በሰሜን ወሎ የክረምት ዝናብ መጥፋቱ
ዓርብ፣ ሐምሌ 25 2017
አርሶ አደሩ መሬቱን አለስልሶ ዘሩን አዘጋጅቶ የክረምቱን ዝናብ መጠበቅ ከያዘ አንድ ወር ሊሞላው ነው የሚሉት በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ የሚገኙ አርሶአደሮች የደመናውን መጥቆር ተስፋ ብናደርግም አሳይቶ እየነሳን ክረምቱ እየተገባደደ ነው ይላሉ።
«‹ደመና ማታ ማታ ይመጣል መልሶ ይጠፋል። መጣ ሲባል መልሶ ይጠፋል፤ ከዚህ ጀምሮ ወደ ትግራይ ዝናብ የለም፤ ጸሎት እየተደረገ ነው።» «‹አሁን ደመና ግጥም ብሎልናል አደራህን እያልን ነው አሳይተን አትንሳን እያልን ነው፤ የገብርኤል ትንሽ ጠብ ጠብ ብሎ ነበር ከዚያ በኋላ የለም።»
የክረምት ዝናብ መዘግየት በሰሜን ወሎ
የክረምቱ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመጣል ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰሜን ወሎ ሀገረስብከት እና የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም በሰሜን ወሎ ዞን ጸሎት እና ዱአ እንዲደረግ አዘዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የወልዲያ ከተማ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ጥበባት አክሊለ ብርሃን ክረምቱ እየተገባደደ ስለመጣ ጸሎት ለፈጣሪ እያቀረብን ነው ብለዋል።
«91 ቀን በመሆኑ ወቅቱ የፀደይ፣ የክረምት፣ መፀው እና ሀጋይ አሁን 1 ወር ሊሆነን ነው ክረምቱ ከዘገየ፤ሰኔ 26 የክረምት መግቢያ ነው፤ የተወሰነ ካፊያ ቢኖርም አለው ማለት አይቻልም፤ የዝናብ እጥረት ሲገጥም ወደፈጣሪ ይጸለያል፤ ምላሽም ይሰጣል።»
የሃይማኖት ተቋማት በሎትና ዱዓ እንዲደረግ አውጀዋል
በተመሳሳይ የሰሜን ወሎ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጸሐፊ የሆኑት ሀጂ አሊጋዝ አስረስም የክረምቱ ጊዜ እየተገባደደ በመሆኑ ከፈጣሪ ምሕረት ለመሻት ዱአ አድርገናል ይላሉ።
«በክረምት ዝናብ አይለመንም ነበር፤ ዝናብ ሲቀርብን ግን ምን አጥፍተን ነው፣ ምን አጉድለን ነው ብለን በሶላት አላህን ለምነናል።»›
በሰሜን ወሎ ዞን ያሉ አርሶ አደሮች በዚህ ወቅት ዘር ዘርተው የመጀመሪያ ዙር አረም የሚያርሙበት ጊዜ ነበር የሚሉት የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ተገኝ አባተ ለቆላማ አካባቢዎች ግን ዝናቡ እስካሁን አልጣለም ሲሉ ይናገራሉ።
«በሰሜን ወሎ በዚህ ጊዜ 1ኛ አረም የምናርምበት ጊዜ ነበር፤ ዛሬ ሐምሌ 24 ነው ዝናብ ችግር የሆነው ቆላማዎቹ አካባቢዎች ሀብሩ፣ ራያ፣ ጉባላፍቶ እስካሁን ዝናብ አልዘነበም። ከሰብል ምርት ጋር ተያይዞም አካባቢዎቹ ተመራጭ ናቸው።»
በሰሜን ወሎ ዞን በክረምት ጊዜ በሰብል የሚሸፈነው 231 ሺህ ሄክታር መሬት ሲሆን የክረምቱ መዘግየትም በሰብል ምርት ላይ መስተጓጎል ሊፈጥር ይችላል ሲሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ተገኘ አባተ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንደ ብሔራዊ ሜትሮዎሎጂ ግንበያ ከሆነ በቀጣዩ ሁለት ቀናት ከበድ ያለ ዝናብ ይጥላል ተብለን እሱን እየጠበቅን ነው ይላሉ።
«የሜትሮሎጂ ትምበያ ሲታይ በዚሁ ሁለት እና ሦስት ቀን ከበድ ያለ ዝናብ እንደሚዘንብ ነው ያለው ትንበያ፤ አሁን አካባቢው ዝናባማ የአየር ንብረት አለው፤ የሚታየው ደመና ወደ ዝናብ ተቀይሮ በዚህ ሁለት ሦስት ቀን ከዘነበልን አርሶ አደሩ ለመዝራት ተዘጋጅቷል።»
በሰሜን ወሎ ዞን ያሉ ቆላማ አካባቢዎች 92ሺህ ሄክታር መሬት በክረምቱ የሰብል ልማት የሚሸፈን ቢሆንም በዝናብ እጥረት ምክንያት ግን ዘር መዝራት አልተቻለም።
ኢሳያስ ገላው
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ