የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጉብኝት፣ የአረቦች ደስታና የአሜሪካ-አረቦች ሥምምነት
ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2017የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት ጀምሮ በሪያድ-ሳዑዲ አረቢያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቅቀዉ ዛሬ ቀጠር ገብተዋል።ትራምፕ የመሩት የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከሳዑዲ አረቢያ አቻዎቹ ጋር የንግድና የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ተፈራርሟል።ትራምፕ እዚያዉ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ከስድስቱ የባሕረ ሠላጤዉ የትብብር ምክር ቤት አባል ሐገራት መሪዎችና ከሶሪያ ጊዚያዊ መሪ አሕመድ አል ሻራዕ ጋር ተወያይተዋል።ዩናይትድ ስቴትስ በሶሪያ ላይ ጥላዉ የነበረዉን ማዕቀብ አንስተዋልም።ነጋሽ መሐመድ ሥለ ትራምፕ ጉብኝት አጭር ዘገባ አጠናቅሯል።
ደማስቆና አሌፖዎች ተደሰቱ፣ ጨፈሩም
ደማስቆ። ሰፊ፣ ትልቅ፣ ማራኪዉ የዑማያድ አደባባይ በሕዝብ ተሞልቶ ሲጨፈር፣ሲቦረቅ፣ ሲዘፈንበት አድሮ አነጋ።ያ ሰፊ አደባባይ፣ ከ661 እስከ 750 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከቀይ ባሕር ግርጌ-አፍሪቃ እስከ ስጳኝ፣ ከመካ እስከ ቡርግዱ-ፈረንሳይ የሚደርሰዉን ሠፊ ክፍለ-አሑጉር በገዛዉ በሙስሊሞቹ ጠንካራ ሥር-ወመንግሥት ሥም ዑመያድ ተብሎ የመሰየሙ መላ፣ የአረብ-ሙስሊሞችን ታላቅ ገድል-ድል ለመዘከር ነበር።ከትናንት ማታ እስከ ዛሬ ማርፈጃዉ ደማስቆዎችን ያስጨፈረዉ ግን የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ሪያድ-ሳዑዲ አረቢያ ላይ ያወጁት ዉሳኔ ነዉ።
«ከአዲሱ የሶሪያ መንግስት ጋር ግንኙነታችንን ወደነበረበት ለመመለስ እየጣርን ነዉ።(ግንኙነቱ) ከፕሬዝደንት አሕመድ አል ሻራዕ ጋር ባደረጉት ዉይይት፣ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሩቢዮ ቱርክ ዉስጥ ከሶሪያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጋር ባደረጉት ግንኙነት ተጀምሯል።ሥለሁኔታዉ ከአልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ጋር (በገፅ)፣ ከቱርክ ፕሬዝደንት ኤርዶኻን ጋር (በሥልክ) ከተነጋገርኩ በኋላ ሶሪያዎች እንዳዲስ እንዲጀምሩ በሶሪያ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ እንዲነሳ ወስኛለሁ።»
የሶሪያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ አሌፖም ቦረቀች።የዩናይትድ ስቴትስና የሶሪያ መሪዎች ፊትለፊት ተገናኝተዉ ሲነጋገሩ ከ25 ዓመታት ወዲሕ የትራምፕና የአል ሻራዕ የመጀመሪያዉ ነዉ።ትራምፕ ፖለቲካ-ዲፕሎማሲን ከንግድ-ምጣኔ ሐብት በቀየጠዉ ጉብኝታቸዉ ለሳዑዲ አረቢያ የ142 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ተስማምተዋል።
ንግድ፣ ጦር መሳሪያና ሙዓለ ነዋይ
ሳዑዲ አረቢያ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ 600ቢሊዮን ዶላር ሥራ ላይ እንድታዉል የሪያድ ገዢዎችን አግባብተዋል።የአዉሮጳ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ጥናት ተቋም አጥኚ ኤሚሊ ታሲናቶ እንደሚሉት ትራምፕ የጠየቁት ከ,ዚያ በላይ ነበር።
«ሳዑዲ አረቢያ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ለንግድና ለሙዓለ ንዋይ ፍሰት 600 ቢሊዮን ዶላር መድባለች።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጠየቁት ግን ሳዑዲ አረቢያ 1 ትሪሊዮን ዶላር እንድትመድብ ነበር።»
ቀጠርም ከዩናይትድ ስቴትሱ ግዙፍ ኩባንያ ቦይንግ 200 አዉሮፕላኖች ለመግዛት አቅዳለች።ከግዢ-ሸመታዉም ሌላ ትንሺቱ ደሴት «የሰማይ ላይ ቤተ-መንግስት» የተባለዉን ልዩ አዉሮፕላን ለትራም ሸልማለች።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም የጦር መሳሪያን ጨምሮ ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአሜሪካ ሸቀጦችን ለመግዛት ተዘጋጅታለች።ትራም የመሩት የአሜሪካ የመልዕክተኞች ጓድ ከባሕሬን፣ ከኩዌትና ከኦማንም ጋር መጠኑ ያልተነገረ የጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ የንግድ ልዉዉጥና የኢንቨስትመት ስምምነት ያደርጋል።ነዳጅ ዘይትና ጋዝ የሚዛቅባቸዉ 6ቱ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ የትብብር ምክር ቤት አባል ሐገራት አጠቃላይ ዓመታዊ ምርታቸዉ ከ2 ትሪሊዮን ዶላር ይበልጣል።
ትራምፕ የነዚሕ ሐገራት ገዢዎችን ልብ ለማማለል ወይም ኢራንን ለማናደድ ገና ከዋሽግተን ሳይነሱ የባሕረ-ሠላጤዉን ታሪካዊ መጠሪያ «ፋርስን» ትተዉ «የአረብ ባሕረ-ሰላጤ» ብለዉታል።አሉት እንጂ በይፋ የማስቀየር ሥልጣን የላቸዉም።ለነገሩ ለኢራንም ቢሆን ከሪያድ ያስተላለፉት መልዕክት ለስለስ ያለ ነዉ።«ኢራን አሸባሪዎችን መርዳቷን ካቆመች፣የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ካቋረጠች» ትራምፕ እንዳሉት ከቴሕራኖች ጋር «ለመስማማት» ዝግጁ ናቸዉ። ሊባኖስም በአዲሱ መንግስቷ ሒዝቡላሕን «አስወግዳ« ለማንሰራራት ተስፋ አላት ብለዋል።
ጋዛ በይፋዉ ዉይይትና መግለጫ ተዘንግታለች
ሥለጋዛዉ እልቂት ትራምፕም-አስተናጋጆቻቸዉምበይፋ ብዙም ያሉት የለም።መከረኛዉ የጋዛ ሕዝብ ግን ዛሬ እያለቀ ነዉ።ዘገቦች እንደ ጠቆሙት ሪያድ ላይ የቢሊዮነ-ቢሊዮናት ሽያጭ ግዢ ሲቀለጣጠፍ፣ ዉዳሴ-ሙገሳዉ ሲፈስ ዛሬ ጋዛ ዉስጥ 70 ፍልስጤሞች ተገድለዋል።ትራምፕ በዚሕ ጉዟቸዉ እስራኤልን አለመጎብኘታቸዉ ግን ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁን ገሸሽ-ገለል የማድረጋቸዉ መልዕክት ነዉ-እየተባለ ይተረጎም፣ ብዙ ይተነተን፣ይዘረዘር ይዟልም።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ