የግንቦት 20 አከባበር፣ የዴሞክራስያዊ ስምረት ትግራይ ምሥረታ እና የኢሳያስ አፈወርቂ ንግግር
ሐሙስ፣ ግንቦት 21 2017የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሹማምንት ትላንት ረቡዕ ግንቦት 20ን በመቐለ ከተማ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ዘክረዋል። አሁን በስደት ላይ የሚገኙት መንግሥቱ ኃይለማርያም ይመሩት የነበረው የደርግ ሥርዓተ-መንግሥት በሟቹ መለስ ዜናዊ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የተተካበት 34 ዓመት ክበረ-በዓል ከትግራይ ውጪ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ትኩረት አልተሰጠውም።
የግንቦት 20 አከባበር ጉዳይ ወትሮም የከረረ የፖለቲካ ውዝግብ በሚታይባቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አንደኛው መነጋገሪያ ሆኖ ታይቷል። ፌስቡክ እና ኤክስን በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሠፈሩ ሐሳቦች እና የሚደረጉ ውይይቶች በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው የፖለቲካ ልዩነት ግፋ ሲልም የብሔር ፖለቲካ ስንጥቃት የሚንጸባረቅበት ነው።
የህወሓት/ኢሕአዴግ አመራሮች እና ታጋዮች ግንቦት 20 ቀን 1983 ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች እያጋሩ በርካቶች “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት ያጋራሉ። ሌሎች ደርግን የተካው ኢሕአዴግ አጠፋ ያሉትን እየጠቀሱ ይኮንናሉ።
ሱሌይማን በኤክስ “እንደ ብዝሃ ብሔር ያላት ሃገር ኢትዮጵያ ግንቦት 20ን አለማክበር እና የትግራይ ሕዝቦች የነፃነት ቀን አስመስሎ መመልከት ግለሰባዊ የጥላቻ አመለካከት እና የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችን መናቅ ነው” ብለዋል። ቲጂ በቀለ በፌስቡክ “ወደድንም ጠላንም ይሄ የታሪካችን አንድ አካል ነው። ልንፍቀውም ሆነ ልናጠፋው የማይቻለን ወርቃማ ታሪክ” የሚል አጭር መልዕክት አስፍረዋል። አቤሴሎም ምትኩ “ሀቅ ነው የታሪካችን አካል ነው። ግን ለአንዳችን ሕይወትን ለአንዳችን ሞትን ለሀገራችን በብሔር መከፋፈልን፤ ለባንዲራችን መጠራጠርን ይዞልን የመጣ ቀን ነው። ያም ሆነ ይህ ግን የታሪካችን አንዱ አካል ነው” የሚል ምላሽ አስፍረዋል።
ጀማል አወል “ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ህዝብ ከአንድ አስከፊ ሥርዓት ወደ ሌላ የባሰ ጭቆና የተሸጋገረበት፤ የነጻነት እና የእኩልነት ንጋት ያላየበት ቀን ነው። ይህ ቀን በሀገሪቱ ታሪክ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ግፍ እና መከራ የደረሰበት፣ ንብረት የተዘረፈበት፣ ንጹሃን በግፍ የታሰሩበት እና የተገደሉበት፣ እናት ልጆቿን በግፍ ከእቅፏ ተነጥቀው ለሞት የተገበሩበት እንዲሁም በእስር ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች የተፈጸሙበት አሳዛኝ ምዕራፍ መባቻ ነው” የሚል አስተያየት አላቸው።
ጀማል “ለ27 ዓመታት በዚህ መሰረት የነገሰውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመቃወማቸውና ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ብቻ በርካታ ዜጎች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች ለእስር፣ ለእንግልትና ከሀገር እስከመሰደድ የተዳረጉት በዚህ ግንቦት 20 ባወረሰው መርዛማ አገዛዝ ነው” ሲሉ በፌስቡክ ጽፈዋል።
ዮናታን ይመኑ “ግንቦት 20 በትግራይ ክልል ብቻ ታስቦ ውሏል። በሌላው የኢትዮጵያ ግዛት ወፍ የለም” ሲሉ ዶይቼ ቬለ በሠራው ዘገባ ሥር አስፍረዋል። እኔም አየሁ የሚል መጠሪያ የሚጠቀሙ ግለሰብ “ግንቦት 20 በመስከከረም 2 ስትስቅ ነበር” የሚል መልዕክት አስፍረዋል። አሌክስ ተክሌ “የትግራይ ሕዝብ ከ60 ሺሕ በላይ ወጣቶች የግንቦት 20ን ድል ለመጎናፀፍ ሰውቷል። ብሔር ብሔረሰቦችም ማነታቸው ታውቆ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ክልል መስርተዋል። ህወሓት ይህን ቀን ቢዘክር አይገርምም” ሲሉ ጽፈዋል። ኡርጂ ታሚ “የኢትዮጵያ የባሕር በር የተዘጋበት ሐዘንም በዛው ይተወስ” ሲሉ ሱፊያ ከማል ደግሞ “ግንቦት 20 ኢትዮጵያ የባህር በር ያጠችበት ቀን ነው” የሚል ተቀራራቢ መልዕክት አጋርተዋል።
ከህወሓት ወደ ስምረት
የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች እየተመሠረተ ነው የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ” ያገኘው ባለፈው ሰኞ ነበር። ክልላዊ ፓርቲ ይሆናል የተባለው ዴሞክራስያዊ ስምረት ትግራይን በመመሥረት ላይ ከሚገኙ መካከል ከአቶ ጌታቸው በተጨማሪ የቀድሞው የትግራይ ክልል የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም አንዱ ናቸው። አቶ ረዳኢ ፓርቲው የሚመሠረተው “ህወሓትን ለማሻሻል” በእርሳቸው እና በጓዶቻቸው የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
አቶ ረዳኢ የፓርቲውን ጊዜያዊ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ፎቶ ግራፍ አያይዘው በፌስቡክ ገጻቸው ይፋ ሲያደርጉ አሮን አሳይ “ትግላችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ። በዚህ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል” የሚል መልዕክት አስፍረውላቸዋል። ወዲቶም ሳባውያን ግን “ሥልጣን ላለማጣት ነው እንጂ፤ የህዝብ ይሉንታ የሌላቹ መሆናቹሁን ኣረጋግጣችሁልናል” ሲሉ ተችተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ እና ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው አለመግባባት በኋላ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከነበራቸው ኃላፊነት ሲነሱ በፌድራል መንግሥት በተሰጣቸው ሥልጣን ምክንያት በምሥረታ ላይ የሚገኘው ፓርቲ ዋንኛ መነጋገሪያ ሆኗል። አዲሱ ደረጄ “ይህ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም። በዐቢይ አሕመድ ትግራይን ለመከፋፈል የተፈጠረ አሻንጉሊት ነው። ጥሩው ነገር በትግራይ እነዚያን አሻንጉሊቶች በቁም ነገር የሚወስዳቸው የለም” ብለዋል። መብራህቶም ዘነበ “ህወሓት የሚተካ ምድራዊ ኃይል ከየትም አይገኝም” የሚል አስተያየት አላቸው።
ወዲ ግን “ቀጥሉበት፤ ሥር የሰደደውን የትግራይ ችግር ለመፍታት መፍትሔው ይህ ነው” የሚል አስተያየት በእንግሊዘኛ ቋንቋ አስፍረዋል። ፍሰሐ ገብረሥላሴ “ከእናንተ አዲስ ነገር የለም” ሲሉ ጽፈዋል። ጉዑሽ ገብረሥላሴ ደግሞ “ከልሒቃኑ በፊት ለትግራይ ሕዝብ መሥራት ያለባችሁ ይመስለኛል” የሚል ምክር ለግሰዋል። ዝናቡ ቲ ጸጋይ “ወጣቱን ትውልድ በጭራሽ አታባክኑ። ይህን መተኪያ የሌለው አቅም በአስቸኳይ አደራጅታችሁ አንቀሳቅሱ” ሲሉ ጽፈዋል።
“የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ባለ ሁለት ስለት ጎራዴ ናቸው። ለአዎንታዊ ለውጥ ጉልበት አሊያም የመከፋፈል እና የግጭት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚሉት ኬፕለር ማሌ ከፓርቲው መሥራቾች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በፌስቡክ ባጋሩት ፎቶ ሥር “እንኳን ደሕና መጣችሁ” ብለዋል።
ስለ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያውያን ምን አሉ?
ፕሬዝደንት ኢሳያስ የኤርትራ 34ኛ የነጻነት በዓል በአስመራ ሲከበር ባሰሙት ንግግር በኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተዋል። ኢሳያስ በአንድ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ያላቸው ግንኙነት ቢሻክርም ኤርትራ ለለውጡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠችው ድጋፍ እንደማይቆጩ ተናግረው የትግራይ ልሒቃንን አበሳጭተዋል። በሌላ ወገን ሥልጣን ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መንግሥት ከኦሮሙማ ጽንሰ ሐሳብ ጋር አስተሳስረው የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የብሔሩን ልሒቃን አስቀይመዋል።
ቢኒያም በኤክስ ባሰፈሩት መልዕክት የፕሬዝዳንቱ ንግግር በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱት አቋም ተቀጥላ እንጂ አዲስ እንዳልሆነ ጽፈዋል። “ኢሳያስ አፈወርቂ ሻዕቢያን ተቀላቅሎ የደርግን መንግሥት በሚዋጋበት ጊዜ፤ የደርግን መንግስት የአማራ ህዝብ መንግስት ነው በማለት ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም ሆኑ ኤርትራውያን የአማራን ህዝብ እንደ ጠላት ህዝብ እንዲያዩ ሲቀሰቅስ እና ሲሰራ ነበር። በኢህአዴግ ጊዜም የኢህአዴግ መንግስት የትግሬ መንግስት ነው በማለት ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ኤርትራውያን ለትግራይ ህዝብ ጥላቻ እንዲኖራቸው በሚችለው መንገድ ሁሉ ሲሰራ ነበር” በማለት ቢኒያም የ79 ዓመቱን የኤርትራ ፕሬዝደንት ይተቻሉ።
“አሁን ደግሞ የኦሮሙማ መንግስት በማለት ሌሎች ህዝቦች የኦሮሞ ህዝብ ላይ እንዲነሱ እየቀሰቀሰ ይገኛል” የሚሉት ቢኒያም “ይህ የኢሳያስ ባህሪ ነው። የእሱ ቋሚ የሆነ የፖለቲካ ስትራቴጂ ነው” የሚል አቋም አላቸው።
ቴዎድሮስ አማረ “ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚያክል በሳል ፓለቲከኛ አፍሪካ የላትም። የአፍሪካ መሪዎች የሚያውቁት የፈረንጅ አጀንዳ በማስፈፀም አይሆንም ያሏቸውን ሁሉንም አይነት መሳርያ በመጠቀም መጨፍጨፍ ከፈረንጆች እርዳታ እና ብድር ለማግኘት ይጠቀሙበታል” የሚል አስተያየት ዶይቼ ቬለበሠራው ዘገባ ሥር አስፍረዋል።
አባተ አበበ “ክቡር ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት፤ በተለይ በኢትዮጵያ ጥቅም እና የዉስጥ ጉዳይ፤ የራስዎት እያረረቦት የሰዉን የሚያማስሉ እንደ እርሶ ያለ በጥባጭና ሴረኛ መሪ አለ እንዴ?” ሲሉ ጠይቀዋል። አበቃ ዘመኑ የሚል የፌስቡክ ስም የሚጠቀሙ ግለሰብ “እርሶ በደርግ፣ በኢህአዴግ እና በብልጽግና ተዋጉ። አሁን ደሞ ምን ፈለጉ? የእርሶም ህዝብ፣ የኢትዮጵያም ህዝብ ጦርነት አይፈልግም እርሶ እና አብይ ከፈለጋችሁ ተጋጠሙ። ያሸነፈ ይጠቅልል” የሚል በስላቅ የተሞላ አማራጭ አቅርበዋል።
መብራቱ ከበደ “የበርካታ አመቶች አገርን የመምራት ልምድ ያላቸው እና ለንግግር ብዙም የማይቸኩሉ፤ ፊጥ ፊጥ የማያበዙት፤ ከሚመሩት ህዝብ ጉያ የለምንም ጋርድ ገብተው የሚወጡት ወዲ አፎም በእውነቱ አገራችንን የገለጹበት መንገድ መሬት ላይ ቁልጭ ብሎ የሚታየውን እውነታ ብቻ ነው” የሚል አስተያየታቸውን አስፍረዋል። ሚካኤል ደስታ ግን “ወኪል እያለ ራሱን ያፅናና። ከምዕራባውያን ጋር አሸባሪ በመርዳቱ እና ጨቋኝ በመሆኑ እንደ አንድ ነፃ መንግስት ዲፕሎማሲ መመስረት ያልቻለው ኢሳያስ አፈወርቂ። ግትር ሽማግሌ ኤርትራያውያንን ያደኸየ፤ ለስደት የዳረገ በሞት እንጂ በቁሙ ስልጣን የማይለቀው ኢሱ” ሲሉ ነቅፈዋቸዋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ