያ ክትባት ዕድሜያቸዉ ከ60 ዓመት በታች ለሆነ ዜጎቹ እንዳይሰጥ መከልከሉ ድጋፍም፣ ስጋትም አስከትሏል። የጀርመን የፌደራልና የክፍለ ሐገራት የጤና ሚንስትሮች ትናንት ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት የአስትራ ዜኒካ ክትባት ልዩ የሐኪም ውሳኔ ካልታከለበት በስተቀር ዕድሜያቸዉ ከ60 ዓመት በታች ለሆነ ሰዎች አይሰጥም። የጤና ሚንስትሮቹ ከዚሕ ውሳኔ ላይ የደረሱት የአስትራ ዜኒካ ክትባት ከተሰጣቸዉ ሰዎች በ31ዱ ላይ አንጎላቸው ውስጥ የደም መርጋት ሕመም በማስከተሉ ነው። የጤና ሚንስትር የንስ ሽፓን ትናንት ከመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር ሆነው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከ31ዱ ሰዎች ዘጠኙ ሞተዋል።
«በሌላ በኩል ይሕን ወረርሺኝ ለመከላካል ካሉን ክትባቶች አንዱ በተወሰነ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ላደጋ ማጋለጡ እቅፋት መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። እስከ ትናንት ድረስ የአስትራዜኒካን የኮቪድ 19ኝ ክትባት ከተወጉ 31 ሰዎች ታመዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ዘጠኙ ሞተዋል። ለሕመም የተጋለጡት ሁሉም በሚባል ደረጃ ዕድሜያቸው 60 ዓመት በታች የሆነ ሴቶችና ጥቂት ወንዶች ናቸው።»
ጀርመን ዉስጥ የአስትራ ዜኒካ ክትባት ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች ለሆኑ ዜጎች እንዳይሰጥ መታገዱ የክትባቱን ሒደትና ፍጥነት ያጉለዋል የሚል ስጋት አሳድሯል። የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ጀርመን ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኘውን የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገዉን ጥረት ማዘግየቱም አይቀርም።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ