የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የአምስት የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት አምሥት የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት መሪዎችን ዋይት ሐዉስ ዉስጥ አነጋግረዋል።ትራምፕ አምሥቱን መሪዎች «ለዉይይት» የጋበዙት ዩናይትድ ስቴትስ ለአዳጊ ሐገራት የምትሰጠዉን ርዳታ መስተዳድራቸዉ በእጅጉ በቀነሰበትና የብዙ የአፍሪቃ ሐገራት ዜጎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ባገደበት ወቅት መሆኑ ነዉ።ይሁንና ዋይት ሐዉስ እንዳስታወቀዉ የትራምፕና የአምሥቱ የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ዉይይት ያተኮረዉ በርዳታ ላይ ሳይሆን በምጣኔ ሐብት ግንኙነት ላይ ነዉ።አንቶኒዮ ካስካይስና ጃኔላ ዱማላኦን የዘገቡትን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
የዶቸ ቬለዋ ዘጋቢ ጃኔላ ዱማላኦን «surprise» ብላዋለች-ጉባኤዉን ።አስደናቂ ወይም ያልተጠበቀ ብንለዉ ያስኬዳል።-የማስደነቁ ሰበብ ሁለት ነዉ።ሥለጉባኤዉ ምንም ወይም ትንሽ ተነግሮ መደረጉ-አንድ።የትራምፕ መስተዳድር ሐገራቸዉ የአፍሪቃን ለመሰሉ ደሐ ሐገራት የምትሰጠዉን ርዳታ በእጅጉ በቀነሰበትና የብዙ የአፍሪቃ ሐገራት ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ ባገደበት ወቅት መሆኑ-ሁለት።
ባንድ-ወይም በሁለቱም ምክንያቶች ባልተጠበቀዉ ጉባኤ የተካፈሉት የጋቦን፣ የጊኒ-ቢሳዉ፣ የላይቤሪያ፣ የሞሮታኒያና የሴኔጋል መሪዎች ናቸዉ።የትራምፕ መስተዳድር የብዙ የአፍሪቃ ሐገራት ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ አግዷል።ዩናይትድ ስቴትስ በUSAID በኩል የምትሰጠዉ ርዳታ በመቋረጡም ሁሉም ሐገራት ተጎድተዋል
USAID የተዘጋዉ ብክነትን ለማስወገድ ነዉ-ትራምፕ
ፕሬዝደንት ትራምፕ ለእንግዶቻቸዉ እንደነገሩት ግን መስተዳድራቸዉ USAIDን የዘጋዉ ብክነትን ለማስቀረት ነዉ።
«የUSAIDን የዘጋነዉ ብክነትን፣ ማጭበርበርና አላግባብ መጠቀምን ለማጥፋት ነዉ።ብዙ ብክነት፣ማጭበርበርና አላግባብ መጠቀም ነበር።ዩናይትድ ስቴትስም አፍሪቃም የሚጠቀሙበት አዲስ የምጣኔ ሐብት ዕድል ለመፍጠር አበ,ክረን እየጣርን ነዉ።ሌላ አካባቢ በጥቂቱ የሚገኘዉ የምጣኔ ሐብት ቅምጥ-ዕድል አፍሪቃ ዉስጥ በብዙ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ አለ።»
ዋይት ሐዉስ ከጉብኝቱ በፊት ባወጣዉ መግለጫም የጉባኤዉ ዓላማ ርዳታ ሳይሆን የንግድና የኤኮኖሚ ግንኙነትን «ማጠናከር ነዉ» ብሏል።በርግጥም የጋቦን ከርሠ-ምድር ነዳጅ ፣ዩራኒዮም፣ብረት፣ ወርቅ፣ሬር ኧርዝና ሌላም ማዕድን ታቅፏል።ጊኒ ቢሳዉ፣ ፎስፌት፣ ነዳጅ፣ጋዝና ወርቅ አላት።ላይቤሪያ ወርቅ፣አልማዝና ማንጋኔዝl፤ሞሪታንያ፣ ብረት፣ወርቅ፣መዳብ፣ነዳጅ፣ ጋዝ፣ ሴኔጋል ብረት፣ሬር ኧርዝ፣ ነዳጅም ጋዝም፣ ሌላም ማዕድናት አሏቸዉ።
የአምሥቱ ሐገራት የማዕድን ሐብት የአሜሪካዉን ቱጃር ፖለቲከኛ ይሁን የድፍን አሜሪካ፣ የአዉሮጳ ወይም የእስያን ሐብት አጋባሾች ቅልብ ቢያማልል በርግጥ አይገርምም።
ከትልልቆቹ ሐገራት መሪዎች ይልቅ የትንንሾቹ ተጋበዙ
የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ፕሮፌሰር ሱሌይማን በሽር ዲያግኔ እንደሚሉት በመጀመሪያዉ የትራምፕ ዘመነ-ሥልጣን ሥለ አፍሪቃ ይነገር-ይደረግ የነበረዉ መጥፎ-መጥፎ ነገር አዉን ተቀይሯል።ይሁንና ትራምፕ ሐገራቸዉ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ካሰቡ በተፈጥሮ ሐብትም፣ በሕዝብ ብዛትም፣ በፖለቲካም የጠነከሩትን የአፍሪቃ መሪዎችን ለምን አልጋበዙም-ይጠይቃሉ ፕሬፌሰሩ።
«ይሁንና አስገራሚ ነገሮች አሉ።የአፍሪቃ አሐጉር ሥምምነት ልታደርግባት የምትችል አሐጉር መሆንዋ፣ አፍሪቃ አሁንም ሆነ ጠቃሚ ለመሆንዋ ዕዉቅና የመስጠት አብነት ነዉ።ይሁንና እኔ የተለመዱ ተጠርጣሪዎች የምላቸዉ እንደ ደቡብ አፍሪቃ ወይም ናጄሪያ ያሉ ጠንካራ ምጣኔ ሐብት ያላቸዉ ሐገራት መሪዎች አልተጋበዙም።እነሱ ቀርተዉ የተጋበዙት እነዚሕ አምስት ሐገራት ናቸዉ።»
የስደተኞችና የአደንዛዥ ዕፅ ጉዳይ
የሞሪታንያዉ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች አማካሪ ዘካሪያ ኡልድ አማር ግን ትራምፕ የአምስቱን ሐገራት መሪዎች የመጋበዛቸዉ ዓላማ ንግድ፣ ምጣኔ ሐብት፣ ምዕድን ብቻ አይደለም።የስደተኞችና የአደንዛዥ ዕፅ ዝዉዉርን መቆጣጠርም ከዋና ዓላማቸዉ አንዱ ነዉ።
«ዶናልድድ ትራምፕ ከልብ የፈለጉት የስደተኞችና የአደንዛዥ ዕፅ መሸጋገሪያ መንገዶችን መዝጋት ነዉ።እነዚሕ አምስት ሐገራት ለበርካታ ዓመታት ስደተኞች ሚሸጋገሩባቸዉ መስመሮች የሚያልፉባቸዉ ናቸዉ።በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሜክሲኮ ድንበር በኩል አሜሪካ የሚገቡት እነዚሕ ሐገራትን አቋርጠዉ ነዉ።አካባቢዉ የዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕፅ መዘዋወሪያም ነዉ።»
የጊኒ ቢሳዉ ተወላጅና የአሜሪካ ጉዳይ አጥኚ ዊሊያም ፌሬይራ እንደሚሉት ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተነጋገሩት አምስቱም መሪዎች በየሐገራቸዉ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊ፣ ሕጋዊ ጥፋቶች ወይም ሰቶች አድርሰዋል ተብለዉ የሚወቀሱ ናቸዉ።
የጊኒ ቢሳዉ ፕሬዝደንት ሥልጣን ማስረከብ የነበረባቸዉ ባለፈዉ የካቲት ነበር።የጋቦን ፕሬዝደንት በሙስናና መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ ይወቀሳሉ።የላይቤሪያዉ መሪ የሐገሪቱን ማሕበራዊ ቀዉስ አባብሰዋል ይባባላሉ።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ ሞሪታንያን የሚመሩት የቀድሞዉ ጄኔራል የሐገሪቱን ፖለቲካዊ ቀዉስ አልፈተም ተብለዉ ይተቻሉ።የሴኔጋሉ መሪ ሥልጣን በያዙበት ወቅት ብዙ ተደንቀዉ ነበር።አሁን ግን በአቀፍ የስደተኞች ዝዉዉር ተሳትፋዋል ይባላሉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን ላንዱም ጥፋት ደንታ ያላቸዉ አይመስሉም።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ