የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነትና የትራምፕ እርምጃ
ማክሰኞ፣ ጥር 20 2017የፓሪሱ የአየር ንብረት ውል ምንነት
የሙቀት አማቂ በካይ ጋዞችን ልቀት መጠን ለመቀነስ 195 ሃገራት የዛሬ 10 ዓመት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ተሰባስበው ከብዙ ውዝግብና ክርክር በኋላ የጉባኤው መዝጊያ ቀን ተራዝሞ ነበር ከስምምነት ደርሰው ፊርማቸውን ያኖሩት። በወቅቱ ሃገራት የተስማሙበት ዋና ጉዳይ ምንድነው የሚለውን የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሳቢን የአየር ንብረት ለውጥ ሕግ ማዕከል መሥራች ማይክል ጌራርድ እንዲህ ያስረዳሉ።
«የፓሪስ ስምምነት በ2015የዓለም ሃገራት በሙሉ በሚባል ደረጃ በተገኙበት የፓሪሱ ጉባኤ ላይ፤ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተላምዶ ለመኖር፣ እያንዳንዱ ሀገር በየራሱ ፍላጎት፤ በብሔራዊ ደረጃ የሚደረግ አስተዋጽኦ ማለት ነው፤ ብክለትን ለመቀነስ የተደረሰ ስምምነት ነው።»
የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ
እንዲህ ካለው ስምምነት ነው እንግዲህ የዓለም ከባቢ አየር ግንባር ቀደም በካይ ሃገራት ተብለው በታሪካዊ ሃላፊነት ከሚወቀሱት መካከል ዩናይትድ ስቴትስ እንድትወጣ በፕሬዝደንቷ የተወሰነው። ዶናልድ ትራምፕ ይህን ውሳኔ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የወሰኑት። ቀደም ሲልም ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው ይህንኑ እርምጃ ወስደው ነበር። ያኔ ግን የጊዜ ገደብ ስላላስቀመጡት የሥልጣን ጊዜያቸው በአራት ዓመት ሲገታ፤ በቦታቸው የተተኩት ጆ ባይደን ውሳኔያቸውን ቀለበሱትና የዋሽንግተን ትብብር ቀጠለ። ፕሮፌሰር ጌራርድ እንደሚሉት ግን ባለፈው ሳምንት ያሳለፉት ተመሳሳይ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ የሚሆን ዓይነት ነው።
«መጀመሪያ ዶናልድ ትራምፕ ሥራ ሲጀምሩ ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ትውጣ ቢሉም እሳቸው ከሥልጣን እስኪነሱ እስከ 2020 ድረስ ተግባራዊ ያልሆነ ሂደት ነበር። አሁን ግን የአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ ነው የተሰጠው፤ ስለሆነም ትራምፕ በሁለተኛው የፕሬዝደንትነታቸው ዘመን ዩናይትድ ስቴትስ መውጣቷን ይፋ አድርገዋል። ይህ ደግሞ ከአሁን ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ በሕግ እውን ይሆናል፤ ያ ማለት ይህ ተግባራዊ እንደሚሆን ሁሉም ያውቃል። ዩናይትድ ስቴትስ በቃ ወጥታለች።»
ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ ውል መውጣቷ ምን ያስከትላል?
እንዲህ ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔ ምን ያስከትል ይሆን? የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት የአየር ንብረት ሕግ ባለሙያ ክርስቲና ቮይት መዘዞቹን ያስረዳሉ።
«አሁን ምን ለውጥ ይኖራል ለሚለው፤ ለምሳሌ በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ከነበረው የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ ያልፋል። ይህ መሆኑ ደግሞ የማይቀር ነው። በተጠቀሰው ዓመት የሙቀት መጠኑ ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ የማድረግ ተስፋ ነበር፤ አሁን ግን ከዚያ ከፍ ማለቱን እናያለን። ይህ ደግሞ በእርግጥ እጅግ ግዙፍ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ እርምጃ ይፈልጋል። እናም የዓለም ሁለተኛ ኤኮኖሚ ባለቤትና ዋነኛዋ በካይ ሀገር ከፓሪሱ የጋራ ስምምነት መውጣት በጣም አሉታዊ ምልክት ነው፤ ሌሎች ወሳኝ ሀላፊነት ያለባቸው ሃገራትም፣ እንግዲህ ዩናይትድ ስቴትስ ቁርጠኛ ካልሆነች፤ እኛም የምናደርገው አነስተኛ ነው እንዲሉ ያደርጋል። በመሆኑም ሌሎች ወገኖች ሊያደርጉት በሚያስቡት እቅድ ላይ አፍራሽ ሚና የማስከተል አደጋ ይኖረዋል።»
የዶክተር ሚሊየን በላይን በየዓመቱ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤዎችን ለበርካታ ጊዜያት የተካፈሉና የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ ናቸው። ትራምፕ አሜሪካ ሃገራት ከተስማሙበት የብክለት ቅነሳ ስምምነት መውጣታቸው ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል የሚለውን አስተያየት ይጋራሉ።
ከቅሪተ አፅም የሚገኘው የነዳጅ ዘይት ቁፋሮ
ይህ ከራሷ ከአሜሪካን አልፎም የቴክኒዎሎጂ ሽግግሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ነው የገለጹት። ከቻይና ቀጥላ በዓለም የበካይ ሃገራት ተዋረድ በሁለተኝነት የተሰለፈችው ዩናይትድ ስቴትስ ከብክለት ቅነሳው የፓሪሱ ስምምነት በመውጣት ብቻ አልተገታችም። ትራምፕ የሀገራቸው የተፈጥሮ ሀብት ቆፋሪዎች ጠንክረው በሥራቸው እንዲገፉበት ማበረታቻቸውን አሰምተዋል።
«የግሽበት ቀውስ የመጣው ከመጠን ባለፈ ወጪ እና እየናረ በሄደው የኃይል አቅርቦት ዋጋ ምክንያት ነው። ለዚህም ነው ዛሬ ብሔራዊ አስቸኳይ የኃይል አቅርቦትን የማውጀው፤ እንቆፍራለን ፣ ውዴ እንቆፍራለን።»
ዶክተር ሚሊየን የትራምፕ እርምጃ አደገኛ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይሉታል፤ ይህን ቅስቀሳ። እሳቸው እንደሚሉት ስምምነቱን ተከትሎ አይቆፈሩም አይነኩም የተባሉት ሁሉ ለኩባንያዎች ክፍት የሚሆኑትበት አጋጣሚ ይከተላል። ያ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጡን ያባብሱታል። ምንም እንኳን የአሜሪካን እርምጃ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ማስከተሉ ባይቀርም፤ ሙሉ ለሙሉ ግን ተግባራዊነቱ ዜሮ ይሆናል ብለው አያምኑም። ለዚህ ደግሞ አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ለአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ ደንቦች ተገዢ የሆኑ አሉ ነው የሚሉት።
የአረንጓዴ የኃይል ምንጮች ጉዳይ
እንዲያም ሆኖ ግን በዓለም ደረጃ አረንጓዴ የኃይል ምንጭን የመጠቀሙ ጥረት መደናቀፍ ስለማይኖርበት ወደዚያ የሚደረገው ግፊት መቀጠል እንዳለበት ነው የተነገረው። የዓለም ሜትሪዎሎጂ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ምንም እንኳን የዋሽንግተን ከዚህ ስምምነት መውጣት ለአረንጓዴ የኃይል ምንጭ የሚውለውን በጀት ትርፋማነት ቢያዘገየውም ጥረቱ ግን ተጠናክሮ ቀጥሎ ለየሃገራቱ የሀብት ምንጭ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
ትራምፕ የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩን ከማይቀበሉት ወገን ናቸው። ይህ አስተሳሰብ እሳቸው ብቻም አይደለም በአብዛኛው ቀኝ ዘመም ፖለቲካ አራማጆች የዓለም የሙቀት መጠን መጨመርም ሆነ የከባቢ አየር መበከልን እውንነት እንደማይቀበሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያመላክታሉ። ሆኖም ግን መረጃዎች የዓለም የሙቀት መጠን ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መምጣቱን፤ የተፈጥሮ ቁጣም በየጊዜ እየጨመረ ለመከሰቱም ሆነ ለመደጋገሙ የአየር ንብረት ለውጥን በምክንያትነት ያቀርባሉ። ዶክተር ሚሊየን ወትሮ በሩቅ ይገምቱት የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አሁን በሁሉም ስፍራ እየታየ መሆኑን አስታውሰዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት ፈራሚ ሃገራትን እያነጋገረ ነው። ቻይና የዋሽንግተን ውሳኔ አሳዛኝ ስትል፣ በዚህ ረገድ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራትን ድምፅ አጉልታ በማስማት የምትታወቀው በጎርጎሪዮሳው 2030 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አስተናጋጅ ብራዚል እርምጃው በተጠቀሰው ዓመት ይደረስበታል ከተባለው ግብ ለመድረስ ሁኔታውን አዳጋች ያደርገዋል ነው ያለችው። አስተያየታቸውን ያካፈሉንን ዶክተር ሚሊየን በላይን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ