የጋዛው ጦርነት ያጠላበት የጀርመንና የእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 60ኛ ዓመት
ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 2017በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 12 ቀን 1965 ዓ.ም. ነበር ጀርመንና እሥራኤል ከረዥም ጊዜ ዝግጅት በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት የበቁት። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ ከዛ ቀደም ብሎ ከ20 ዓመታት በፊት ያበቃ ቢሆንም የዶቼቬለው የንስ ቱራው እንደዘገበው ፣ ናዚ ጀርመን አውሮጳ በሚገኙ አይሁዶች ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ትውስታ ስር የሰደደ በመሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን መመስረቱ ጊዜ ወስዷል። በናዚ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቁጥራቸው 6 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የተነገረ አይሁዶች መጨፍጨፋቸው ፣ በጦርነቱ የተፈጸመው ግፍ ጠባሳ በቀላሉ እንዳይሽር ማድረጉ አልቀረም። የዛሬ 60 ዓመትየእስራኤልና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ የተመሰረተው በያኔው የጀርመን መራኄ መንግስት ሉድቪክ ኤርሀርድና በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሌቪ ኤሽኮል ስምምነት ነበር።ስምምነቱ ሊፈፀም የተቻለውም ሁለቱ ሀገራት ቀስ በቀስ መቀራረብ ከጀመሩ በኋላ ነበር ። ከዲፕሎማሲያዊ ስምምነቱ በኋላ በቀጠሉት አሥርት ዓመታትም ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ በኤኮኖሚ በወታደራዊ በሳይንሳዊ እና በባህል መስኮች የቅርብ ትብብር መስርተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነኙት 60ኛ ዓመት አከባበር ላይ ግን የጋዛው ጦርነት ጥላ አጥልቶበታል። ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱበት 60ኛ ዓመት በታሰበበት ባለፈው ሳምንት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ኢሳክ ሄርዞግ ጀርመን ነበሩ። በማግስቱ ደግሞ የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እና ሄርዞግ ወደ እስራኤል በመሄድ በዚያ በተካሄዱ ዝግጅቶች እለቱ ታስቧል። ጦርነቱ ካበቃ ከ80 ዓመታት በኋላም ጀርመን ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ግን ከባድ መሆኑ ግን አልቀረም።
ሄርዞግ በርሊን በነበሩበት ወቅት የጀርመን ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር እስራኤል ጋዛ ለሚገኙ ሲቭሎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ የጣለችውን እገዳ በማንሳት ለዓለም አቀፍ ሕግም ተገዥ እንድትሆን ጥሪ አቅርበው ነበር። የእሥራኤል ጠላቶች ለሕግ ባይገዙም እኛ ግን ለሕግ መገዛት አለብን ሲሉ ሽታይንማየር ሄርዞግን አሳስበው ነበር።
«እስራኤል ከዛሬ አንድ ዓመት ከ6 ወር አንስቶ በጋዛ ከአሸባሪዎች የሚሰነዘሩ አደጋዎችን ለመከላከል ውጊያ እያካሄደች ነው። ይህም በአሁኑ ጊዜ ተጠናክሮ እየተካሄደ ነው። ጥፋቶቹ እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። የጀርመን መገናኛ ብዙሀን በየቀኑ በጋዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚደርስባቸውን ስቃይ እየዘገበ ነው። በዚህ የማይነካው የለም ። እናም ለዚህ ነው እርስዎ ሰብዓዎ እርዳታ ለጋዛ እንዲገባ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ የምጠይቅዎት።በእርዳታ ላይ የተጣለውe እገዳ መነሳት አለበት። የሰብዓዊ እርዳታዎች አቅርቦት፣ የህክምና አቅርቦት ሌላ ጊዜ ሳይሆን አሁን መቅረብ አለባቸው። »
ከዚሁ ጋርም እራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላትም ተናግረዋል ።ሽታይንማየር የዛሬ ሳምንት ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ 60ኛው ዓመት አከባበር እሥራኤል በሄዱበት ወቅት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ጋር ስለጋዛው ጦርነት ተነጋግረዋል። ይሁንና ከውይይቱ በፊት ነታንያሁ ጋዛ ሰርጥ የሚገኘውን አሸባሪ የሚሉትን ሀማስን የሚያፈርስ ያሉትን አዲስ ጥቃት እስራኤል መጀመርዋን አስታውቀው ነበር። ዘመቻው እስካሁን ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን ዘመቻ ለማሳካትምፍልስጤማውያን ጋዛ ከሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ እስራኤል አዛለች። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፣ሽታይንማየር ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ከቆረጠባቸው ከነታንያሁ ጋር ለመነጋገር የያዙትን እቅድ እንዲሰርዙ አስቀድሞ ጥሪ አቅርቦላቸው ነበር። አመንስቲ ጥሪውን ያቀረበው ነታንያሁ ጋዛ ውስጥ ይፈጸማል በሚባለው የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋት አላቸው የሚባለውን ሚና በመጥቀስ ነበር።
የዛሬ ሳምንቱ የእስራኤል ፕሬዝዳንት የጀርመን ጉብኝት የተካሄደው ጀርመን በወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ መሪ ፍሪድሪሽ ሜርስ የሚመራ አዲስ መንግስት በመሰረተች በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር ። መራኄ መንግስት ሜርስ እንደ ቀደሙት የጀርመን መራኄ መንግስታት ሁሉ ጀርመን ለእስራኤል ልዩ ሃላፊነት እንዳለባት የሚያምኑ መሪ ናቸው። የቀድሞዋ የጀርመን መራኄ መንግስት አንጌላ ሜርክል የዛሬ 17 ዓመት እስራኤልን በጎበኙት ወቅት በእስራኤል ፓርላማ ወይም ክኔሴት ተገኝተው ሀገራቸው ይህ ሃላፊነት እንዳለባት ተናግረው ነበር። በሜርክል አመለካከት ጀርመን ለእስራኤል ህልውና እና ደኅንነት ልዩ ፖለቲካዊ ሃላፊነት አለባት። ይህ ፖለቲካዊ እንጂ ሕጋዊ ባይሆንም ከርሳቸው ከቀደሙት አብዛኛዎቹ እንዲሁም ከርሳቸው በኋላም የተከተሉት መራኄ መንግስታት ይህን መሰረታዊ መርኅ ሲተገብሩ ቆይተዋል። ።
ምንም እንኳን እስራኤል በጋዛ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ወቀሳ ቢቀርብባቸውም የጀርመን ፖለቲከኞች ሀማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. እስራኤል ውስጥ የሽብር ጥቃት ከፈጸመ በኋላ እስራኤል ራስዋን የመከላከል መብት አላት ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ። የአውሮፓ ኅብረት ዩናይትድ ስቴትስ ጀርመን እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት አሸባሪ ሲሉ የፈረጁት ሀማስ ባደረሰው በዚሁ ጥቃት ቁጥራቸው 1200 የሚደርስ ሰዎች ሲገደሉ ከ250 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ታግተው ነበር።
ያም ሆኖ ጀርመን ለእስራኤል ህልውና እና ደኅንነት አለኝ የምትለውን ልዩ ፖለቲካዊ ሃላፊነት ማሳካቱ ግን እጅግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የዶቼቬለው የንስ ቱራ በዘገባው ጠቅሷል። እስራኤል በጋዛ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ጀርመን ውስጥ የሚቀርቡባቸው ትችቶች እየጨመሩ ነው። እስራኤል ትንናት ለመጀመሪያ ጊዜ እርዳታ እንዲገባ ፈቀደች እንጂ ካለፈው መጋቢት አንስቶ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ፍልስጤም ግዛት እንዳይገባ ከልክላ ነበር። ይህም በጋዛ ረሀብና ሞት አስከትሏል። ከዛሬ አንድ ዓመት ከ6 ወር በፊት ሀማስ ላደረሰው ጥቃት አጸፋ እስራኤል በከፈተችው ጦርነት የሀማስ የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው መረጃ መሰረት ሀማስ በሚያስተዳድረው የፍልስጤማውያን ግዛት ከ 52 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ሜርስ መራኄ መንግስት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ARD ለተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ የእሥራኤል ጉዳይ በጣም የሚሳስበን ነው። ግልጽ መሆን ያለበት የእስራኤል መንግስት በዓለም ቀቀፍ ሕጎች በዓለም አቀፍ የጦር ሕጎች ስር የተቀመጡትን ግዴታዎች ማሟላት አለበት በማለት አስጠንቅቀዋል።
እስራኤል በጋዛ አጠናክራ የቀጠለችው ዘመቻ ከብሪታንያ ከካናዳ እና ከፈረንሳይ መንግስታት በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል። የሶስቱ ሀገራት መሪዎች ማዕቀብን ጨምሮ በዝርዝር ያልገለጹትን ተቸባጭ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል። ከእሥራኤል ጋራ ታሪካዊ ግንኙነት አለኝ የምትለው ጀርመን በዚህ ስምምነት ውስጥ እጇን አሳገባችም።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በምህጻሩ ICC የእስራኤልጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ እና በቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸውe ዮአቭ ጋላንት ላይ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2024 የእስር ማዘዣ ቆርጧል።ICC የእስር ማዘዣውን ከቆረጠበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በጋዛ ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች ነው። ከፍርድ ቤቱ መስራቾች አንዷ የሆነችው ጀርመን ነታንያሁ ጀርመን ከመጡ ማሰር አለባት። ይሁንና በየካቲት ወር በተካሄደው የጀርመን ምርጫ ማግስት ከነታንያሁ ጋር በስልክ የተነጋገሩት ሜርስ ነታንያሁ ጀርመንን እንዲጎበኙ እና ሳይታሰሩም ከጀርመን መውጣት የሚችሉበትን መንገድ እና ዘዴ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር ። ሆኖም ሜርስ መራኄ መንግሥት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ግን ይህን አባባላቸውን አልደገሙትም። ይልቁንም ሜርስ በመራኄ መንግስትነት ከተመረጡ በኋላ ለARD በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከመስከረም 26 2016 ዓምህረሩ ጥቃት በኋላ እስራኤል ራስዋን የመከላከል መብት እንዳላት ተናግረው ሆኖም አሁን አስከፊው ጦርነት በሚካሄድበት በጋዛ ሰርጥ ሀገሪቱ ሰብዓዊ ግዴታዎቿን መውጣት እንደሚገባት አሳስበዋል ይህኑኑ ጉዳይም ለጀርመን ፓርላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሰሙት ንግግር መንግስታቸው ከእስራኤል ጎን እንደሚቆም አረጋግጠው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ የጋዛ ሰብዓዊ ይዞታ እንዲሻሻል ጀርመን የበኩልዋን ጥረት እንደምታደርግ እና እንደምትጠብቅም ተናግረዋል። የቱክስ አቁም ላይ ለመድረስ የሚካሄደው ድርድር ይሳካል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
«ለተኩስ አቁም የሚደረገው ድርድር እና የጀርመን ዜጎችም የሚገኙበት ሀማስ የያዛቸውን ታጋቾች በሙሉ መልቀቁ ይሳካል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የጋዛ ህዝብ በተለይም የህጻናት የሴቶችና የአዛውንቶች ሰብዓዊ አያያዝ እንዲሻሻል የሚደረገውን ጥረት በሙሉ እንደግፋለን፤ይሻሻል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን። ክቡራትና ክቡራን እንዲሁም የስራ ባልደረቦች ይህ ሰብዓዊ ግዴታ ነው። በከአካባቢው የተከሰተው ከፍተኛ ለህይወት የሚያሰጋ ረሀብ በአስቸኳይ ሊወገድ ይገባል»
ነታንያሁ በርሊን ከመጡ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል። የቀድሞ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ ግን በተደጋጋሚ እስራኤልን ጎብንተዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የወጣባቸው የእስር ማዘዣ ላይ የተነሳው ውዝግብ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ምን ያህል የተወሳሰበና እስካሁንም ድረስ በጋዛው ጦርነት ተጽእኖ ውስጥ እንደወደቀ የሚያሳይ ነው። ጀርመን ከእስራኤል ጋር የመንግስት ምክክሮችን ታካሂዳለች ይህም የሁለቱም መንግስታት የካቢኔ አባላት በአንድ ላይ የሚያካሂዱት ስብሰባ ነው። ምክክሮቹም የግንኑነቻቸውን ልዩ ጠቀሜታ እንዲያጎሉ ታስበው የሚደረጉ ናቸው። ጀርመን እስካሁን እስራኤልን ጨምሮ ከ12 ሀገራት ጋር መሰል ምክክሮችን ታካሂዳለች። ከእስራኤል ጋር የመጨረሻ ምክክር ከተካሄደ ሰባት ዓመት አልፎታል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ