ጀርመን ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ በፍጥነት መዛመት ጀመረ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 2 2013ጀርመን ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ በከፍተኛ ኹኔታ መሠራጨት መጀመሩ ተገለጠ። ባለፉት በ24 ሰዓታት ብቻ 30 ሺህ ሰዎች ገደማ በኮቪድ 19 መያዛቸውን እንዲሁም 598 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንም ሮበርት ኮኽ የተባለው የበሽታ መቆጣጠሪያ ምርምር ተቋም አስታውቋል። ኮቪድ 19 በወረርሽኝነት ከተከሰተ ወዲህ ጀርመን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ሲመዘገብ የመጀመሪያ መሆኑን ነው ተቋሙ ያመለከተው። በዚህ አያያዝ እስከ የፈረንጆች ገና ድረስ በዚህ መልኩ መቆየት እንደማይቻል በማመልከትም በአፋጣኝ ጠንከር ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊደረግ እንደሚገባ ተመራማሪዎች አሳስበዋል። የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሆርስት ዜሆፈርም በተመሳሳይ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ ገደቡ ባፋጣኝ መደረግ አለበት ሲሉ ለጀርመኑ ደር ሽፒግል መጽሔት በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል። የወረርሽኞች ባለሞያና ቤርሊን የሚገኘው ሻርሊ የተባለው የሕዝብ ጤና ተቋም ኃላፊ ዶክተር ቶቢያስ ኩርዝ ለዶይቸ ቤለ እንደተናገሩት የኮሮና ተሐዋሲ መዛመቱ «አሳሳቢ» ደረጃ ላይ ደርሷል። ምናልባትም ጠንከር ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል እንደሚችልም ተናግረዋል። ዓርብ ታኅሣሥ 2 ቀን 2013 ዓም ከሰአት በፊት የጀርመን ግዛቶች ጠቅላይ ሚሥትሮች በኮሮና ተሐዋሲ በፍጥነት መሠራጨትን አስመልክቶ ለመምከር ተሰባስበው ነበር። የሚንስትሮቹ ስብሰባ እና በጀርመን ሊወሰድ ይችላል ተብሎ ስለሚገመተው ርምጃ እንዲገልጥልን ከቤርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ አድርገናል። ሙሉውን ቃለ መጠይቅ ከድምጽ ማጫወቻው ላይ ማድመጥ ይቻላል።
ይልማ ኃይለ ሚካኤል/ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ