ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠዉን ወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጧ
ማክሰኞ፣ የካቲት 25 2017ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ ማቋረጧን አስታወቀች፤ ዩክሬን ርምጃው አደገኛ መዘዝ እንደሚኖረው ገልጻለች።የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ ከካናዳ እና ሜክሲኮ ወደ አገሪቱ በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለው ቀረጥ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ዛሬ በአገሪቱ ኮንግረስ የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የተካረረው የአሜሪካና የዩክሬን ግንኙነት
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከተመለሱ በኋላ፣ዩናይትድስቴትስ ከዩክሬን ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መሄዱ ታይቷል።በሁለት አገራት መሪዎች መኻከል፣ ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በቃላት ጦርነት የታጀበና ኀይለ ቃል የተሞላበት የጋራ ጋዜጠኛ መግለጫ መካኼዱ፣የተበላሸውን ግንኙነት ዐደባባይ ላይ አውጥቶታል።
ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት፣በዩክሬንና ሩሲያ መኻከል የሚካሄደውን ጦርነት በፍጥነት ማስቆም እንደሚፈልጉ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ሙሉ ትኩረታቸው በሰላም ጉዳይ ላይ መሆኑን አንድ የኃይት ሐውስ ባለስልጣን ተናግረዋል።በመሆኑም ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ ርዳታ በማቆም ለሰላም የሚኖረውን ዕድል ማየት እንደሚገባ አመልክተዋል ባለሥልጣኑ።
"አደገኛ ሁኔታ"
ከአሜሪካ ታገኝ የነበረው ማንኛውም ድጋፍ የተቋረጠባት ዩክሬን ግን፣ዕርምጃውን አደገኛ ብላዋለች።ኦሊሻንድ ሜሪዚኮ በዩክሬን ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ናቸው።"በቅርቡ ከባድ መዘዞችን እናያለን፤ አደገኛ ውጤቶች።"
እኚሁ እንደራሴ፣የአሜሪካ ርምጃ ከአሜሪካ መወገንም ይመስላል ብለዋል።ሩሲያ የአሜሪካን ርምጃ በማውደስ፣ ይህ ለሰላም መስፈን የተሻለው አስተዋጽኦ እንደሚችል አስታውቃለች።በዚህ ሁሉ መኻል፣ ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር ያላትን ትብብር ለመቀጠል እንደምትፈልግ የገለጸች ሲሆን፣ኪዬቭ ወደ ድርድር እንድትመለስ በሩ ክፍት መሆኑን ደግሞ የዩናይትድስቴትስ ምክትል ፕሬዘዳንት ጄዲ ቫንስ ቀደም ሲል መግለጻቸው ይታወቃል።
በካናዳና ሜክሲኮ ላይ ገቢራዊ የሆነው ቀረጥ
በሌላ በኩል፤ የትራምፕ አስተዳደር ከካናዳ እና ሜክሲኮ በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለው የ25 በመቶ ቀረጥ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል። በዚህ ጉዳይ ከአሁን በኋላ ከሁለቱ አገራት ጋር ምንም ዐየነት ድርድር እንደማይኖር ትናንት ለጋዜጠኞች የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣አገራቱ ታሪፉን ለማስቀረት ያላቸው አማራጭ ምን እንደሆነ ጠቁመዋል።"ቀረጥ ሊጣልባቸው ይገባል፤ ስለዚህ ማድረግ የሚጠበቅባቸው የመኪናም ሆነ ሌሎች ማምረቻ ተቋሞቻቸውን አሜሪካ ውስጥ መገንባት ነው።ይህ ከሆነ ምንም ዐይነት ቀረጥ አይኖርባቸውም።"
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ከካናዳና ሜክሲኮ በሚመጡ ምርቶች ላይ የተጣለው ቀረጥ፣ አሜሪካውያን በየቀኑ በሚጠቀሙባቸው፣ እንደ ጋዝ፣ ስጋ እና ሌሎች የችርቻሮ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።ካናዳ በምላሹ፣ ከአሜሪካ በሚገቡ የቤት ዕቃዎች፣ ወይን፣ ቢራና በመሳሰሉ ምርቶች ላይ 25 በመቶ ቀረጥ የጣለች ሲሆን፣ የሜክሲኮ የአጸፋ ርምጃ ምን እንደሚሆን ዛሬ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካን ርምጃ ተከትሎ፣በመላው ዓለም የአክሲዮን ገበያዎች መውደቁ ተዘግቧል።የአውሮፓ ህብረት በካናዳና ሜክሲኮ ላይ የተጣሉት ቀረጦች፣ ለኢኮኖሚ መረጋጋት ስጋት መሆናቸውን አስጠንቅቋል።
ትራምፕ ለኮንግረስ የሚያደርጉት ንግግር
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፣ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዛሬ ምሽት ለሁለተኛ ጊዜ ስልጣን ከያዙ በኋላ በሀገሪቱ ኮንግረስ የጋራ ስብሰባ ላይ የመጀመሪያውን ንግግር ያደርጋሉ።
በዚሁ ንግግራቸው፣ለዓመቱ ቅድሚያ በሚሰጡባቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር እንደሚናገሩ ይጠበቃል።ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣"ትሩዝ ሶሻል"በተባለው የማኀበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ምሽቱ ትልቅ ይሆናል ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ