የጳጉሜ 2 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጳጉሜን 2 2012የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ ኹለተኛ ግጥሚያውንም ትናንት ያለ ድል አጠናቋል። የማንቸስተር ሲቲ ኹለት ተጨዋቾች በኮሮና ተሐዋሲ መጠቃታቸውን ቡድናቸው ዐስታውቋል። የባየር ሌቨርኩሰኑ ካይ ሐቫርትስ በቡንደስሊጋው ውድ ክፍያ ዝውውር በ100 ሚሊዮን ዩሮ ለቸልሲ ፈርሟል። አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ እንደተመኘው ባርሴሎናን ጥሎ መሄድ አልተፈቀደለትም። ቢያንስ ለአንድ ዓመት በባርሴሎና ይቆያል ተብሏል። የዓለማችን ምርጡ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች በወሳኝ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያው በፈጸመው ከባድ ስኅተት
ኔሽንስ ሊግ
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ለኔሽን ሊግ ግጥሚያ ትናንት ከስዊዘርላንድ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ባለፈው ሳምንት ከስፔን ጋር በነበረው ተመሳሳይ የኔሽን ሊግ ግጥሚያ በተመሳሳይ ውጤት ነው የተለያየው።
ኔሽን ሊግ፦ የአውሮጳ (UEFA) 55ቱም አባል ቡድኖች ተሳታፊ የሚኾኑበት ግጥሚያ ነው። ውድድሩ በአራት ምድብ ተከፍሎ ነው የሚከናወነው። የመጀመሪያው ውድድር በ2018/2019ነበር የተከናወነው። ኹለተኛው ዙር ዘንድሮ 2020/21 እየተከናወነ ነው። እስከ ጥቅምት ወር ድረስም የምድብ ግጥሚያ ይከናወናል። እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ ወር ድረስም ውድድሩ ተከናውኖ የየምድቦቹ አሸናፊዎች በግማሽ ፍጻሜ እና በፍጻሜው ሰኔ ላይ ይጫወታሉ።
ጀርመን በምትገኝበት ምድብ 4 ስፔን በ4 ነጥብ አንደኛ፤ ዩክሬን በ3 ነጥብ 2ኛ ሲኾኑ፤ ጀርመን በ2 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ስዊዘርላንድ 1 ነጥብ ይዞ የመጨረሻውን 4ኛ ደረጃ ይዟል። የምድቡ መሪ ስፔን ቅዳሜ ዕለት ዩክሬንን 4 ለ0 ነው ያሸነፈችው። ቱርክ ከሰርቢያ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የበርካታ ሃገራት ቡድኖች የወዳጅነት ግጥሚያቸውን አከናውነዋል። ብሬመን ከሐኖቨር፤ አያክስ አምስተርዳም ከአውግስቡርግ፤ ሻልከ ከቦሁም፤ ማግደቡርግ ከቮልፍስቡርግ፤ ብሬመን ከሬህደን፤ ሽቱትጋርት ከሽትራስቡርግ፤ ሐምቡርግ ከሄርታ ቤርሊን፤ ዑኒዮን ቤርሊን ከኑይረንበርግ፤ ሊቨርፑል ከብላክፑል ያደረጓቸው ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ።
ሊቨርፑል በግብ በተንበሸበሸበት የቅዳሜው ግጥሚያ 7 ለ2 በማሸነፍ በዕለቱ ከነበሩ ግጥሚያዎች ከፍተኛውን ግብ አስመዝግቧል። ቅዳሜ ዕለት በአጠቃላይ ከ60 በላይ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። የወዳጅነት ግጥሚያው ትናንትም የተከናወነ ሲኾን፤ ዛሬም ቀጥሎ 5 ግጥሚያዎች ይኖራሉ።
ካይ ሐቫርትስ ለቸልሲ መፈረሙ
የ21 ዓመቱ ወጣት የባየር ሌቨርኩሰን ተጨዋች ካይ ሐቫርትስ በ100 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ወደ ቸልሲ ተዘዋውሯል። ቸልሲ የቡንደስሊጋው ውድ ተጨዋችን ያስፈረመው ከዓምስት ዓመት በላይ ነው። ቸልሲ ቀደም ሲል የላይፕሲሹን ቲሞ ቬርነር በ50 ሚሊዮን እንዲሁም የአያክስ አምስተርዳሙ ሐኪም ኂይሽን በ40 ሚሊዮን ዩሮ ማስመጣቱ የሚታወስ ነው።
በዚህም ቸልሲ በሚቀጥለው የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚኾን ከወዲሁ ይጠበቃል። ካይ ሐቫርትስ በለንደን ቆይታው የሀገሩ ልጆች ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር እና ቲሞ ቬርነር አብረውት ስለሚጫወቱ እንግዳነት ብዙም አይሰማውም።
ካይ ወደሌላ ሀገር የሊግ ቡድን ካቀኑ ከቡንደስሊጋ የቀድሞ ተጨዋቾች ኹለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ነው። ከዚህ ቀደም በ2017 የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ዑስማኔ ዴምቤሌ ወደ ባርሴሎና የተዛወረው በ105 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ነበር።
ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎና ይቆያል
አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ የኮሮና ምርመራ አድርጎ ዛሬ ወደ ቡድኑ ባርሴሎና ልምምድ እንደሚመለስ ትናንትና ተገልጦ ነበር። ባለፈው ሳምንት ምርመራ እንደማያደርግ በአባቱ በኩል ዐሳውቆ የነበረው ሊዮኔል ሜሲ ዛሬ በባርሴሎና አዲሱ አሰልጣኝ ሮላንድ ኮዬማን ስር ኾኖ ወደ ልምምዱ ተመልሷል። ከእንግዲህም ቢያንስ ለአንድ ዓመት ለልጅነት ቡድኑ ባርሴሎና የመጫወት ግዴታ አለበት።
ሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ ባርሴሎና በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ በጀርመኑ ባየር ሙይንሽን 8 ለ2 በኾነ ከባድ ሽንፈት ከውድድሩ ከተሰናበተ በኋላ እሱም ቡድኑ ውስጥ መቆየት እንደማይፈልግ ዐስታውቆ ነበር። የ33 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂን ለማስፈረም የተለያዩ የአውሮጳ ቡድኖች ፍላጎት አሳይተው የነበረ ቢኾንም የስፔን ሊጋ ባስቀመጠው የሰባት መቶ ሚሊዮን ክፍያ የተነሳ ምኞታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ፕሬሚየር ሊግ ኮሮና
የማንቸስተር ሲቲ ኹለት ተጨዋቾች በኮሮና ተሐዋሲ መጠቃታቸውን ቡድናቸው ዐስታወቀ። አልጀሪያዊው አማካይ ሪያድ ማህሬዝ እና የፈረንሳዩ ተከላካይ አይመሪክ ላፖርቴ ናቸው። ኹለቱ ተጨዋቾች በኮሮና ተሐዋሲ የመያዝ ምልክት እንደማይታይባቸው ግን የቀድሞው የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ባለድል ይፋ አድርጓል። ተጨዋቾቹ በፕሬሚየር ሊግ እና በብሪታንያ መንግስት መመሪያ መሠረት ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ለይተው ለሚቀጥሉት ቀናት ይቆያሉ።
እንግሊዝ ውስጥ በኮሮና የተጠቃ ሰው ለዐስር ተከታታይ ቀናት ከሌላ ሰው ጋር ሳይገናኝ ራሱን ለይቶ ይቆያል። በፕሬሚየር ሊጉ የቀጣይ ዘመን ውድድር ማንቸስተር ሲቲ የመጀመሪያ ግጥሚያውን ከኹለት ሳምንት በኋላ የሚያከናውነው ከዎልቨርሐምፕተን ጋር ነው። በዚያ ውድድር ኹለቱ ተጨዋቾች መሰለፍ ይችላሉ።
የሜዳ ቴኒስ
በሜዳ ቴኒስ ውድድር ዘንድሮም ዋንጫውን ይወስዳል ተብሎ የተጠበቀው ሰርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ በፈጸመው ስህተት በዳኞች ውሳኔ ከውድድሩ ተሰናብቷል። በዚህ ዓመት ባደረጋቸው 20 ውድድሮች 20ውንም በማሸነፍ ለዩኤስ ኦፐን ሩብ ፍጻሜ ደርሶ የነበረው ሠርቢያዊ ራሱን ከውድድሩ በራሱ ጥፋት አሰናብቷል።
የ33 ዓመቱ ኖቫክ ጄኮቪች በጨዋታ በመበለጡ ከተናደደ በኋላ የሜዳ ቴኒስ ኳሷን ወደ ጎን በመሠረብ ኾን ብሎ ባይኾንም የመስመር ዳኛዋን አንገት መትቷል። የመስመር ዳኛዋ ትንፋሽ አጥሯቸው ሜዳው ላይ ሸብረክ ብለው አንገታቸውን በመያዝ ሲሰቃዩ ታይተዋል። ወደ መስመር ዳኛዋ በፍጥነት ያመራው ኖቫክ ጄኮቪች ኳሱን ወደ መስመር ዳኛዋ የሠረበው ኾን ብሎ እንዳልኾነ ቢገልጥም፤ ጨዋታውን ሲመሩ የነበሩት ዳኞች ግን ተመካክረው ከውድድር ውጪ እንደኾነ ነግረውታል።
ኖቫክ ጄኮቪች አንድ ጨዋታ ቢቀጣ አለያም ሌላ አማራጭ ቢወሰድ ፍላጎቱ እንደኾነ ለዳኞቹ በመንገር ለመከራከር ቢሞክርም ከጨዋታ የመታገዱን ውሳኔ ግን ዳኞቹ ሳይሰርዙት አጽንተውታል። እሱም ተጋጣሚውን ጨብጦ የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ መሠረቢያውን እና ሻንጣውን ሸካክፎ በንዴት ከሜዳ ወጥቷል።
ከትናንትና ጀምሮ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የዓለማችን ዕውቁ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች የፈጸመውን ተግባር ኮንነዋል። ኖቫክ ጄኮቪች በትናንቱ ውድድር የመስመር ዳኛዋን በኳስ ከመምታቱ በፊት ነጥብ ሲቆጠርበት በንዴት ኳሷን ከሜዳው ውጪ በዘፈቀደ ሲሰርብ ነበር። ይህ ድርጊቱ ሊያስቀጣው እንደሚችልም ጨዋታውን ሲተነትኑ የነበሩ ጋዜጠኞች አስቀድመው ሲናገሩ ነበር። እንደተባለውም ለዋንጫ ደርሶ የማሸነፍ ዕድሉን በሠራው ጥፋት በሩብ ፍጻሜው አምክኗል።
ኖቫክ ጄኮቪች ዘንድሮ የዩኤስ ኦፐን ግጥሚያ ዋንጫን ያነሳል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር። ዋነኛ ተፎካካሪዎቹም በውድድሩ ተሳታፊ አልነበሩም። ስፔናዊው ራፋኤል ናዳል ወደ ኒውዮርክ ተጉዞ መወዳደሩን ያልፈለገው በከተማዪቱ የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭትን በመፍራት ነው። ስዊዘርላንዳዊው ዕውቅ የሜዳ ቴኖስ ተፎካካሪ ሮጀር ፌዴሬር ደግሞ የጉልበት ጉዳት ስለገጠመው በውድድሩ መሳተፍ አልቻለም። እናም ይኼ አጋጣሚ ለኖቫክ ጄኮቪች 18ኛ የዋንጫ ድሉን ለማስመዝገብ መልካም አጋጣሚ ነበር። ድንገተኛ ንዴት እና ግልፍተኝነት ግን ለዓመታት የለፋበትን ውጤት ሳያጣጥመ መክኖ እንዲቀር ከመንገድ አስቀርቶታል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ