የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ትናንት ቅዳሜ በደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ በትንሹ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።
ካለፈው ዓርብ ምሽት ጀምሮ ለ10 ሰዓታት ያለማቋረጥ ሲጥል የነበረው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፉ ከ 200 በላይ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው አፈናቅሏል። ከሟቾቹ ሁለት ህጻናት እና ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ይገኙበታል ። በጎርፉ ዘጠኝ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተጠራርገው ሲወሰዱ በስድስት አውራ ጎዳናዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የጎርፉን መከሰት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ተይዘው እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት እንዳመለከተው ካለፈው የሚያዝያ ወር የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ 45 ሺ ያህል ሶማሊያውያን በ,ጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሶማሊያ በተደጋጋሚ በሚደርስባት የአየር ንብረት ለውጥ ሰላባ ስትሆን ፤ በጎርጎርሳዉያኑ 2023 ለ100 ሰዎች ህልፈት እና ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቁት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ምክንያት የሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅ ደርሶባት ነበር።
በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በብሄራዊ ጦሩ ቁጥጥር ስር ባለ እስር ቤት ላይ ባደረሱት የአየር ጥቃት 19 ሰዎች ተገደሉ ።
ትናንት ቅዳሜ ኤል ኦብይድ በተሰኘችው ከተማ ላይ በድሮን ሳይፈጸም አልቀረም በተባለው ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ 45 እስረኞች ተጎድተዋል። ጥቃቱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ዳርፉር ውስጥ በሚገኘው የአቡ ሾክ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ካደረሱ አንድ ቀን በኋላ የተፈጸመ ነው ተብሏል። በጥቃቱ 33 ሰዎች መገደላቸውን የርዳታ ሰራተኞን ጠቅሶ የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት ዘግቧል። የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያው በሳምንቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሰለባ መሆኑንም ነው ዘገባው ያመለከተው።
የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ባሳለፍነው ሳምንት ለስድስት ተከታታይ ቀናት የብሔራዊ ጦሩ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው በምስራቃዊቷ የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ላይ ብርቱ የድሮን ጥቃት ፈጽሟል። በጥቃቱ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻዎችን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት መድረሱ ተዘግቧል።
የሱዳን ብሔራዊ ጦር የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል የድሮን ድጋፍ ትሰጣለች ሲል ይከሳል። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ግን ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።
መነሻዋን ሊቢያ አድርጋ ስደተኞችን ጭና ወደ ጣልያን ስትጓዝ ከነበረች አነስተኛ ጀልባ 59 ሰዎችን ከአደጋ መታደጉን አንድ የጀርመን የህይወት አድን የግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ።
ድርጅቱ እንዳለው በጀልባዋ ላይ የነበሩ ሰዎችን ሲታደግ ቀደም ብሎ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ ሶስት ሰዎች በጀልባዋ ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል። የግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንዳለው የፕላስቲክ ጀልባዋ በጣሊያኗ የላምፔዱሳ አቅራቢያ ስትንሳፈፍ ከታየች በኋላ ባደረገው የአውሮፕላን ቅኝት ስደተኞቹን መታደግ ችያለሁ ብሏል። በአደጋው የሞቱት ሁለቱ የሶስት እና የአራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናት እንደሆኑ ነው የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ያመለከተው ። ለሁለቱ ህጻናት ህልፈት የውኃ ጥም ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የጠቀሰው የግብረ ሰናይ ድርጅቱ የሟቾቹን አስክሬን መረከቡን አመልክቷል። ከሟቾች አንዱ ስደተኛ ግን ባህር ውስጥ ሰጥሞ መሞቱ ነው የተጠቀሰው ።
ከምዕራባዊ ሊቢያ ባለፈው ረቡዕ ሳትነሳ አልቀረችም የተባለችው ጀልባዋ አቅጣጫዋን ስታ ለቀናት ባህር ላይ ስትንሳፈፍ መቆየቷ ነው በዘገባው የተመለከተው። ከጀልባዋ በህይወት የተረፉ ስደተኞችም ወደ ላምፔዱሳ ደሴት መወሰዳቸውን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።
ዩክሬን ከሩስያ ጋር የተኩስ አቁም ንግግር ልታደርግ መሆኑን ፕሬዚዳንት ቮልዶሚር ዜሌንስኪ አስታወቁ።
ሁለቱ ሃገራት ለሶስት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የተኩስ አቁም ለማድረግ የፊታችን ሐሙስ የቱርኳ ኢስታንቡል ውስጥ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዙን ዜሌንስኪ ይፋ አድርገዋል። የዜሌንስኪ የተኩስ አቁም ንግግር ሊደረግ ነው የሚለው ሃሳባቸው የተሰማው የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፊታችን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ/ም የተኩስ አቁም ንግግር ዕቅድ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። ቮልዶሚር ዜሌንስኪ በዛሬው መግለጫቸው " በመጨረሻም ሩስያ ጦርነቱን ለማብቃት ፍላጎት ማሳየቷ በበጎ ጎኑ ይወሰዳል " ብለዋል።
ሁለቱ ሃገራት ወደ አስከፊው ጦርነት ከገቡ ከጎርጎርሳዊው 2022 ወዲህ ፊት ለፊት ተነጋግረው አያውቁም።
አሁን የሃገራቱ የመገናኘት ዜና ከመሰማቱ አስቀድሞ ዩክሬን እና አጋሯ የአውሮጳ ህብረት የተኩስ አቁሙ ለሰላሳ ቀናት የጸና እንዲሆን ይሻሉ ፤ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ አልሰጡም።
የሁለቱን ሃገራት የተኩስ አቁም ንግግር ለማስተናገድ ብርቱ ፍላጎት እንዳላት ቱርክ ስትገልጽ የአውሮጳ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዉያን ሃገራት ንግግሩ ውጡታማ እንዲሆን ከወዲሁ ግፊት ማድረግ ጀምረዋል።
ጀርመን ከአጎራባች የአውሮጳ ሀገራት ተሻግረው የመጡ 19 ተገን ጠያቂቂዎችን ጨምሮ በርካታ ስደተኞችን ከድንበሯ መለሰች ።
ርምጃው በስደተኞች ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አቋም እንዳለው የተነገረለት አዲሱ የጀርመን መንግስት የመጀመሪያው ነው ተብሏል። መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርስ የሚመሩት አዲሱ መንግስት ስልጣን በተረከበ በሁለት ቀናት ውስጥ ጀርመን የምትዋሰንባቸው ድንበሮች ቁጥጥር ሲያጠናክር በዚሁ የተገን ጥያቄ ያቀረቡ 19 ስደተኞች ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ቢልድ አም ዞንታግ የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል።
ባለፉት የሀሙስ እና ዓርብ ቀናት ብቻ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች ወደ ጀርመን ለመግባት ከሞከሩ 365 ሰነድ አልባ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች መካከል 19 ተገን ጠያቂዎችን ጨምሮ 305 ስደተኞች ጀርመን እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
የተገን ጥያቄ ካቀረቡ ስደተኞች ውስጥ “ለጥቃት የተጋለጡ” ናቸው የተባሉ አራት ሰዎች ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል።
የተገን ጠያቂዎች እና የስደተኞች ጥያቄ ውድቅ ለመደረጉ ህገ ወጥ ቪዛ እና የተጭበረበሩ የጉዞ ሰነዶች ይዘው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።
ጀርመን በሁለቱ ቀናት ጥብቅ የድንበር ቁጥጥሯ ተመላሽ ከተደረጉ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች በተጨማሪ 14 ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር አውላለች። በተጨማሪ በሌሎች 48 ሰዎች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱን ያመለከተው ዘገባው የግራ ቀኝ እና የቀን አክራሪ አስተሳሰቦችን ጨምሮ አክራሪ የእስልምና አስተምሮ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ዘጠኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ታምራት ዲንሳ