ዓለም የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር መስማማት ተስኖታል
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2017
የተመድ ያመቻቸው የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመው የጄኔቫው ጉባኤ ካለውጤት መጠናቀቁ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ተሰምቷል። የምድርም ሆነ የውኃ አካላትን ከሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች፤ እንዲሁም ከአደገኛ ንጥረ ነገሮች የሚዘጋጁ የፕላስቲክ ቁሳቁሶች እንዳይመረቱ በጋራ ለመወሰን ያልተቻለው ለምን ይሆን?
«ፕላስቲክ ማምረት ይቁም! ጥፋታችንን አታፋጥኑ! ጠንካራ የፕላስቲክ ስምምነት አሁኑኑ!»
ደማቅ ቀይና ቢጫ ቲሸርት የለበሱ ወደ 250 ገደማ የሚሆኑ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ጄኔቫ ከሚገኘው የተመድ ሕንጻ ፊት ለፊት ተሰልፈው ድምጻቸውን ያሰማሉ። እነሱ ከፊቱ ከሚገኙበት ሕንጻ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡት የ185 ሃገራት ተወካዮች የፕላስቲክ ብክለትን መቆጣጠር ከሚያስችል ስምምነት ለመድረስ ድርድር ይዘዋል። ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2017 ድረስ የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር ያለመ ጉባኤ ጄኔቭ ስዊትዘርላንድ ላይ ተካሂዷል። ለ11 ቀናት በዘለቀው ውይይትና ድርድር በርካታ አከራካሪ ነጥቦች ተነስተዋል።
የፕላስቲክ ብክለትን የመቆጣጠር ውይይቶች ሂደት
በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ዓ ም የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር ናይሮቢኬንያ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነበር ሃገራት ሕጋዊ አሳሪነት ያለው የጋራ ስምምነት እንዲኖር የተስማሙት። አላማው በዋናነት የፕላስቲክ ምርቶች ዳግም ለጥቅም መዋል የሚችሉበት እንዲሁም፤ የሚመረቱበት ጥሬ ዕቃም ምንነት ትኩረት እንዲያገኝ የሚለውን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህ መነሻነትም ስድስት ተከታታይ ውይይትና ድርድሮች በሦስት ዓመታት ውስጥ ቢካሄዱም ሃገራት ከስምምነት አለመድረሳቸው ባለፈው ዓርብ ይፋ ሆኗል።
እንደ ናይሮቢው ጉባኤ እቅድ ሃገራት የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ደንቦችን በጎርጎሪዮሳዊው 2024 መጨረሻ ላይ በጋራ ማጽደቅ ነበር። ሆኖም በ2025 ዓመተ ምሕረትም ከታሰበው ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ላይ ተነግሯል።
ያላስማሙ ነጥቦች
ለ10 ቀናት የታቀደው የፕላስቲክ ብክለትን መግታትን አላማ አድርጎ የታቀደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከታሰበበት አንድ ቀን ጨምሮ ሃገራት ሲደራደሩ ቢያመሹም በ11ኛው ቀን የተነገረው አለመሳካቱ ነው። ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት አሳሳቢው ነገር ተደራዳሪዎቹ ሃገራት ከስምምነት አለመድረሳቸው ብቻ ሳይሆን በቀጣይ እንዴት ይደረግ የሚለው ግልጽ አካሄድ አለመኖሩ ነው። በዚህም በርካታ ሃገራት ሀዘንና ቁጣቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል። የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ለዓመታት በተካሄደው ድርድር ተስፋ የተደረገው ስምምነት አለመገኘቱን አስመልክተው አንቶኒዮ ጉተሬሽ ያስተላለፉትን መልእክት በዕለቱ እንዲህ ገልጸዋል።
«ዋና ጸሐፊው ምንም እንኳን በውኃ አካላት ጭምር የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ ሕጋዊ ማሰሪያ ያለው ስልት ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም፤ ስምምነት ላይ ሳይደረስ በመጠናቀቁ በጣም አዝነዋል። እንዲያም ሆኖ አባል ሃገራት የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል እና በቀጣይ ሂደቱም ለመሳተፍ፤ በአላማ ለመተባበር፤ ዓለም የሚፈልገውን ስምምነት ለመፍጠር ለሰዎችና እና ለአካባቢ ፈተና የሆነውን እንቅፋት ለማስወገድ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አወድሰዋል።»
በ11ዱ ቀናት ድርድርና ውይይት ገሚሱ የፕላስቲክ ምርት መጨመርን ስለመቆጣጠር፤ ፕላስቲክ የሚመረትባቸው መርዛማ ንጥረ ነገሮችን የሚመለከት ሕጋዊ አሳሪነት ያለው ውል እንዲኖር ስለማድረግ፤ ገሚሱ ደግሞ የተመረተውን ፕላስቲክ ዳግም ጥቅም ላይ ስለማዋል፤ ዲዛይኑን ስለማሻሻልና መልሶ ስለመጠቀም ሃሳቦችን ሲያነሱ እንደከረሙ ነው የተነገረው።
በተለይም በስፋት ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ አምራች የሆኑ ሃገራትና የፕላስቲክ ኢንደስትሪዎች የፕላስቲክ ምርት መገደብን በመቃወም የቆሻሻ አወጋገድ እና ዳግም ለጥቅም ማዋል ላይ ትኩረት እንዲደረግ ተሟግተዋል። በዚህ ጉዳይ አጥበቀው ከተከራከሩት ሃገራት ዋነኞቹ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሳውድ አረቢያ እና ኩየት ይገኙበታል። ዋሽንግተን የፕላስቲክ ምርቶችንመገደብ፤ እንዲሁም በፕላስቲክ ምርት ሂደት የሚጨመሩ ነገሮች ላይ ሊደረግ የታሰበውን እገዳ አጥብቃ የተቃወመችው በማምረት ሂደት ላይ ዋጋ ያስጨምራል ከሚል መነሻ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋ።
የፕላስቲክ የጤና ጠንቅነት
በየዓመቱ በመላው ዓለም ከ400 ሚሊየን ቶን በላይ አዲስ ፕላስቲክ እንደሚመረት መረጃዎች ያመለክታሉ። ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ ካልተደረገ በጎርጎሪዮሳዊው 2040 ላይ የፕላስቲክ ምርት በ70 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል። አሳሳቢው ጉዳይ ከሚመረተው ፕላስቲክ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለአንዴ ብቻ ጥቅም ላይ ውሎ የሚጣል ነው። ከተጣለው የሚሰበሰበው 15 በመቶው ብቻ ሲሆን፤ ለዳግም ምርትነት የሚወሰደው ከዚሁ ላይ ዘጠኝ በመቶው ብቻ ነው።
46 በመቶው የሚሆነው ፕላስቲክ መሬት ላይ ይጣላል፤ 17 በመቶው ይቃጠላል፤ 22 በመቶው ደግሞ በየቦታው አፈር ላይ አንድም በውኃ አካላት ላይ ይወድቃል።
ግሪን ፒስ የተሰኘውን የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ወክለው በጄኔቫው ጉባኤ በታዛቢነት የተገኙት ሞሪትዝ ያገር ሮሽኮ የፕላስቲክ ውዳቂ እያስከተለ ያለውን ችግር ይናገራሉ።
«ፕላስቲክ በሁሉም ቦታ አለ። ፕላስቲክ በጣም ጥልቅ በሆነ የውቅያኖስ ጉድጓድ ሳይቀር አትላንቲክ ውስጥ ይገኛል። ፕላስቲክ በከፍተኛ ተራራዎች ጫፍ ላይ ሳይቀር አለ። በእኛም ውስጥ እንዲሁ አለ። በጊዜ ሂደት በሳምንባችን፤ በደማችን፤ እንዲሁም በጡት ወተታችንንም ውስጥ ተገኝቷል።»
እሳቸው የሚሉትን እውነትነት የሚያረጋግጡት የአካባቢ ተፈጥሮ የኬሚስትሪ ባለሙያ በሄምሆልስ ማዕከል የአካባቢ ተፈጥሮ ምርምር ፕሮፌሰር የሆኑት አኒካ ያንከም በበኩላቸው በምንበላው ምግብ እና መጠጥ ብቻ ሳይሆን በምንተነፍሰው አየርም ውስጥም ፕላስቲክ መገኘቱ በምርምር ተደርሶበታል ነው የሚሉት።
«እስካሁን በደረስንበት በምንበላው ምግብ፤ በምንጠጣው ውኃ እና ሌሎችም መጠጦች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአየር ውስጥም ፕላስቲክ አግኝተናል። ስለዚህ እንተነፍሰዋለን በምግባችን ውስጥ እንመገበዋለን። አሁን በእርግጠኝነት የማናውቀው ምን ያህል ጊዜ በሰውነት ውስጥ ይቆያል የሚለውን ነው። ሆኖም በሰውነት ውስጥ ሲያልፍ የሚለቀቅ ኬሚካልም ይዟል። ባለፈው ዓመት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፕላስቲክ በውስጡ ከ16 ሺህ ኬሚካሎች በላይ ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ ከአራቱ አንዱ አደገኛ እንደሆኑ እናውቃለን። ከአሉታዊ ተጽኦኗቸው አንዱ ለምሳሌ በሆርሞን ስርአት ላይ የሚመጣ ሊሆን ይችላል።»
የድርድሩ እጣ ፈንታ
የፕላስቲክ ቆሻሻ አካባቢን መበከሉም ሆነ የሚያስከትለው የጤና ጠንቅ በይፋ ቢታወቅም ሃገራት እንደተጠበቀው ሕጋዊ ማሰሪያ ያለው የፕላስቲክ ምርትን በመቀነስ እና ፕላስቲኩን ለመሥራት የሚውሉ መርዛማ ንጥረነገሮችን መቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም። ፈረንሳይ እና የአውሮጳ ሕብረት አባላትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሃገራት የፕላስቲክ ምርት እንዲቀንስ እና በምርት ሂደቱ ለጤና አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎች አጠቃለም ቁጥጥር እንዲደረግበት የሚያስገድድውል እንዲኖር ግፊት ቢያደርጉም አለመሳካቱ እንዳበሳጫቸው የፈረንሳይ የሥነ ምህዳራዊ ሽግግር ሚኒስትር ተናግረዋል። 14ቱ የፓስፊክ ትናንሽ ደሴት ሃገራት ወኪሎችም በተመሳሳይ ድርድሩ ይህን የመሰለ ስምምነት እንዳይኖር በሚፈልጉ ጥቂት ሃገራት እንቢታ መስተጓጎሉ አካባቢያቸውን ለተጨማሪ የፕላስቲክ ብክለት የሚያጋልጥ ብለውታል።
የማይታይ የጤና ስጋት መኖሩን የሚያምን ይኑር ወይም የሚታወቀው የፕላስቲክ ቆሻሻ በየቦታው መኖር የማያሳስበው ወገን ይኑር አንድ እውነት ግን አለ ይላሉ የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ መርኀግብር ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን፤ በዓለም ላይ የፕላስቲክ ጎርፍ መገታል አለበት።
«ይህን ችግር መፍታት የማያሻማ ግልጽ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በሰውነትህ ውስጥ ፕላስቲክ ካለ እኔም ሰውነት ውስጥ ፕላስቲክ አለ፤ ከሌላ ክፍለ ዓለም ያለ ሰውም በሰውነቱ ፕላስቲክ ካለ ያለን አማራጭ በጋራ ሠርተን መፍትሄ ማምጣት ብቻ ነው። ስለዚህ በዘርፈ ብዙ ቦታ ሠርተን ይህን እንዲሳካ ማድረግ ይኖርብናል።»
ብዙዎች በጄኔቫው ጉባኤ ላይ ተስፋ አሳድረው ድርድሩን በንቃት ቢያከናውኑም የታሰበው ውጤት ግን አልተገኘም። በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ምን መደረግ እንደሚኖርበትም የተባለ ነገር የለም። የውይይቱ መክሸፍ መዘዝ በየሀገሩ የቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች በፕላስቲክ እየተሞሉ ውቅያኖስን እየተደፈኑ፤ የባሕር ዳርቻዎችና ሌሎች ሕዝብ የሚገኝባቸው ቦታዎችም ላይ የሚከመሩ የፕላስቲክ ተራራዎችን በጋራ ለማስወገድ የሚያስችል ግልጽ መስመር አለመገኘቱን አስከፊ ያደርገዋል።
እስካሁን የፕላስቲክ ቆሻሻን መቆጣጠር የቻለች ሀገር ስዊድን ናት። 95 በመቶው የፕላስቲክ ውዳቂ አንድም ለዳግም አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል፤ አንድም ስኬታማ በሆነው የቆሻሻ ማስወገድ ስልታቸው ይከላል። ኬንያ ደግሞ ከፕላስቲክ ጋር በተገናኘ ከፍተኛውን ቅጣት የደነገገች ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ተነግሯል።
ሸዋዬ ለገሠ
ልደት አበበ