ጀርመን ተገን ጠያቂዎችን ከድንበር መለሰች
እሑድ፣ ግንቦት 3 2017መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርስ የሚመሩት አዲሱ መንግስት ስልጣን በተረከበ በሁለት ቀናት ውስጥ ጀርመን የምትዋሰንባቸው ድንበሮች ቁጥጥር ሲያጠናክር በዚሁ የተገን ጥያቄ ያቀረቡ 19 ስደተኞች ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ቢልድ አም ዞንታግ የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል።
ባለፉት የሀሙስ እና ዓርብ ቀናት ብቻ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች ወደ ጀርመን ለመግባት ከሞከሩ 365 ሰነድ አልባ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች መካከል 19 ተገን ጠያቂዎችን ጨምሮ 305 ስደተኞች ጀርመን እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
የተገን ጥያቄ ካቀረቡ ስደተኞች ውስጥ “ለጥቃት የተጋለጡ” ናቸው የተባሉ አራት ሰዎች ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል።
የተገን ጠያቂዎች እና የስደተኞች ጥያቄ ውድቅ ለመደረጉ ህገ ወጥ ቪዛ እና የተጭበረበሩ የጉዞ ሰነዶች ይዘው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።
ጀርመን በሁለቱ ቀናት ጥብቅ የድንበር ቁጥጥሯ ተመላሽ ከተደረጉ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች በተጨማሪ 14 ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር አውላለች። በተጨማሪ በሌሎች 48 ሰዎች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱን ያመለከተው ዘገባው የግራ ቀኝ እና የቀን አክራሪ አስተሳሰቦችን ጨምሮ አክራሪ የእስልምና አስተምሮ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ዘጠኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘገባው አመልክቷል።