የግንቦት 4 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017ሪያል ማድሪድ ትናንት ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ በባርሴሎና ሽንፈት ገጥሞታል ። ባርሴሎና ዋንጫ የማንሳት እድሉን እጅግ ከፍ አድርጓል ። የባዬርን ሙይንሽን የረዥም ዘመን ተጨዋች ቶማስ ሙይለር ከቡድኑ ስንብት ተደርጎለታል ። አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ከባዬር ሌቨርኩሰን መለየቱን ይፋ አድርጓል፤ ሪያል ማድሪድ ይጠብቀዋል ።
54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቅቋል
ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲከናወን የቆየው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቅቋል ። በወንድ እና ሴት የፍጻሜ ውድድር ከተካሄደባቸው መካከል፦ የ5000፤ የ1500 እንዲሁም የ100 ሜትር በአራት የዱላ ቅብብል ይገኝበታል ።
በአጠቃላይ ውድድሩ 1,379 አትሌቶች፣ 31 ቡድኖች እና ተቋማት እንዲሁም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሳተፋቸው ተገልጧል ። ለአንድ ሳምንት ግድም በተከናወነው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በድምር ውጤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 279 ነጥብ በማምጣት በአንደኛነት አሸንፏል ። መቻል 242 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ ሸገር ሲቲ በ143 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።
በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድበ ባርሴሎና ዳግም ጉድ ሆነ
በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ትናንት ሪያል ማድሪድን 4 ለ3 በመርታት የደረጃ መሪነቱን ይበልጥ አጠናክሯል ። በትናንቱ ግጥሚያ ቀዳሚውን ግብ በተገኘ ፍጹም ቅጣት ምት 5ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ኪሊያን እምባፔ ነበር ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ይኸው ግብ አዳኝ ኪሊያን እምባፔ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር ባርሴሎናን በገዛ ሜዳው እና በደጋፊው ፊት አስደንግጦ ነበር ። ሁለተኛው ግብ እንድትቆጠር ቪንሰንት ጁኒዬር በድንቅ ሁኔታ ከተከላካዮች እግር ፊት አስቀድሞ ኳሷን ለኬሊያን እምባፔ በመላክ ብቃቱን ዐሳይቷል ።
በ19ኛው ደቂቃ ባርሴሎና ያገኘውን የማእዘን ምት ኤሪክ ጋርሺያ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል ። በገዛ ሜዳቸው ግራ ተጋብተው የነበሩት የባርሴሎና ደጋፊዎችን እፎይ ያስባለች እና ያነቃቃች ግብ ። ከተከላካዮች ዕይታ ውጪ ከግቡ በስተግራ ቆሞ አጋጣሚውን ሲጠብቅ የነበረው ላሚን ያማል 32ኛው ደቂቃ ላይ ባርሴሎናን አቻ ያደረገውን ግብ ተረጋግቶ አስቆጥሯል ። ሰባት የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተደርድረው ሌሎች ተጨዋቾች ላይ ትኩረት ባደረጉበት ቅጽበት ለብቻው ነጠል ብሎ የነበረው ላሚን ጉድ አድርጓቸዋል ። የሚያዝያ 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ጨዋታው ተጋግሎ 34ኛ ደቂቃ ላይ ራፊና ዲያስ 3ኛውን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ባርሴሎናን ቀደሚ አድርጓል ። ይኸው ራፊና 41ኛው ደቂቃ ላይም የተሻማ ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ በማለፍ ግብ ሳይሆን ቀርቷል ። በፈጣን እንቅስቃሴው የሪያል ማድሪድ ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ የቆየው ራፊና 45ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተሳክቶለት ለራሱ ሁለተኛ ለባርሴሎና የማሸነፊያዋን አራተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል ።
የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ፍጥጫ አሁንም ቀጥሏል
መደበኛው 45 ደቂቃ ተጠናቅቆ በጭማሪው 8ኛ ደቂቃ ላይ እምባፔ ለሪያል ማድሪድ ቢያስቆጥርም ግቡ ከጨዋታ ውጪ ተብሏል ። ወዲያውም ባርሴሎና 4 ለ2 እየመራ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቅቆ ረፍት አድርገዋል ። ከረፍት መልስ 52ኛው ደቂቃ ላይ ላሚን ያማል ሪያል ማድሪድን ያስደነገጠ ግብ ቢያስቆጥርም ለጥቂት ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮበታል ። 70ኛ ደቂቃ ላይ ቪንሰንት ጁኒዬር በድንቅ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ኪሊያን እምባፔ 3ኛ ግብ ለሪያል ማድሪድ በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል ። ኪሊያን እምባፔ በ27 ከመረብ ያረፉ ኳሶች የላሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ ነው ። የባርሴሎናው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ25 ግብ ይከተለዋል ።
ባርሴሎና በትናንቱ ግጥሚያ 94ኛ ደቂቃ ላይ በሎፔዝ አምስተኛ ግብ ቢያስቆጥርም ኳሷን ቀደም ብሎ በእጁ በመንካቱ ግቡ ተሽሯል ። ብርቱ ፍልሚያ የታየበት የሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ፦ በ97ኛው ደቂቃ ላይ በባርሴሎና የ4 ለ3 ድል ተጠናቅቋል ። ከ2 ለ0 ተነስቶ በማሸነፍ 82 ነጥብ የሰበሰበው ባርሴሎና እና ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዲተር ሐንስ ፍሊክ ፈንጥዘዋል ። በ75 ነጥቡ የተወሰነው ሪያል ማድሪድ እና አሰልጣኙ ካርሎ አንቼሎቲም አንገታቸውን ደፍተዋል ። 20 ቡድኖች ያሉት የስፔን ላሊጋ ሊጠናቀቅ ሦስት ዙር ጨዋታዎች ይቀሩታል ። የሚያዝያ 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የፊታችን ሐሙስ ማታ ቀጣይ 36ኛ ጨዋታውን ከኢስፓኞል ጋር የሚያደርገው ባርሴሎና ካሸነፈ ዋንጫውን መውሰዱን ያረጋግጣል ። በላሊጋው 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢስፓኞል ጨዋታውን ቢያሸንፍ በቀጣይ የአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግ ማጣሪያ ተሳታፊ ለመሆን ጭላንጭል ዕድል ይኖረዋል ። ሆኖም በማጣሪያው ተሳታፊ ለመሆን ባርሴሎናን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። የሐሙሱ ጨዋታ ለኤስፓኞል ብርቱ ፈተና ሲሆን ለባርሴሎና ዋንጫውን መውሰዱን የሚያረጋግጥበት ወሳኝ ግጥሚያ ።
አርሰናል ከኋላ ተነስቶ በሊቨርፑል ከመሸነፍ ተርፏል
አርሰናል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ አስቀድሞ መውሰዱን ያረጋገጠው ሊቨርፑልን አንፊልድ ውስጥ ትናንት ገጥሞ ከ2 ለ0 በመነሳት አቻ ተለያይቷል ። 83 ነጥብ ላለው ሊቨርፑል የትናንቱ ግጥሚያ ምንም የሚፈይደው ነገር ባይኖርም 68 ነጥብ ላለው አርሰናል ግን ወሳኝ ነበር ። በሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ባፓሪ ሳንጃርሞ የተሰናበተው አርሰናል የትናንቱን የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ አሸንፎ ቢሆን ኑሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን መቶ በመቶ ያረጋግጥ ነበር ። በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሰባተኛ ላይ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት እንኳን በ62 ነጥቡ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድል አለውና ።
ለአውሮጳ ሊግ የምድብ ጨዋታ የማለፍ ዕድል ይዞ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላ ነጥቡ 63 ነው ። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 69 ያደርሳል ። ያም በመሆኑ 68 ነጥብ ያለው አርሰናል የሻምፒዮስ ሊግ ተሳታፊነቱን የሌሎች ቡድኖችን ውጤት ሳይጠብቅ ለማረጋገጥ ከቀጣይ ጨዋታዎቹ ቢያንስ አንዱን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። በርካታ የግብ ክፍያ ስላለውም አንድ ጨዋታ አቻ ቢወጣም ያዋጣዋል ።
ኢፒስዊች ታወን፣ ላይስተር ሲቲ እና ሳወዝሀምፕተን ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ወራጆች ናቸው ። በእነሱ ምትክ ባለፈው ሳምንት የሁለተኛ ዲቪዚዮን ዋንጫውን የወሰደው ሊድስ ዩናይትድ ወደ ዋናው ፕሬሚየር ሊግ ማለፉን አረጋግጧል ። ሌላኛው ማለፉን ያረጋገጠ ቡድን በርንሌይ ሲሆን፦ ለቀሪ ሦስተኛ ቦታ ደግሞ ሼፊልድ ዩናይትድ፣ ሰንደርላንድ፣ ኮንቬንትሪ እና ብሪስቶል ሲቲ ይጋጠማሉ ።
ሐምቡርግ ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ አለፈ
በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረዳቸው የተረጋገጠ ቡድኖች ናቸው ። በእነሱ ምትክ ሐምቡርግ ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ ማለፉን አረጋግጧል ። አንድ ጨዋታ እየቀረ ሁለተኛ ሆኖ የሚጨርስ ቡድን ማንነት ገና ዐልታወቀም ። በዋናው ቡንደስሊጋ 29 ነጥብ ሰብስቦ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሐይደንሀይም ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ቡድን ጋር በደርሶ መልስ ይጋጠማል ። ከሁለቱ የአሸነፈ ቡድን የቀጣይ ቡንደስሊጋ ተሳታፊ ቦታ መያዙን ያረጋግጣል ። የመጋቢት 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡንደስሊጋ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያሉት ቡድኖች የሰበሰቡት ነጥብ በቀጥታ ወደ ቡንደስሊጋው ለማለፍ ዕድል ይሰጣቸዋል ። አንድ ዙር ቀሪ ጨዋታ እየቀረ ሐምቡርግ በ59 ነጥብ ይመራል ። ኮሎኝ በ58 ይከተላል ። ኤልቨርስበርግ እና ፓዴርቦን 55 ነጥብ አላቸው ። ዱይስልዶርፍ እና ካይዘርስላውተርንም በ53 ነጥባቸው ገና የማለፍ ዕድላቸው አልመከነም።
ዣቪ አሎንሶ ከባዬርን ሌቨርኩሰን መለየቱን ይፋ አድርጓል
አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ በጀርመን ቡንደስሊጋ ምሥጢር ሁኖ የቆየውን ከባዬርን ሌቨርኩሰን የመለየቱን ጉዳይ አረጋግጧል ። ባዬርን ሌቨርኩሰንን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደረሰው ዣቪ አሎንሶን ሪያል ማድሪድ በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን መጠናቀቂያ ይጠብቀዋል ። ዣቪ አሎንሶ ባለፈው ሳምንት ዐርብ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የባዬርን ሌቨርኩሰን ውሉ ለመጠናቀቁ ገና አንድ ዓመት ይቀረው እንደነበረም ገልጧል ።
በሌላ ዜና፦ ለባየርን ሙይንሽን የረዥም ዘመን ተጫዋች በመሆን ክብረ ወሰን የሰበረው አጥቂ የ35 ዓመቱ ቶማስ ሙይለር ከቡድኑ ስንብት ተደረገለት ። በአሊያንትስ አሬና ቅዳሜ ዕለት የተሰናበተው በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ0 ካሸነፉ በኋላ ነው ። ቶማስ ሙይለር ለባየርን ሙይንሽን 750 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል ። የዘንድሮውን ጨምሮ 13 የቡንደስሊጋ ዋንጫዎችን ቡድኑ ሲያሸንፍ አብሮ ነበር ። ለሁለት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም በጀርመን ብሔራዊ ቡድኑ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫዎችንም ማንሳት ችሏል ። ቶማስ ሙይለር በባየር ሙይንሽን ታሪክ ከጌርድ ሙይለር (570) እና ሮቤርት ሌቫንዶብስኪ (344) ቀጥሎ 248 ግቦችንን በማስቆጠር ሦስተኛ ግብ አግቢ ነው ። 222 ግብ ሊሆኑ የሚችሌ ኳሶችንም በማመቻቸት ይታወቃል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ