አዲስ አበባ የውጭ ዜጎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዙ ተክልከዋል ሲል የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ
የትግራይ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ወደ ትግራይ ለጉብኝት የሚጓዙ ቱሪስቶችን ጨምሮ በተለያየ ስራ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች ወደ ክልሉ እንዳይጓዙ በኤርፖርቶች ክልከላ እየተደረገባቸው ነው ሲል ትናንት ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ቱሪዝም ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ አስታወቀ ። ወደ ትግራይ የሚጓዙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እና ሌሎች ባለጉዳዮች በኤርፖርቶች መጉላላት እየገጠማቸው መሆኑን ያስታወቀው ቢሮው ከግንቦት 2 ቀን ወዲህ የጉዞ ክልከላ መኖሩን ገልጿል። ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት ወንድሙ አሳምነው ለፈረንሳይ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት «የውጭ ዜጎች ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ መታገዳቸውን አረጋግጣለሁ» ቢሉም ምክንያቱ ግን እንደማይታወቅ ተናግረዋል። የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሐላፊ አቶ ኃይላይ በየነ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፌዴራሉ መንግስት አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
የፌደራል ባለስልጣናትም ሆኑ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዳልሰጡት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አስታውቋል። የትግራይ ቱሪዝም ቢሮም በውጭ ዜጎች ላይ የተጣሉት ገደቦች በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት ሆነዋል ሲል ተናግሯል። አፍሪካ ኢንተለጀንስ የተባለው ድረ ገጽ ከአዲስ አበባ ወደ አፋርና ትግራይ ክልሎች የሚሄዱ መንገደኞች ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲመለሱ እየተደረገ ነው ሲል ዘግቧል።ድረ ገጹ መመሪያው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የወጣ ነው ሲልም ጠቅሷል።
ሪያድ ትራምፕ የመካከለኛ ምሥራቅ ጉብኝታቸን በሳዑዲ አረብያ ጀመሩ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአራት ቀናት የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝታቸውን ዛሬ በሳዑዲ አረብያ ጀመሩ። ትራምፕ ሪያድ እንደገቡ የሳዑዲ አረብያን የመሪነት ሥልጣን ይዘዋል ተብለው የሚታሰቡት ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን አቀባበል አድርገውላቸዋል። ትራምፕን ይዞ የተጓዘው Air Force One በሳዑዲ አየር ኃይል F-15 ጀቶች ታጅቦ ነበር በሳዑዲ አረብያ ዋና ከተማ ሪያድ ያረፈው። ትራምፕ በአራቱ ቀናት ጉብኝታቸው፣ የኢራንን የኒዩክልየር መርሃ ግብርን ለማፈራረስ አሜሪካን የጀመረችው ጥረት፣ የጋዛውን ጦርነት ማስቆም እንዲሁም የነዳጅ ዘይት ዋጋን ማውረድ ላይ የሚያካሄዱት ንግግሮች ይገኙበታል። የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ለትራምፕ ባደረጉት የምሳ ግብዣ ላይም ኤለን ሙስክን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ የአሜሪካን ኩባንያዎች ባለቤቶችም ተገኝተዋል። ትራምፕ ዛሬ በሚካሄደው የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ ይገኛሉም ተብሏል። በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝታቸው ሳዑዲ አረብያን የመጀመሪያ መዳረሻቸው ያደረጉት ትራምፕ ሳዑዲ አረብያ በዩናይትድ ስቴትስ ትላልቅ ኢንቬስትመንቶችን ለማካሄድ ቃል በመግባትዋ መሆኑ ተዘግቧል። ትራምፕ በቀድሞው የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ቀብር ላይ ለመገኘት ስልጣን ከያዙ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣሊያን ሄዱ እንጂ የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን በሳዑዲ አረብያ ለማድረግ ነበር ያቀዱት። በትራምፕ የአሁኑ ጉብኝት የተካተቱት ሳዑዲ አረብያ፣ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበው በወንዶች ልጆቻቸው የሚመሩት የትራምፕ የቤቶች ግንባታ የሚያካሂዱ ድርጅቶች የሚገኙባቸው ሀገራት ናቸው። ከመካከላቸው የጂዳው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ፣የዱባዩ ቅንጡ ሆቴል እና የኳታሮቹ ቪላዎች ይገኙበታል። ትራምፕ ከሦስቱ ባለጸጋ ሀገራት ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በኃይል ትብብር ላይ ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በርሊን የጀርመን ንጉሳዊ አገዛዝ የተባለውን ቀኝ ጽንፈኛ ቡድን አገደች
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት የጀርመን ንጉሳዊ አገዛዝ «Kingdom of Germany» የተባለውን ቀኝ ጽንፈኛ ቡድን አገዱ። የዚሁ «የጀርመን ዘውዳዊ ስርዓት የዜጎች ንቅናቄ» የተባለው ቡድን አንጃ መሪ የተባሉ 4 ሰዎች መያዛቸውንም አስታውቀዋል። ሰዎቹ የተያዙት በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች በተካሄደ አሰሳ ነው። ድርጅቱ ትይዩ መንግስት በመመስረት እና ወንጀለኛ የኤኮኖሚ መዋቅር መስርቷል በሚል ወንጀልም ተከሷል። ሚኒስትር ዶብሪንድት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ቡድኑ ከዛሬ ጀምሮ መታገዱን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት በነርሱ መረጃ መሠረት የጀርመን ንጉሳዊ አገዛዝ 6ሺህ ገደማ ደጋፊዎች አሉት። በመንግስት መረጃ መሠረት ደግሞ የደጋፊዎቹ ቁጥር 1ሺህ ገደማ ነው የሚል ግምት አለ። በዛሬው ዘመቻ አራት ሰዎች ታስረዋል። ከመካከላቸው የየጀርመን ንጉሳዊ አገዛዝ መሪ ይገኝበታል።
የአቃቤ ሕግ ቢሮ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የቡድኑን መስራች ፔተር ፊትሴክን ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሌሎች ሦስት ተጠርጣሪዎች እድሜያቸው ከ37 እስከ 59 የሚደርስ እንደሆነ አስታውቀዋል። ። የቡድኑ ዋነኛ አባላት ሙሉ በሙሉ ቀኝ ጽንፈኛ ባይሆኑም እንደ ቀን ጽንፈኛ ነው የሚቆጠሩት። ፓርላማን ጨምሮ ለዴሞክራሲያዊም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊ መዋቅሮች እውቅና አይሰጡም። ቀረጥም ሆነ የማኅበራዊ ዋስትና መዋጮ ወይም ቅጣቶችን ለመክፈል ፈቃደኛም አይደሉም።
እየሩሳሌም እስራኤል ጦሯ በሚቀጥሉት ቀናት በሙሉ ኃይሉ ጋዛ ይገባል አለች
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው በሚቀጥሉት ቀናት በሙሉ ኃይሉ ጋዛ እንደሚገባ አስታወቁ። የኔታንያሁ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ዘመቻውን ለማጠናቀቅ በሚቀጥሉት ቀናት በሙሉ ኃይላችን እንገባለን ብሏል። ኔታንያሁ ዛሬ እንደተናገሩት ዘመቻውን ከፍጻሜ ማድረስ ማለት ሀማስን ማሸነፍ መሆኑን ይኽውም ሀማስን ማውደም እንደሆነ ተናግረዋል። ምናልባት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሊደረግ ይችላል እንጂ ያሉት ኔታንያሁ ጦርነቱን የምናቆምበት ሁኔታ የለም እስከ መጨረሻው እንጓዛለን ብለዋል። እስራኤል ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ምህረቱ የሀማስ ጥቃት በኋላ በከፈተችው የአጸፋ ጥቃት አብዛኛዎቹ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸው የተነገረ ከ52 ሺህ በላይ ጋዛ ውስጥ መገደላቸውን ሀማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ስቶክሆልም ዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች ድርጅት ስደተኞችን ወደ መጡበት እንዲመልስ ስዊድን ገንዘብ ልትለግስ ነው
ስዊድን ስደተኞችን ወደመጡበት መመለሱ እንዲፋጠን ለዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች ድርጅት በምህጻሩ IOM 100 ሚሊዮን የስዊድን ክሮነር ወይም 10.3 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገባች። ሀገሪቱ ገንዘቡን ለድርጅቱ የምትለግሰው ስደተኞችን እንዲጠርዝና ከኢራቅ ከሶማሊያ ከኡዝቤክስታን እና ከቱኒዝያ ሕገ ወጥ በሚባለው መንገድ የሚካሄደውን ስደት ለማስቆም መሆኑን የስዊድን መንግስት አስታውቋል። በጎርጎሮሳዊው 2015 በርካታ ተገን ጠያቂዎች ወደ ስዊድን ከጎረፉ በኋላ በተከታታይ ሀገሪቱን የመሩት የግራና የቀኝ ክንፍ መንግስታት የሀገሪቱን የተገን አሰጣጥ ሕግ አጥብቀዋል። የስዊድን መንግሥት ለIOM የለገሰው ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ከኢራቅ ሶማሊያ ኡዝቤክስታን እና ቱኒዝያ ስዊድናና ሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የሚገኙ ስደተኞችን በብዛት ለማባረር ይውላል ብሏል ።
በርሊን የተመድ ዋና ፀሐፊ አባል መንግስታት መዋጮ እንዲከፍሉ ተማጸኑ
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬሽ አባል ሀገራት ለዓለም የሰላም ማስከበር ዘመቻ የበኩላቸውን የመዋጮ ድርሻ እንዲከፍሉ ተማጸኑ። የተመ የሰላም አስከባሪ መስሪያ ቤት በአሁኑ ጊዜ ኮንጎ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ደቡብ ሱዳን ሊባኖስ ፣ቆጵሮስ እና ኮሶቮ ጨምሮ በሌሎች ሀገራት 11 ዘመቻዎችን ይመራል። ይሁንና ከመካከላቸው በጎርጎሮሳዊው ሰኔ መጨረሻ በሚያበቃው በአሁኑ የስራ ዘመን ለዘጠኙ የተመደበው በጀት 5.6 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህም ካለፈው ዓመት በጀት ጋር ሲነፃጸር በ8.2 በመቶ ያንሳል። በሕጉ መሠረት የድርጅቱ 193 አባል ሀገራት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው ። ይሁንና ይህን ሁሉም ተግባራዊ ባለማድረጋቸው የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ከባድ የገንዘብ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ጀርመን ውስጥ በሰላም ማስከበር እጣ ፈንታ ላይ በተነጋገረው ጉባኤ ላይ ጉተሬሽ ተናግረዋል። እናም ጉተሬሽ አባል ሀገራት በሙሉ ግዴታቸውን በማክበር መዋጮአቸውን በሙሉ በጊዜው እንዲከፍሉ አሳስበዋል።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ