ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጸሙ
ሰኞ፣ ጥር 12 2017ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጸሙ
መዲና ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደዉ ቃለ መሃላ ሥነ-ስርዓት ላይ፤ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፣የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ጃቪየር ሚሌይ ፣የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል። ከአፍሪቃ ተጋባዥ እንግዶች ስለመኖር አለመኖራቸዉ እንስካሁን ይፋ የወጣ ዘገባ የለም።
ትራምፕ ሰኞ ዕለት ከኃይል እስከ ኢሚግሬሽን ባሉ ጉዳዮች ላይ ብዙ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛሬ ቃለመሃላ ከመፈፀማቸዉ በፊት እንደተናገሩት ከኃይል አቅርቦት እስከ ህገ ወጥ ስደተኞችን ከአገሪቱ የሚያባርር ህጎችድረስ እንደሚፈርሙ ተናግረዋል።
የተመሠረቱባቸውን ክሶችና ውልጀላዎችን አልፈው፤ ከተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎችም ተርፈው በድጋሚ ወደኋይት ሃውስ የገቡት ትራምፕ፤ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ለዜጎች አንድነት ለአሜሪካ ዳግም ልዕለ ሃያልነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በዋሽንግተን እና በአካባቢዋ በተከሰተዉ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት ሥነ-ስርዓቱ እንደተለመደዉ አደባባይ ላይ አልተከናወነም። ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ 20 ሺህ ገደማ ታዳሚዎች በቃለ መሃላዉ ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዋል። ትራምፕ ወደቃለመሐላ ሥርዓቱ ከመሄዳቸው አስቀድሞ በቤተክርስቲያን ተገኝተው የጸሎት ሥርዓት ተካፍለዋል።የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ደብሊው ጆርጅ ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ እንዲሁም የቀድሞ ዴሞክራት እጩ ሄላሪ ክሊንተን በበዓለ ሲመቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
የጀርመን መራሂተ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ከትራምፕ ቃለ-መሃላ ከመፈፀማቸዉ በፊት ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ግንኙነት «ጠቃሚ» ሲሉ ተናግረዋል። የራሺያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ለ 47 ኛዉን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የእንኳን ደስ ያሎት መልክት ልከዋል። ፑቲን ለዉይይት በራቸዉ ክፍት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቃለመሃላዉ ከመካሄዱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት፤ የዋሽንግተኑን ወኪላችንን አበበፈለቀን ስለ ስነስርዓቱ በቀጥታ ስርጭት በስልክ አነጋግረነዋል። ያድምጡ!
አበበ ፈለቀ / አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ