የጥር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 26 2017የኬንያ እና የሱዳን አትሌቶች የተሳተፉበት 42ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በትናንትናው ዕለት ተከናውኗል አዲስ አበባ ውስጥ ። የዩጋንዳ አቻቸውን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የሚገጥሙት ሉሲዎቹ ከጅቡቲ ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ ሊያደርጉ ነው ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ ውጤቶችንም አጠር አድርገን እናቀርባለን ።
አትሌቲክስ
4 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበለት 42ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ተከናወነ ። በወንድ እና በሴት የ6፣ የ8 እና የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድሮች እንዲሁም የድብልቅ ሪሌ ፉክክር መከናወኑም ተጠቅሷል ። በውድድሩ ከክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ቡድኖች እና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በተጨማሪ ከኬንያ እና ከሱዳን ሁለት ሁለት አትሌቶች ተሳታፊ እንደነበሩም ተዘግቧል ።
የውድድሩ ዓላማ በዋናነት አትሌቶች በአገር ውስጥ የውድድር እድል እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑም ተገልጧል ። የተለያዩ አትሌቶችን ከተለያዩ ዘርፎች በማሳተፍ የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል መፍጠርም ዋነኛ ግቡ እንደነበር ተጠቁሟል ። በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች በአጠቃላይ የ865,000 ብር የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱንም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘግቧል ። ደረጃቸውን የጠበቁ የመወዳደሪያ ስፍራዎች በበቂ በሌሉበት ሁኔታ መሰል ውድድሮች ጠቀሜታቸው ላቅ ያለ ነው። በኢትዮጵያ በዋናነት የመሮጫ ቦታዎች እጥረት ብርቱ ፈተና መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል ። የጥር 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
እግር ኳስ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ትናንት በአርሰናል 5 ለ1 ጉድ ሁኗል ። ለማንቸስተር ሲቲ የማጽናኛዋን ብቸና ግብ ኧርሊንግ ኦላንድ አስቆጥሯል ። ጨዋታው በተጀመረ 2ኛ ደቂቃ ላይ በማርቲን ኦዴጋርድ ማግባት የጀመረው አርሰናል መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው ሦስተኛ ደቂቃ ጭምር ተከታታይ ግቦችን ሲያስቆጥር ነበር ። ቶማስ ፓርቴይ፣ ማይለስ ሌዊስ እና ካይ ሐቫርትስ እንዲሁም ኤታን ንዋኔሪ አምስቱን ግቦች በተከታታይ በማስቆጠር ማንቸስተር ሲቲን ኩም አድርገዋል ። አርሰናል በደረጃ ሰንጠረዡም 50 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ መሆን ችሏል ።
ቅዳሜ ዕለት በርመስን በሜዳው 2 ለ0 አሸንፎ የተመለሰው መሪው ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረውም አርሰናልን በስድስት ነጥብ ይበልጣል ። 56 ነጥብ አለው ። ብራይተንን የግብ ጎተራ አድርጎ 7 ለ0 ያበራየው ኖቲንግሀም ፎረስት በ47 ነጥብ ሦስተኛ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ 41 ነጥቡ ላይ ተወስኖ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ክሪስታል ፓላስን ትናንት አስተናግዶ የ2ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። በ29 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይዋዥቃል ። ላይስተር ሲቲ፣ ኢፕስዊች ታወን እና ሳውዝሐምፕተን ከ18ኛ እስከ 20ና ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ። የጥር 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ትናንት ሆልሽታሽን ኪዬልን 4 ለ3 አሸንፎ ነጥቡን 51 በማድረስ በመሪነት እየገሰገሰ ነው ። ባዬርን ሌቨርኩሰን በ45 ይከተላል ። ትናንት አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትበትም ሆፈንሀይምን 3 ለ1 ድል አድርጓል ። ከቮልፍስቡርግ ጋር ትናንት አንድ እኩል የተለያየው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በቡንደስሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ ይገኛል፥ 38 ነጥብ አለው ። ላይፕትሲሽ በ33 ነጥብ አራተኛ ነው፥ ቅዳሜ ዕለት ከዑኒዮን ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። ሐይደንሀይም፣ ሆልሽታየን ኪዬል እንዲሁም ቦሁም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተደርድረዋል ።
ሉሲዎች
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ከጎረቤት ጅቡቲ ጋር የወዳጅነት ከኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ይጋጠማል ።
በአፍሪቃ አገራት የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ (WAFCON) የማጣሪያ የመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ግጥሚያዎቹ የካቲት ወር ውስጥ ይከናወናሉ ። የመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ከመከናወኑ በፊት የፊታችን ረቡዕ ሳምንት (የካቲት 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) ሉሲዎች ከጅቡቲ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የወዳጅነት ግጥሚያ ያከናውናሉ ። የመልሱ ጨዋታም የካቲት 9 ቀን እዛው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሊከናወን ቀጠሮ ተይዟል ።
የጅቡቲ ቡድን በዓለም አቀፍ መድረክ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ያለፉትን ስድስት ግጥሚያዎች ብንመለከት በሁሉም አንዲትም ግብ ሳያስቆጥር በሰፋ ግብ ነበር የተሸነፈው ። በሩዋንዳ የ2 ለ0፤ በብሩንዲ የ3 ለ0፤ በዩጋንዳ የ5 ለ0 እንዲሁም በቶጎ የ6 ለ0 እና 7 ለ0 በደርሶ መልስ የ13 ለ0 ግብ መሸነፉ ይታወሳል ።
የጅቡቲ ቡድን ከሉሲዎቹ ጋር ካደረጋቸው ግጥሚያዎች ከአምስት ዓመት በፊት ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ 8 ለ0 በደርሶ መልስ 10 ለ0 ያሸነፉበት ከፍተኛው ነው ። በአንጻሩ የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ተጋጣሚው የዩጋንዳ ቡድን ከሉሲዎቹ ጋር ተገዳዳሪ መሆኑ ይታወቃል ። ለአዲሱ የሉሲዎች አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከጅቡቲ ጋር የተዘጋጀው የወዳጅነት ግጥሚያ ምን የሚፈይደው ነገር ይኖራል? የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ።
ሉሲዎቹ ከዩጋንዳ ጋር የሚያደርጓቸው የደርሶ መልስ የአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ደግሞ ለካቲት 14 እና 19 ቀጠሮ ተይዞባቸዋል ። ዩጋንዳ በአንጻሩ በአፍሪቃ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ጠንካራ የሚባል ቡድን ነው ። የዛሬ ሁለት ዓመት ከስምንት ወር ከሉሲዎቹ ጋር ባደረገው ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ግጥሚያ የኡጋንዳ ቡድን በደርሶ መልስ 1 ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል ። ሁለቱ ቡድኖች ለአፍሪቃ ዋንጫ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስድስት ግጥሚያዎች፦ ኢትዮጵያ ኡጋንዳን ሦስት ጊዜ አሸንፋ አንድ ጊዜ አቻ ወጥታለች ። ኡጋንዳ ኢትዮጵያን ሁለት ጊዜ አሸንፋ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይታለች ። የዩጋንዳ ቡድን የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴው ጠንከር ያለ ከመሆኑ አንጻርስ አሰልጣኙ ምን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል? የጥር 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድ ተከላካይ ናኦሚ ግርማ
ናኦሚ ግርማ የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ በመግባት የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት መሆን ችላለች ። ምንም እንኳን ሳን ሆዜ ካሊፎርኒያ ተወልዳ ብታድግም ከእንግሊዝኛ ባሻገር አማርኛም የምትናገረው ናኦሚ ኳስ የጀመረችው በአባቷ የተነሳ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል ። አባቷ «ማለዳ ሶከር» በሚል ሳን ሆዜ ውስጥ ባቋቋሙት ቡድንም ናኦሚ የኳስ ሕይወቷን ሀ ብላ በመጀመር በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ መሆን ችላለች ። «ማለዳ ሶከር» የተቋቋመው ኢትዮጵያውያን ልጆች እንዲገናኙበት ለማድረግ እንደነበረም ተዘግቧል ። አባቷ አቶ ግርማ ዐወቅ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተሰደዱት ጦርነትን በመሸሽ፤ እናቷ ወ/ሮ ሠብለ ደምሴ ደግሞ ለትምህርት እንደነበር ቢቢሲ አክሎ ዘግቧል ።
ናኦሚ በሴቶች የእግር ኳስ ታሪክ ከዚህ ቀደም የነበረውን የዝውውር ክፍያ ክብረ ወሰን መስበርም ችላለች ። በአንድ ሚሊዮን ዶላር ከዩናይትድ ስቴትስ ሳና ዲዬጎ ዌቭ ቡድን ወደ እንግሊዙ ቸልሲ ቡድን የተዘዋወረችው ናኦሚ የዓለማችን ምርጥ ተከላካይ መሆኗም ተዘግቧል ። ከዚህ ቀደም ከፍተኛው የዝውውር ክፍያ 866,000 ዶላር ነበር ። ክፍያውም በቤይ ኤፍ ሲ ቡድን ለማድሪድ የተፈጸመው የዛምቢያዋ አጥቂ ራቼል ኩንዳናንጂን ባለፈው ዓመት ለማስመጣት ነበር ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ