የጤና ባለሞያዎች ጥያቄዎች ትኩረት እንዲሰጣቸውና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ኢሰመኮ አሳሰበ
ሐሙስ፣ ግንቦት 14 2017በጤና ባለሞያዎች የቀጠለው የሥራ ማቆም አድማ እና በመንግሥት የሚወሰዱ ርምጃዎች አፋጣኝ መፍትኄ ሊያገኙ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ። ችግሩ በመቀራረብ እና በመነጋገር ሊፈታ ይገባል ያለው ኢሰመኮ ፖሊስ የሕክምና ባለሞያዎችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን መገንዘቡንም ዐሳውቋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ከ20 ያላነሱ የጤና ባለሞያዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች መታሰራቸውን ጠቅሷል። ሁሉም በአስቸኳይ እንዲለቀቁም ጠይቋል። መንግሥት ለጥያቄው ሰላማዊ እና አፋጣኝ መፍትኄ እንዲሰጥ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየጠየቁ ሲሆን፤ የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ ባለሞያዎቹ በአስቸኳይ ወደ ሥራቸው ካልተመለሱ የሞያ ፍቃድ ሊነጠቁ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕክምና ባለሙያዎች ለመንግሥት ያቀረቧቸው ያላቸውን ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ከጥቅማጥቅም፣ ከምቹ የሥራ ቦታ ጋር የተያያዙ 12 ጥያቄዎች በሰጡት 30 ቀናት ምላሽ አላገኙም በሚል "ከግንቦት 5 ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን" መረዳቱን ገልጿል።
ኢሰመኮ ጉዳዩን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ ከጤና ባለሙያዎች ተወካዮች ጋር ውይይቶች ማድረጉንና በዚህም "በአንዳንድ የሕክምና ተቋማት በጽኑ ሕሙማን ማዕከል የሚገኙ ታማሚዎችን ጨምሮ በሐኪሞች እጥረት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸውን፣ ከክልል ከተሞች ረጅም ቀጠሮ ጠብቀው ለሕክምና የመጡ ታካሚዎች ለእንግልት የተዳረጉ መሆኑን፣ በባለሙያዎች እጥረት ምክንያት አንዳንድ የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎችን ለረጅም ፈረቃዎች እንዲሠሩ ለመመደብ የተገደዱ መሆኑን" አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል
የሪጅን ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ሙሉጌታ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ በተፈጠረው ኹኔታ ታካሚዎች ሕክምና ለማግኘት ለረጅም ሰዓታት እንደሚጠብቁም ለማረጋገጥ ተችሏል። ኮሚሽኑ ሁለቱን አካላት [መንግሥትን እና የጤና ባለሙያዎችን] አቀራርቦ ለማወያየት ዝግጁ መሆኑንም አቶ ዮናስ ገልፀዋል። ኢሰመኮ ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ አድርገዋል፤ በሌሎች በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰዋል ያላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ያዋለ መሆኑን፣ አያያዛቸውን አስመልክቶም ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ፣ የጤና ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያ
የተለያዩ የሲቪክ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህ ገዳይ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው እና የችግሩ አፈታትም ሰላማዊ እንዲሆን እየጠየቁ ነው። ከእነዚህም መካከል ኢሶዴፓ አንዱ ሲሆን የፓርቱው ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ አሁንም ችግሩን ለመፍታት ጊዜ አለ ሲሉ ገልፀዋል። የጤና ሚንስትር ደኤታ ዶ.ር ደረጀ ድጉማ የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት የጤና ባለሙያዎች በአስቸኳይ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ ይህ ካልሆነ የሙያ ፍቃድ ሊነጠቁ እንደሚችሉ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ እስጠንቅቀዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ግን "ከሥራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እና ሌሎች ማናቸውም እርምጃዎች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች እና የሰብአዊ መብቶች መርኾዎችን የተከተሉ ሊሆኑ እንደሚገባ" ማሳሰባቸው ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ተጠቅሷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የታሰሩ ባለሙያዎች እንዲለቀቁ ጠይቋል
የመብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናልትናንት ኤክስ ላይ ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት ከ20 ያላነሱ የጤና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ መታሰራቸውን በመግለጽ ባለሥልጣናት መብታቸውን በመጠቀም ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ የታሰሩትን የጤና ባለሙያዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ