ጀርመን ለኢትዮጵያ የሰብአዊ አቅርቦት ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓ
ረቡዕ፣ የካቲት 19 2017በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተጠሪ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ጀርመን የምታደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ከየትኛውም ቅድመ ኹኔታ የነጻ መሆኑን በአድናቆት ጠቅሰዋል።
«ጀርመን ለኢትዮጵያ ታማኝ የሰብአዊነት አጋር ናት» - በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሃነፌልድ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶ/ር ራሚዝ አላክባሮቭ እንዲሁም በድርጅቱ ሥር ካሉ ተቋማት መሪዎች ጋር ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 አዲስ አበባ ውስጥ በሰጠት መግለጫ፣ ጀርመን የተባበሩት መንግሥታት በሦስት ተቋማቱ አማካኝነት በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በጎርጎሪዮሳዊው 2025 ዓ,ም ለሚያከናውናቸው የሰብአዊ ተግባራት የሚሆን የ50 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓ ይፋ ተደርጓል።
ይህ የገንዘብ ድጋፍ በሚቀጥሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ ምላሽ ጥረት ያጠናክራል፤ ተጋላጭ በሆኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ያለውን አሳሳቢ ችግር ለመፍታትም ያስችላል ተብሏል። የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎች የተፈጥሮ አደጋዎች ያደረሷቸውን መጎሳቆሎች እና በግጭት ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያስፈልጉ የረድኤት ተግባራትን ለማዳረስ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሃነፌልድ ሀገራቸው ጀርመን ለኢትዮጵያ ታማኝ የሰብአዊነት አጋር መሆኗን እና ይህንንም እንደምታስቀጥለው በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።
«የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማገዝ አሁንም ቁርጠኛ ነው። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ቁርጠኝነት ማለት አስተማማኝነት ማለት ነው። ባለፈው ዓመት ጀርመን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ብቻ ከ44 ሚሊየን ዩሮ በላይ ሰብአዊ እርዳታ የሰጠች ሲሆን፥ አብዛኛው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ እና በመጪዎቹ ወራት ተግባራዊ የሚደረግ ነው። ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የተቀናጀ የስደተኞች ምላሽ 4.1 ሚሊዮን ዩሮ አግኝቷል። የሕፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ለሕፃናት ጥበቃ በተለይም ለፆታዊ ጥቃቶች ምላሽ 3.8 ሚሊዮን ዩሮ ተሰጥቶታል።
የተባበሩት መንግሥታት ሴቶችም እኩልነትን እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመፍታት የፕሮጀክቱን አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል። እነዚህ ሦስት ተቋማት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሀገር አቋራጭ ድጋፍ የሚውሉ የ50 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል። ይህ የገንዘብ ድጋፍ በሚቀጥሉት ዓመታት በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሰብአዊ ምላሽም ይደግፋል።»
ጀርመን ያደረገችው የገንዘብ ድጋፍ ከቅድመ ኹኔታዎች ነፃ ነው
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተጠሪ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ራሚዝ አላክባሮቭ በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚገኙት የተለያየ ዘርፍ ላይ የሚሠሩት ተቋማት ይህንን የጀርመንን የገንዘብ ድጋፍ ለሰብአዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ የልማት ሥራዎችም ያውሉታል ብለዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀነሰ ባለበት በዚህ ጊዜ ጀርመን ይህንን ድጋፍማድረጓንም አመስግነዋል። ሀብቱ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ዘርፎች፣ በጾታ ጥበቃ እና መሰል ሥራዎች ላይ ፈሰስ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
«በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን፣ ዩኒሴፍ እና UN ሴቶች ሕይወት አድን ርዳታን ለማድረስ እና ለተጎዱ ማኅበረሰቦች የመቋቋም አቅምን በማሳደግ ይደገፋሉ። በተለይም UNHCR ለስደተኞችን እና ለተፈናቃይ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አስተናጋጅ ማኅበረሰቦች ጥበቃ፣ የጤና እንክብካቤ፣ መጠለያ፣ ንጹሕ ውኃ እና የትምህርት ድጋፍ ይሰጣል። የጀርመን አስተዋፅዖ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከብሔራዊ አገልግሎት ጋር እንዲዋሃዱ በማድረግ የረጅም ጊዜ ለውጥ እንዲፈጠር ያደርጋል።»
የተባበሩት መንግሥታት፣ የጀርመን ሕዝብ እና መንግሥት የኢትዮጵያን ሰብአዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ድጋፍ በጥልቅ ያደንቃል ያሉት ኃላፊው ይህ አጋርነት የዓለም አቀፍ አብሮነት ኃይልን እና እና ዘላቂ መፍትሔ ለሚያሻቸው እጅግ ለተቸገሩ ሰዎች ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ ገልፀዋል። አክለውም ጀርመን የምታደርገው ድጋፍ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ መሆኑን አውስተዋል።
«የጀርመን የገንዘብ ድጋፍ በትክክል እንዲህ ተብሎ ለተወሰነ ዓላማ ወይም በቅድመ ኹኔታ የቀረበ ነው። ይህ ማለት በቅድመ ኹኔታ የቀረበ አለመሆኑን በታላቅ ደስታ መቀበል አለብኝ። ቅድመ ሁኔታ የለውም፣ ከድጋፉ ጋር የተያያዙ ልዩ ሁኔታዎችን አያካትትም። እንዲሁም የረዥም ጊዜ ዘላቂ የአቅርቦት እና በራስ ያለመቆም ችግሮችን የሚፈታ ነው።»
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሃነፌልድ ከጀርመን ግብር ከፋዮች የሚመጣ ነው ያሉት ይህ የገንዘብ ድጋፍ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ እናረጋግጣለን ብለዋል። አሜሪካ ታደርግ የነበረውን ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ ትቀጥላለች የሚል ተስፋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ስለመኖሩም በዚሁ ወቅት ተገልጿል። ዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ በጊዜያዊነት በማቋረጧ የተከሰተ አደጋ ስለመኖር አለመኖሩ እና ተፅዕኖው ምን እንደሆነ እየተገመገመ መሆኑንም የተቋሙ የኢትዮጵያ ተጠሪ ገልፀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር